እነ ጃዋር መሐመድና ተቋማቱ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ‹‹ፈጽመናል አልፈጸሙም›› በሚል ተካካዱ
በተጠረጠሩበት የአመፅ ጥሪ ማድረግ፣ የሰው ሕይወት ማጥፋት፣ የእርስ በርስ ግጭት መፍጠር፣ የንብረት ውድመትና ሌሎችም የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኘው እነ አቶ ጃዋር መሐመድና ሁለቱ የመንግሥት ተቋማት (ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ፌዴራል ፖሊስ) የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ‹‹ፈጽመናልና አልፈጸሙም›› በሚል ተካካዱ፡፡ ሁለቱ ተከራካሪ ወገኖች ‹‹ፈጽሜያለሁና አልፈጸሙም›› በሚል ሊተማመኑ ያልቻሉት፣ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት ነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ከአቶ ጃዋር መሐመድ መታመም ጋር ተያይዞ ሰጥቶት በነበረው ትዕዛዝ ላይ ነው፡፡
ፍርድ ቤቱ ነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በነበረው ችሎት ሰጥቶት የነበረው ትዕዛዝ ተጠርጣዎቹ በሙሉ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እንዲያደርጉ፣ አቶ ጃዋር እንዲታከም፣ ከባለቤቱና ከልጁ ጋር የቪዲዮ ኮንፈረንስ ተመቻችቶለት እንዲነጋገርና ተጠርጣሪዎች ካሜራ ባልተገጠመበት ቦታ ሆነው ከጠበቆቻቸው ጋር በነፃነት እንዲነጋገሩ ነበር፡፡
ፍርድ ቤቱ ከአራት ቀናት ቆይታ በኋላ ነሐሴ 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ እንደተሰየመ (ቀደም ብሎ በነበሩት ችሎቶች ሲሰየሙ የነበሩ ዳኛ ተቀይረዋል) ትዕዛዞቹ መፈጸም አለመፈጸማቸውን ሲያረጋግጥ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርምራ ቢሮ በተወካዩ በኩል ለፍርድ ቤቱ በላከው ደብዳቤ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ ሐምዛ አዳነና አቶ ሸምሰዲን ጠሀ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ተደርጎላቸው ነፃ መሆናቸው መረጋገጡን አስታውቋል፡፡ ስለሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ግን ያለው ነገር የለም፡፡
አቶ ጃዋር በራሱ ወጪ የቪዲዮ ኮንፈረንስ ተዘጋጅቶለት ባለቤቱንና ልጁን አግኝቶ መነጋራቸውንም ፖሊስ ማረጋገጡን ዳኛው ለታዳሚው ተናግረዋል፡፡ ሕክምናን በሚመለከት ግን በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት እንደማንኛውም ተጠርጣሪ በፌዴራል ፖሊስ ሪፈራል ሐኪም ቤት እንዲታከም ተጠይቆ ‹‹በራሴ ሐኪም ካልሆነ አልታከምም›› በማለት ፈቃደኛ አለመሆኑንም የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ በደብዳቤ ማሳወቁን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ በተወካዩ በኩል ለፍርድ ቤቱ የላከውን ደብዳቤ በመቃወም መጀመርያ የተናገረው አቶ ጃዋር ነው፡፡ እንደገለጸውም እሱ ካለው የፖለቲካ ተሳትፎ አንፃር ሲደረግበት ከነበረው ከፍተኛ የሆነ የስም ማጥፋት ዘመቻ አንፃር ለሕይወቱ ሥጋት አለው፡፡ ምክንያቱንም ለፖሊሶችና ለዓቃቤ ሕግ አቅርቦ በግል ሐኪም እንዲታይ ተስማምተው ነበር፡፡ ለጊዜው ሐኪም እንዳልተገኘ ነግረውት የቆየ ቢሆንም፣ ነሐሴ 13 ቀን 2012 ዓ.ም. እነሱ ቢስማሙም በበላይ ኃላፊዎች ትዕዛዝ በግል ሐኪም የመታየቱ ነገር መሰረዙን እንደነገሩት ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ‹‹እኔ በግል ሐኪም ልታይ ያልኩት የመንግሥትን ሐኪም በመናቅና የራሴን ከፍ ለማድረግ ሳይሆን ሥጋት ስላለብኝ ነው፤›› ብሏል፡፡ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ከፊትና ከኋላ በተደቀነ መትረየስ ታጅበው የሚንቀሳቀሱት ሥጋት ስላለ እንጂ ጃዋርና በቀለ ያመልጣሉ ተብሎ እንዳልሆነ እንደማሳያ ጠቁሟል፡፡
አቶ ጃዋር እንደገለጸው፣ ነሐሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. መታመሙን ለፍርድ ቤት ማሳወቁንና በዕለቱም ሲመለስ ሕመሙ ፀንቶበት ሲያስመልሰው ማደሩን ተናግሯል፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ‹‹አላመመውም›› የሚል መግለጫ እንደተሰጠበት ጠቁሞ ‹‹አዝናለሁ›› ብሏል፡፡
