Connect with us

“የመንግስትን ውሳኔ እደግፋለሁ” ክቡር ገና

"የመንግስትን ውሳኔ እደግፋለሁ" ክቡር ገና
Photo: ሲራራ

ነፃ ሃሳብ

“የመንግስትን ውሳኔ እደግፋለሁ” ክቡር ገና

“የመንግስትን ውሳኔ እደግፋለሁ” ክቡር ገና

መንግሥት የኢትዮጵያ አየር መንገድን ድርሻ ወደ ግል የማዞር እንቅስቃሴውን ለጊዜውም ቢሆን ለማቆም መወሰኑን  በገንዘብ ሚኒስትሩ በኩል ሰምተናል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የሕዝብ ሀብት የሆነውን አየር መንገድ ወደ ግል ለማዛወር ሲያስብ፣ ይህን ውሳኔ በርካታ ባለሙያዎች ስንቃወም ቆይተናል፡፡

የሕዝብ ንብረት የሆነውን አየር መንገድ ከግልም ከውጭ ለሚመጡ የግል ባለሀብቶች ነበር ሀብቱን ለማዞር የተፈለገው፡፡

መንግሥት አየር መንገዱን ለመሸጥ ለምን እንደፈለገ ምክንያቱን ስንጠይቅ የሚሰጠው መልስ የተለያየ መሆኑ በሕዝቡም ሆነ በባለሙያው ላይ ብዥታ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡

አንዳንድ ጊዜ አየር መንገዱ የሚሸጠው አገሪቱ ያለባትን እዳ ለማቃለል እንደሆነ ሲነገር ይደመጣል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ አየር መንገዱ የተሻለ ሥራ እንዲሠራ ለማድረግ ነው የሚል ምክንያት ሲሰነዘር ይስተዋላል፡፡

በተለያየ ጊዜ የተለያየ ምላሽ እና ምክንያት ሲሰጥ ነው የቆየው፡፡ ይህን ድርጅት ለምን መሸጥ እንደተፈለገ ግልጽ በሆነ መልኩ ማወቅ አልተቻለም፡፡

አየር መንገዱ ሁሉም በሚያውቀው መልኩ አትራፊ ተቋም ነው፡፡ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ የምትታወቅበት መለያዋ ሆኖ ነው የቆየው፡፡ በተጨማሪም በርካታ ሠራተኞችን ቀጥሮ እያሠራ ያለ ተቋም ነው፡፡

የተሻለ ትርፍ ለማግኘት ነው የሚሸጠው እንዳይባል አየር መንገዱ በየጊዜው በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በአትራፊነት የሚሻለም ተቋም ነው፡፡ ለመሸጡ ትርጉም የሚሰጥ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት በመንግሥት በኩል እስካሁን ድረስ አልተሰጠም፡፡

አሁንም ቢሆን ይሸጣል የተባለውን ተቋም አይሸጥም ሲሉ የተለየ ምክንያት ስላገኙ ነው የሚል ግምት የለኝም፡፡ ምናልባት አሁን ላይ የአየር ትራንስፖርት ገበያው እየተቀዛቀዘ ስለመጣ አየር መንገዱን ለመግዛት ፍላጎት ያለው አካል ከመጥፋቱ ጋር የሚያያዝ ምክንያት ሊኖረው እንደሚችል ግን እገምታለሁ፡፡

ቀድሞም ቢሆን አየር መንገዱን ለመሸጥ የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ ምክንያት አልነበረም፤ አሁንም ውሳኔያቸውን ለመሻር ኢኮኖሚያዊ ምክንያት አላስቀመጡም፡፡ ቀድሞም ቢሆን ውሳኔው ፖለቲካዊ ነበር፡፡ አሁንም የወሰኑት ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው፡፡

አየር መንገዱ በውጭ ተቋም የሚተዳደር ቢሆን ኖሮ ይኼ አየር መንገድ እስከዛሬ ያለፈባቸውን ችግሮች አልፎ ዛሬ በስኬት ላይ ይገኝ ነበር ወይ? የሚለው በአግባቡ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነበር፡፡ የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ በጣም ጠንካራ እና ትልቅ አየር መንገድ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ አየር መንገድ መንቀሳቀስ ያቃተው አየር መንገድ ሆኗል፡፡

