Connect with us

አንበጣውን-አንበጣ እንሁንበት…

አንበጣውን-አንበጣ እንሁንበት
Photo: Social media

ማህበራዊ

አንበጣውን-አንበጣ እንሁንበት…

አንበጣውን-አንበጣ እንሁንበት፡፡

ዛሬ የጨነቀውን ገበሬ ካልደረስንለት ነገ ከተሜው በተራው ይጨነቃል፡፡  

ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የተከሰተው የአንበጣ ወርሺኝ አርሶ አደሩን መከራ ውስጥ ከትቶታል፡፡ ከትግራይ እስከ ኡጋዴን ጫፍ በኢትዮጵያ ሰብል አናት ያረፈውን አንበጣ አንበጣ ካልሆንበት ችግሩ ይከፋል፡፡

የበርሃ አንበጣው ለምክክር ለክርርክር እና ለዝግጅት ጊዜ የሚሰጥ አይደለም፡፡ እሱ አንዴ አለፈ ማለት አንድ አመት ከንቱ ሆነ ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ገበሬው ቅዝዝ ያለው፡፡ በጉልበቱ ታግሏል፡፡ በድምጹ እየጮኽ ለማባረር ሞክሯል፡፡ ከመሬት ታግሎ ለፍሬ ያበቃውን ማሽላ አልፎ ሂያጅ የአንበጣ አጥፊ ሲያወድምበት ጭንቅ ላይ ወድቋል፡፡ ይኼ ጭንቅ ገበሬው ቤት አይቀርም፤ ነገ ከተሜውን የሚያዳርስ ችግር ነው፡፡

የበርሃ አንበጣው አፋርን ትግራይን ሶማሊን አማራና ኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል፡፡ በድሬዳዋ የገጠር ቀበሌያትም በተመሳሳይ፤ ግብርና ሚኒስቴር አሁንም ርብርብ ያስፈልጋል ሲል ጥሪ አድርጓል፡፡ 

የግብርና ሚኒስቴር መግለጫ ስምንት አውሮፕላኖች ተጨማሪ ከውጪ በማስመጣት ለመከላከል የሚሰራው ስራ እንደሚቀጥል ነግሮናል፡፡ አዲስ አበባ ኑሮ ሲወደድ ታለቅስ እንደሁ እንጂ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር ግብርና ዝናብ እጥረትና መሰል የአንበጣ ሰብል አውዳሚ ጉዳይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምሳሌያዊ ንግግሮችን ያህል የማያነጋግራት ከተማ ሆናለች፡፡

እያንዳንዱ ዜጋ በአንድም በሌላም አቅጣጫ አንበጣ እንደወረረው ቢረዳ መልካም ነው፡፡ የችግሩ ውጤት የሁሉን ደጃፍ የሚያንኳኳ ኪሳራ ነውና፤ አሁንም የበርሃ አንበጣ ቁጥጥር ርብርቡ ጊዜ ሳይሰጠው እንዲቀጥልና ሀገራዊ አጀንዳ እንዲሆን ማድረጉ ቀዳሚው ቢሆን መልካም ነው፡፡

በአሸተው አዝመራ አናት ሆ ብሎ የመጣው አንበጣ ውሎ አድሮ መግዛት በሚፈልገው ሸማች ኑሮ ክንዱን ማሳረፉ አይቀርም፡፡ ለወገን ማሰቡ ቢቀር ለራስ ሲባል አንበጣውን አንበጣ እንሁንበት፡፡

Click to comment

More in ማህበራዊ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top