እዚህ አገር የእሱን ያህል ጠላት ያለው እንደሌለና ቤቱ በፌዴራል ፖሊስ እየተጠበቀ መሆኑን የተናገረው አቶ ጃዋር፣ ጠላቱ መንግሥት ሳይሆን በመንግሥት ውስጥ ያሉ ሰዎች መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡ ‹‹መድኃኒት ብወስድ ልመረዝና ልገደል ስለምችል እኔ በማላውቀው ሐኪም መታከም አልፈልግም፤›› ብሏል፡፡ ምግብ ሲበላ ስለሚያስመልሰው መመገብ ማቆሙን አስታውቆ፣ ‹‹አዕምሮዬን ብስት እንኳን በማላውቀው ሐኪም መነካት አልፈልግም፤›› በማለት የሚናገረው ለሪከርድ እንዲያዝለት መሆኑንም ገልጿል፡፡
አቶ ጃዋር፣ አቶ በቀለ ገርባና አቶ ሐምዛን ጨምሮ ለ14 ተጠርጣሪዎች የቆሙት ጠበቆችም ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡ አቤቱታ፣ ፍርድ ቤቱ ሰጥቶት በነበረው ትዕዛዝ መሠረት ደንበኞቻቸውን ለማግኘት በተለይ አቶ ጃዋርና አቶ በቀለን ጨምሮ አራት ተጠርጣሪዎች ታስረው በሚገኙበት የቀድሞ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በተደጋጋሚ ቢመላለሱም፣ በሚገናኙበት ቦታ ላይ ተገጥሞ የነበረው ካሜራ አለመነሳቱን ተናግረዋል፡፡ ካሜራው እንደተነሳ ከፖሊሶች ተደውሎላቸው ተመልሰው የሄዱ ቢሆንም፣ ተጠርጣሪዎቹን ሊያገናኟቸው እንዳልቻሉ ጠቁመው ‹‹የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አልተከበረም›› ብለዋል፡፡ ፖሊስ ሲጠየቅ ከሥልጣኑ ውጭ መሆኑን እየገለጹና በሌላ አካል ትዕዛዝ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እየተጣሰ ባለበት ሁኔታ ‹‹ተባብረን በቅንነት ካልሠራን በዚህ ሁኔታ ወደፊት መራመድ አንችልም፤›› ብለዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተወካይ ለፍርድ ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፣ እነ አቶ ጃዋር የታሰሩበት ቦታ (ቢሮው) አዲስ ነው፡፡ ካሜራ የተገጠመው ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው መጽሐፍት ያሉበት ቤተ መጽሐፍት (ላይብረሪ) ስላለ እሱን ለመጠበቅ እንጂ፣ ጠበቃንና ተጠርጣሪዎችን ለመቆጣጠር እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ ካሜራ የሌለበት ቦታ አመቻችተው መገናኘታቸውንና ይህንንም በማስረጃ ለማረጋገጥ ከተፈለገ ሲገቡ የፈረሙበትን ሰነድ ማቅረብ እንደሚቻል አክለዋል፡፡
ሕክምናን በሚመለከት ተወካዩ መኮንን እንደተናገሩት፣ ማንኛውም በወንጀል ተጠርጥሮ በእስር ላይ የሚገኝ ዜጋ ሕክምና የሚያገኘው በፌዴራል ፖሊስ ሪፈራል ሐኪም ቤት ነው፡፡ መንግሥት በጀት በጅቶ የእስረኞችን ሰብዓዊ መብት ባከበረ ሁኔታ ሕክምና እንዲያገኙ እያደረገ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆኑት አቶ በቀለ ገርባ ሲሆኑ፣ በሐኪም ቤቱ በተደረገላቸው ሕክምና በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡ መርሕ እንደሚከበርና ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል መሆኑን የጠቆሙት የፌዴራል ፖሊስ ተወካይ መኮንን፣ የተጠርጣሪውን ሰብዓዊ መብት የመጠበቅ ግዴታ እንዳለባቸውና ማንኛውንም ኃላፊነት ተቋሙ እንደሚወስድም ተናግረዋል፡፡ አቶ ጃዋር ጤነኛ እንዲሆን እንደሚፈልጉ ነገር ግን ሁሉንም ነገር የሚያደርጉት መርህን አክብረው መሆኑን አክለዋል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ደግሞ ለፍርድ ቤቱ እንደተናገረው አቶ ጃዋር የሕክምና አቅርቦቱ እያለ ‹‹አልፈልግም›› ብለዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በግል ሐኪም እንዲታከሙ ወይም ይታከሙ የሚል ትዕዛዝ አልሰጠም፡፡ ምክንያቱም የግል ሐኪም ቤትና ሐኪም የሚፈቀድበት የራሱ የሆነ አካሄድ ስላለውና ያንን አልፎ ትዕዛዝ መስጠት ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም ስለሚሆን ተጠያቂነትን ስለሚያመጣ መሆኑን ገልጿል፡፡
አቶ ጃዋር ‹‹እኔ በመረጥኩት ሐኪም ብቻ ካልሆነ አልታከምም›› ያለው የተጠራ አመፅ ስለነበር (በ12/12/12) ያንን ለማቋቋም መሆኑን ዓቃቤ ሕግ ጠቁሞ፣ በቤተሰቦቻቸው (በእህታቸው) ጭምር ‹‹አቶ ጃዋር ተመርዘዋል›› እየተባለ ያልሆነ ነገር በድረ ገጾች እየተናፈሰ ከመሆኑ አንፃር ‹‹እኛም ታመዋል ወይስ አልታመሙም?›› በሚለው እየተጠራጠርን መሆኑን ተናግሯል፡፡ በዓለም አቀፍ አሠራር መርህ መሠረት አንድ ታሳሪ ሲታመም ሐኪም ቤት መቅረብ እንዳለበትና እንዴት በመረጠው ሐኪም መታከም እንዳለበት በተቀመጠው መሥፈርት መሠረት፣ አቶ ጃዋርም የማይታከሙበት ምክንያት እንደሌለ ጠቁሞ፣ መንግሥት ባቀረበላቸው ሐኪም ቤትና ሐኪም እንዲታከሙ እንዲተባበሩ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ጠይቋል፡፡