የኬንያም አየር መንገድ ወደ ግል ባለሀብት ድርሻው ከተዛወረ በኋላ እንደቀድሞው ትርፋማ መሆን ተስኖት ኪሳራ ውስጥ ሲገባ ተመልክተናል፡፡ አየር መንገዶች ብዙ ችግር አለባቸው፡፡ የእኛም አየር መንገድ ችግር አለበት፡፡ ነገር ግን የእኛ አየር መንገድ ችግሮቹን ተቋቁሞ ትርፋማ እየሆነ ያለ ተቋም ነው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለምን ትርፋማ ሆነ ከተባለ ዋናው ምክንያት በመንግሥት በመደገፉ ነው፡፡ በአስተዳደር ሥራው ላይ የግሉ ዘርፍ ተሳታፊ ሆኖ ቢቆይ ግን በእርግጠኝነት ተቋሙ አንድ ችግር ሲገጥመው የግል ዘርፉ ትርፍ አሳዳጅ በመሆኑ የግል ዘርፉ ተቋሙን ጥሎ ይጠፋል፡፡ የመንግሥት የአሁኑ ውሳኔ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ውሳኔው ግን በጣም የሚደገፍ ነው፡፡

አየር መንገዱ የብዙ ሰዎች ላብ እና ወዝ የተንጠፈጠፈበት ተቋም ነው፡፡ በብዙ ልፋት እና ድካም ያደገ እና እየሰፋ ያለ መሥሪያ ቤት ነው፡፡ በልዩ ሁኔታ ሊጠበቅ እና እንክብካቤ ሊደረግለት የሚገባው አገር ምልክት የሆነ ንብረት ነው፡፡

መንግሥት ወደ ግል እንዲዞሩ ቀደም ብሎ ውሳኔ ካሳለፈባቸው ተቋማት መካከል የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎትም ይገኝበታል፡፡ እሱንም ወደ ግል ለማዛወር የተወሰነው ውሳኔ ለጊዜው እንዲቆም ተደርጓል፡፡ ይህም የሚደገፍ ውሳኔ ነው፡፡

የሆነ ሆኖ አሁንም በግልጽ የተቀመጠ ነገር አይታይም፡፡ መንግሥት ቀድሞ በያዘው የፕራይቪታይዜሽ ዕቅድ ላይ የፖሊሲ ለውጥ ያምጣ፣ ሐሳቡን ይተወው አይተወው በግልጽ የተቀመጠ ነገር ባይኖርም በተቋማት ደረጃ በተያዙ ዕቅዶች ግን የመንግሥትን ወላዋይነትን እያሳየ ነው፡፡ “የለውጥ አመራሩ” የሊብራል ኢኮኖሚ ተከታይ መሆኑን የሚያሳዩ ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ ነበር፡፡ 

አሁን ግን  የወላዋይነት መንፈስ እየታየበት ነው፡፡  እንዲህ ያለ ወላዋይነት ደግሞ የሚመጣውታ ቀድሞውንም ውሳኔው በጥናት  ተመርኩዞ  ካለመወሰኑ ጋር ተያይዞ  የሚመጣ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ቀሪ ድርጅቶችን ለመሸጥ እየሄደበት ያለውን መንገድ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ለውሳኔ የደረሰባቸውን ጥናቶችም በአግባቡ ማየት አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡

እኔ በግሌ የፕራይቬታይዜሽን ሐሳብን ሙሉ በሙሉ የምቃወም ሰው አይደለሁም፡፡ ከመንግሥት ይልቅ የግል ዘርፉ ቢሰማራባቸው ውጤታማ የሚሆኑ ተቋማትን መንግሥት ወደ ግል ባለሀብቱ ቢያዞር ቅሬታ የለብኝም፡፡ ተገቢም ነው፡፡ ለአብነት በቀደመው ጊዜ በመንግሥት ሥር የነበሩ የቢራ ፋብሪካዎች ነበሩ፡፡

መንግሥት ፋብሪካዎቹን ወደ ግል በማዛወር የቢራ ፋብሪካዎቹ ዛሬ ላይ ውጤታማ ሆነዋል፡፡ መሰል ተቋማት ካሉ አሁንም ቢሆን ወደ ግል መዛወር አለባቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡ የትኛዎቹ ተቋማት ናቸው መሸጥ ያለባቸው? መቼ እና እንዴት ባለ ሁኔታ? የሚሉት ጥያቄዎች ግን በገለልተኛ ባለሙያዎች በአግባቡ ተጠንተው መቅረብ ይገባቸዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ሲወሰን በቂ ውይይትና ምክክርም መደረግ  አለበት፡፡ በሕዝብ አንጡራ ሀብት ለዘመናት የተገነቡ የአገር ንብረት ስለሆኑ እንዲሁ እንደዘበት አንድ ቡድን ብቻ ብድግ ብሎ ሊወስንባቸው አይገባም፡፡

ሲራራ-ቢዝነስ|ኢኮኖሚ

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top