የሀገርን ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል የመንግሥትን ምስጢር በውጭ ላለ የሽብር ቡድን አሳልፎ በመስጠትና በሀገሪቱ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ በማድረግ ወንጀል የተጠረጠሩ አምስት ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ተጠርጣሪዎቹ የአዲስ አባባ የህወሓት ጽህፈት ቤት የቀድሞ ኃላፊ አቶ ተወልደ ገብረጻዲቅ፣ የህግና ፍትህ ዳይሬክተር አቶ ተስፋለም ይሕደጎ እና የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የደህንነት ኃላፊ አቶ አጽብሃ አለማየሁ እና ሌሎች ሁለት ግለሰቦች ናቸው።
መርማሪ ፖሊስ እስከአሁን በተጠርጣሪዎች ላይ የሠራቸውን ምርምራ ለፍርድ ቤቱ ያብራራ ሲሆን፥ የሰው ምስክር መቀበሉንና የመንግሥትን ምስጢር አሳልፈው መስጠታቸውን የሚያስረዱ ማስረጃዎች መሰብሰቡን ተናግሯል።
በሀገሪቱ ሁከትና አመፅ እንዲፈጠር ሲሠሩ ነበር ያለው መርማሪ ፖሊስ፤ በሰኔ 22 እና 23 /2012 ዓ.ም የሀገሪቱን ህገ መንግሥት በኃይል ለማፍረስ ከሌሎች የሽብር ቡድኖች ጋር በመሥራት ተጠርጥረው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን በማስረዳት ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀን እንዲሰጠውም ጠይቋል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው በድጋሚ ተይዘው መቅረባቸው ተገቢነት የለውም፤ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድ አይገባም የሚል መቃወሚያ አቀርበው ተጠርጣሪዎቹ በዋስ እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱ መዝገቡን አስቀርቦ መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በተመሳሳይ ዜና በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ የግድያ ወንጀል የተጠረጠረውና ሸሽቶ በሐምሌ 3 ቀን 2012 ዓ.ም አዳአ ድሬ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በቁጥጥር ስር የዋለው ከበደ ገመቹ ትናንት ፍርድ ቤት ቀረበ።
በችሎቱ ውሎ መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው ተጨማሪ ጊዜ በተጠርጣሪው ላይ በሠራው የምርመራ ሥራ ከተጠርጣሪው እጅ ላይ ከተገኘው ስልክ የድምፅ እና የመልዕክት ልውውጥ ከኢትዮ ቴሌኮም በማስመጣት በርካታ ማስረጃ ማሰባሰቡን ለችሎቱ አብራርቷል።
በእጁ ላይ የተገኘው የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ለብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ኤጀንሲ ለምርመራ መላኩን ያብራራው መርማሪ ፖሊስ፤ በትናንትናው ችሎት መገለጽ የሌለባቸው ከበስተጀርባ ያሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ምርመራዎች እየተደረጉ መሆናቸውን ገልጿል።
በዚህ መልኩ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ለማከናወን ለተጨማሪ ምርመራዎች 14 ቀን እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
ተጠርጣሪው በአስተርጓሚ አስተያየት ካለው እንዲያቀርብ የተጠየቀ ቢሆንም፤ ምንም ዓይነት አስተያየት እንደሌለው ምላሽ ሰጥቷል።
ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱ ለተጨማሪ ምርመራ ለፖሊስ 14 ቀን በመፍቀድ ውጤቱን ለመጠባበቅ ለነሐሴ 19 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በተያያዘ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ቃለ መጠየቅ በማድረግ ፕሮግራሙን ቆርጦ በማቅረብ፤ እንዲሁም ሰኔ 22 እና 23/ 2012 ዓ.ም በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኦ.ኤም.ኤን) አመጽና ብጥብጥ እንዲነሳ በመቀስቀስ የተጠረጠረው ጋዜጠኛ ጉዩ ዋርዮም ትናንት ፍርድ ቤት ቀርቧል።
መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠርጣሪው ጋዜጠኛ ከላይ በተጠቀሰው ሚዲያ አመጽ እንዲነሳ ቅስቀሳ ማድረጉን የሚያስረዳ የሰነድ ማስረጃ ማሰባሰቡን እና ተጨማሪ የምስክር ቃል መቀበሉን ተናግሯል።
በእጁ ላይ የተገኘ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ በፎረንሲክ እያስመረመረ መሆኑንም መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።
ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሰልጣን እና ከተለያዩ ተቋማት ማስረጃ ለማሰባሰብና ቀሪ ምርመራ ለመሥራት ተጨማሪ 14 ቀን እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱም የምርመራ መዝገቡን መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለነሐሴ 8 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።(ኢኘድ)