ኑ እርስ በእርስ የምንጯጯህውን ጩኽት አንበጣው ላይ እንጩኽ፤
እርስ በእርስ የምንሰዳደደውን ትተን አንበጣውን እናሳድ፤ አሊያ ከርሞ ሸማች መኾን የለም
****
ከሄኖክ ስዩም
የአንበጣ መንጋው አሁንም ስጋት ነው፡፡ አሁንም በደረሰ ሰብል አናት የተኛ መዓት ነው፡፡ ድምጻችንን አንሰስት፣ አንዱ ሌላው ላይ ለመጮህ ያወጣነውን ድምጽ ለአንበጣ ማባረሪያ እናሰማው፡፡ ከክልሌ ውጣ በሚባልባት ህብረት አልባ ሀገር እንዲህ ያለ አንበጣ ማሳችን ላይ እንዳሻው ቢሆን አይገርምም፤ አሁንም ግን ስለ ምስኪኑ ገበሬ እናስብ፤
አንድ አንበጣ ከመቶ በላይ እንቁላል ትፈለፍላለች፡፡ በሰዓት 15 ኪሎ ሜትር መጓዝ ለአንበጣ ወክ ነው፡፡ እንዲህ ቁጥር ስፍር የለሌለው አንበጣ የደረሰ ሰብል ካጋጠመው አንዳችም አያስተርፍም፡፡
ዛሬም አንበጣን በሰው ጉልበት፣ በፉሪዛና በወንጭፍ ለማባረር የምንታገል ህዝቦች መሆናችን ያስገርማል፡፡ ከመቶና ከሺህ ዓመታት በፊትም እንዲህ ያለ ነገር ሲገጥመን እንዲህ ባለው ኋላ ቀር ዘዴ አባረናል፡፡ ዓለም ሌላ ምዕራፍ ደርሶ ዛሬም አርሶ አደሩ ስቃይ ሲገጥመው በምታውቀው ፍታ የሚል ሥርዓት ከጫንቃው አልወረደም፡፡ ያም ቢሆን ግን ከተሜው ጉዳዬ አይደለም ከሚለው መንፈስ መላቀቅ አለበት፡፡
አንበጣውን ከምድራችን ካላጠፋን ቀጣዩን አመት ስለመሸመት ማውራት አንችልም፡፡ ፈተናው ለገበሬው ብቻ የሚመስለው ሞኝ ነው፡፡ ገበሬው ወቅቶ ከምሮም ከችግር ያልወጣ መከረኛ ነው፡፡ ሀገር ግን እንዲህ ያለውን ፈተና ትኩረት ሰጥታ ካላሸነፈችው ትሸነፋለች፡፡ የሚባላ ፖለቲከኛ የሚበላው ባጣ ህዝብ መካከል እጣ ፈንታው ምን እንደሆነ መገመት ነው፤
ሳይንስ በአንድ ካሬ ኪሎ ሜትር እስከ አርባ ሚሊዮን አንበጣ ሊሰፍር ይችላል ማለት ነው፡፡ የራሱን ክብደት ሦስት እጥፍ መብላት የሚችል ፍጥረት በዚህ ቁጥር ሰፍሮ ዝም ማለት መቅሰፍትን አሜን ብሎ የመቀበል ያክል ይቆጠራል፡፡
ደርሰው ያልተነሱ ሰብሎችን በፍጥነት ለማንሳት ዩኒቨርሲቲዎችና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መረባረብ አለባቸው፡፡ መከላከያን መሰል አካላት ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ ሰሞነኛ ተግባር ነው፡፡ መንጋውን ከኢትዮጵያ ስለማስወጣት ከዳር ዳር አብሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡
የአንበጣ መንጋው መነሻ አካባቢ የሚደረጉ የኬሚካል ርጭቶችና ቁጥጥርም ቢጠናከር መልካም ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰዓት የጥፋት መሆኑን ለግብርናው ልሂቃን መንገር አይጠበቅብንም፤ መንጋውን በትኖ ለማባረር የአባቶችን እውቀት ከዘመኑ ጥበብ ጋር ማቆራኘት ያስፈልጋል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ፍጥነት፤