Connect with us

በእነጀዋር መሐመድ ጉዳይ የሚቀርቡ ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ቃላቸውን ሊሰጡ ነው

በእነጀዋር መሐመድ ጉዳይ የሚቀርቡ ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ቃላቸውን ሊሰጡ ነው
Photo: Facebook

ወንጀል ነክ

በእነጀዋር መሐመድ ጉዳይ የሚቀርቡ ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ቃላቸውን ሊሰጡ ነው

አቶ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሐምዛ አዳነ እና ሌሎች 14 ግለሰቦች በተጠረጠሩበት የቅድመ ምርመራ መዝገብ 5 ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ቃላቸውን እንዲሰጡ ችሎቱ ትእዛዝ ሰጠ።

ጠቅላይ ዐቃቤ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሐምዛ አዳነ እና ሌሎች 14 ግለሰቦች በተከፈተባቸው የቅድመ ምርመራ መዝገብ በተጠረጠሩበት ወንጀል ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ቃላቸውን እንዲሰጡ ይፈቀድል ሲል የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ የወንጀል ችሎትን ጠይቆ ተፈቅዶለታል።

ምስክሮችን ለመጠበቅ የወጣውን አዋጅ መነሻ በማድረግም አምስት ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ቃላቸውን እንዲሰጡ ችሎቱ ትእዛዝ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለሐምሌ 30 ቀን 2012 ዓ.ም በዚሁ ፍርድ ቤት ባስከፈተው የቀዳሚ ምርመራ መዝገብ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ የዓለምወርቅ አሰፋ፣ ጌቱ ተረፈ፣ ታምራት ሁሴን፣ በሽር ሁሴን፣ ሰቦቃ ሳሮ፣ ኬኔ ኡመቻ፣ ጋሪ አብደላ፣ ቦጋለ ድሪብሳ፣ ሐምዛ አዳነ፣ ሸምሰዲን ጣፋ፣ መለሰ ድሪብሳ እና ቦና የተሰኙ 14 ተጠርጣሪዎች ተካተውበታል።

ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው አቤቱታ መሠረት 15 ምስክሮች እንዲያስረዱ ጠይቋል።

ከ15ቱ መካከል አምስቱ የምስክሮች እና የወንጀል ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ 699/2003 በተለያዩ አንቀጾች በተጠቀሰው መሠረት የምስክሮች ማንነት ሳይገለጽ፣ ስማቸውም ሳይጠቀስ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡም ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤት ያቀረበው አቤቱታ ሊደርሰን ይገባል፤ እሱን ሰምተን መልስ እንድንሰጥ ወይም መቃወሚያ እንድናቀርብ የመሰማት ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ሊከበር ይገባል ሲሉም አመልክተዋል።

በተያያዘም የተጠርጣሪ ግለሰቦቹ ጠበቆች ይህንን አቤቱታ ሰምተን የምስክሮቹን ማንነት በግልጽ ልናውቅ ይገባል ሲሉ የሕገ ምንግሥቱን አንቀጽ 20 ጠቅሰው አመልክተዋል።

ከሰፊ ክርክር በኋላ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከመረመረ በኋላ ብይን ሰጥቷል።

በዚህ ብይን ዐቃቤ ሕግ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ እንደሚመሠርት ለማወቅ መቻሉን፣ ይህ የቅድመ ምርመራ ችሎት በተጠርጣሪዎች ላይ ውሳኔ የማያስተላለፍ በመሆኑ አቤቱታው ለተጠርጣሪዎች ሊደርስ አይገባም የሚለውን የዐቃቤ ሕግ መቃወሚያ ተቀብሏል።

ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ቃላቸውን ይስጡ የሚለውን የዐቃቤ ሕግ አቤቱታ ከሕገ መንግሥቱ ጋር አይጋጭም በማለት አምስቱም ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ማንነታቸው ሳይታወቅ የምስክርነት ቃላቸውን ሊሰጡ ይገባል ብሏል።

በመሆኑም ችሎቱ የሁሉንም ምስክሮች ቃል ለመቀበል ለነሐሴ 04 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
(EBC)

Click to comment

More in ወንጀል ነክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top