ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው መመርያ ችግር እንደፈጠረበት የግል ትምህርት ቤቶች ማኅበር አስታወቀ
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በመማር ማስተማሩ ሒደት ላይ ችግር እንዳይፈጠር ትምህርት ሚኒስቴር የግል ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እንዲያደርጉ ያወጣው መመርያ፣ በተቋማቱ ህልውና ላይ ችግር ፈጥሯል ሲል የአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች ማኅበር አስታወቀ፡፡
የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አበባየሁ ደሜ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሚኒስትሩ የተማሪዎች ክፍያን አስመልክቶ ከ50 በመቶ እስከ 75 በመቶ ሆኖ ይህንንም ከወላጅ ኮሚቴ ጋር ተወያይተው እንዲወስኑ ቢልም፣ ከወላጅ ኮሚቴው ጋር የተወሰነውን አንዳንድ ወላጆች እየከፈሉ አለመሆኑንና ይህም ለመምህራን ደመወዝም ሆነ የቤት ኪራይ ለመክፈል ችግር ፈጥሯል፡፡
የኮሮና ቫይረስ በትምህርቱ ዘርፍ ማለትም በትምህርት ቤቶች፣ በወላጆችና በመንግሥት ላይ ያሳደረውን አሉታዊ ጫና የግል ትምህርት ተቋማትን እንዳያዘጋ፣ ተዘዋዋሪ ብድር እንዲሰጥ፣ የቤት ኪራይና የመምህራን ደመወዝ መክፈል እንዲቻል በማለት ከትምህርት ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር በነበራቸው ውይይት ማንሳታቸውን አቶ አበባየሁ ገልጸው፣ ይህ ባልተሟላበት ሁኔታ የተማሪዎች ክፍያ ከ50 እስከ 75 በመቶ እንዲሆን መወሰኑ አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡
አንዳንድ ወላጆች የወላጅ ኮሚቴው ያስቀመጠውን የክፍያ መጠን ባለመቀበልና ‹‹መንግሥት የወሰነው ከ50 እስከ 75 በመቶ ነው›› በማለት 50 በመቶ ብቻ እንደሚከፍሉ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ መቶ በመቶ መክፈል ሲፈልጉ በወረዳዎች በኩል ‹‹ከሕግ ውጪ እየሠራችሁ ነው›› እንደሚባሉም አቶ አበባየሁ ገልጸዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ገረመው ሁሉቃ (ዶ/ር) በበኩላቸው መመርያው ከመውጣቱ በፊት ጥናት መደረጉን፣ በአገሪቱ የተከሰተውን ወረርሽኝ ያሳደረውን አሉታዊ ጫና በትብብር ለመሻገር ሲባልም ሁሉንም በእኩል የሚያይ መመርያ መውጣቱን አስረድተዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር የግል ትምህርት ቤቶች ህልውናቸው ተጠብቆ እንዲቀጥል እንደሚፈልግ፣ የግል ትምህርት ቤቶችን የመጉዳት ፍላጎት ስለሌለውም የሸማቾች መብት ጥበቃ ባለሥልጣን የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ክፍያ እንዳይከፍሉ ብሎ ያስተላለፈው መመርያ ትክክል አለመሆኑን በመገንዘብ ለወላጅ፣ ለትምህርት ቤትና ለመንግሥት የሚጠቅም ውሳኔ መተላለፉን አስታውሰዋል፡፡
የተማሪዎች ወርኃዊ ክፍያ ከ50 በመቶ እስከ 75 በመቶ እንዲከፈል፣ ለዚህም ትምህርት ቤቶች ከወላጅ ኮሚቴ ጋር ተነጋግረው እንዲወስኑና ኃላፊነቱ የወላጅ ኮሚቴው መሆኑን በመግለጽ፣ የተወሰነውን ክፍያ አልከፍልም የሚሉ ወላጆች ካሉ ቅሬታ ማቅረብ እንደሚቻልም ገረመው (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
የትኛውም ወላጅ አቅም ያለውም ቢሆን ከ75 በመቶ በላይ መክፈል እንደማይችል፣ ትምህርት ቤቱን እረዳለሁ የሚል ወላጅ በስጦታም ሆነ በሌላ መልክ ገንዘብ መስጠት እንደሚችል አክለዋል፡፡
ወላጆች በወላጅ ኮሚቴ የተወሰነውን የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው፣ መመርያው ወላጆች እንዳይከፍሉ ሳይሆን ተረዳድቶ ከችግር መውጣት ላይ ያነጣጠረ ነው ብለዋል፡፡
ተዘዋዋሪ ብድርን አስመልክቶ ትምህርት ሚኒስቴርና የግል ትምህርት ቤቶች በነበራቸው ውይይት መነሳቱን ያስታወሱት ገረመው (ዶ/ር)፣ ብድር የመስጠት ኃላፊነት የባንክ ቢሆንም ትምህርት ቤቶች ለሚኒስቴሩ በሚያቀርቡት ደብዳቤ መሠረት ትብብር እንደሚደረግ፣ ይህንንም በውይይታቸው ወቅት እንደተናገሩ ገልጸዋል፡፡
እስካሁን ድረስ የኦሮሚያ ክልል የግል ትምህርት ቤቶች ማኅበር ብቻ ብድር እንዲመቻችለት ትምህርት ሚኒስቴር ድጋፍ እንዲያደርግለት ደብዳቤ ማስገባቱን፣ ከዚህ ባለፈ የአዲስ አበባም ሆነ የሌሎች ክልሎች ማኅበራት ጥያቄ እንዳላቀረቡ ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤት አሠሪዎች ማኅበር አልከፍልም የሚሉ ወላጆች ስለመኖራቸው፣ ተዘዋዋሪ ብድርም ሆነ ሌሎች ችግሮች ገጥመውኛል ብሎ ቅሬታ እንዳላቀረበ ገረመው ገልጸው (ዶ/ር)፣ ሚኒስቴሩ ቅሬታውን ተቀብሎ ችግሮችን በጋራ እንደሚፈታ ተናግረዋል፡፡
የግል ትምህርት ቤቶች ችግር ከገጠማቸው አብረው ለመፍታት ዝግጁ እንደሆኑ፣ ቢሮዋቸውም ሁሌም ክፍት እንደሆነና ጉዳዩን የሚመሩት ራሳቸው በመሆናቸው ችግሮችን አብረው ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውንም ሚኒስትር ዴኤታ አስታውቀዋል፡፡
ትምህርት ቤቶችም ለተማሪዎቻቸው በቴሌግራምና በሌሎች ቻናሎች፣ ከዚሁ ጎን ለጎንም ትምህርት በሬዲዮና ቴሌቪዥን ተጠቅመው ተማሪዎቻቸውን የማስተማር ግዴታ የተጣለባቸው ሲሆን፣ ይህንን ሳይፈጽሙ ወላጆችን ክፈሉ ማለት እንደማይቻል የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ አበበ ቸርነት አሳስበዋል፡፡
ቢሮው ከትምህርት ቢሮ የተላለፈውን መመርያ እንደሚያስፈጽም፣ ትምህርት ቤቶችም በመመርያው መሠረት መሥራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡ #ሪፖርተር