አቶ ጃዋር በድጋሚ ባቀረበው አቤቱታ በታሰሩበት ቦታ የተገጠመው ካሜራ አለመነሳቱንና ካሜራ በሌለበት ቦታ ከጠበቆች ጋር እንዲገናኙ እንደሚዘጋጅ ቢነገረውም፣ እንዳልተዘጋጀ ተናግሮ የጠበቆቹን አቤቱታ አጠናክሯል፡፡ ሕክምናን በሚመለከት የግል ሕክምና በሚመለከት ለፖሊስም ሆነ ለዓቃቤ ሕግ የተናገረው፣ ‹‹ለሕይወቴ ስለሚያሠጋኝ በግል ሐኪሜ ልታይ›› እንጂ ሌላ ነገር እንደሌለ በድጋሚ አጽንኦ ሰጥቶ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡
የኦኤምኤን ጋዜጠኛ የነበረው ተጠርጣሪ ጋዜጠኛ መለሰ ድሪብሳ ደግሞ ባቀረበው አቤቱታ እንዳስረዳው፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም ትዕዛዙ አልተፈጸመም፡፡ በስልክ እንዲገናኙ የተሰጠው ትዕዛዝም እየተመረጡ ለአንዳንድ እስረኞች እንጂ ‹‹ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል ነው›› የሚለውን መርሕ ባከበረ መልኩ እየተፈጸመ አለመሆኑንም ተናግሯል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሁሉም ተጠርጣሪዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም ተግባራዊ አለመደረጉን ገልጾ፣ አብረዋቸው ታስረው የነበሩና ሁሉንም ነገር በጋራ ሲጠቀሙ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ተመርምረው ቫይረሱ ተገኝቶባቸው ሳለ፣ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ተከብሮ ለእነሱም ምርምራ መደረግ እንዳለበትም አመልክቷል፡፡ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው የታወቁ ተጠርጣሪዎች አሁን ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን የጠቆመው ተጠርጣሪው ጋዜጠኛ መለሰ፣ ያሉበት ቦታ እንዲስተካከልለትና አስፈላጊው እንክብካቤ እንዲደረግላቸውም ጠይቋል፡፡ ምግብ እንደማይገባላቸውም ጠቁሞ፣ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲከበርና ሊደረግላቸው የሚገባ ሁሉ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥ ደጋግሞ አመልክቷል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክርና አቤቱታ ያዳመጠው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት አንድ ተጠርጣሪ ከጠበቆቹ፣ ከሃይማኖት አባቱ፣ ከቤተሰቡ፣ ከጓደኞቹና ከሐኪሙ ጋር የመገናኘት መብት እንዳለው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 21(2 ሥር መደንገጉንና በአንቀጽ 13 (2) ድንጋጌ መሠረት ተፈጻሚ መሆን እንዳለበትም በመጠቆም፣ አቶ ጃዋር በግል ሐኪማቸው ሕክምና እንዲያገኙ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ጠበቆችና ተጠርጣሪዎችም በሕጉ ድንጋጌ መሠረት ሚስጥራቸው ሊጠበቅ በሚችልበት ቦታ እንዲገናኙ እንዲደረግ በመግለጽ፣ ፌዴራል ፖሊስ ይህንን ሳይፈጽም ቢቀርብ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድም አስጠንቅቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ከላይ የተገለጸውን ሒደት ከጨረሰ በኋላ ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን በቀዳሚ ምርመራ መዝገብ ላይ የሚመሰክሩለትን ምስክሮች መስማት ጀምሯል፡፡ በዕለቱ ከሰዓት በኋላ እስከ 11፡30 ሰዓት ድረስ ሁለት የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን በዝግ ችሎት ሰምቶ እንዳጠናቀቀ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ከላይ የተገለጹት ተጠርጣሪዎች ባቀረቧቸው አቤቱታዎች፣ ዓቃቤ ሕግና ፖሊስ የሰጡትን ምላሽ መርምሮ ብይን ለመስጠትና ቀጣይ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ለነገ ነሐሴ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡(ሪፖርተር – ታምሩ ጽጌ)