Connect with us

መኖሪያ-ቤታቸው ውስጥ ሱፐር-ማርኬት ለከፈቱ ጨካኞች

መኖሪያ-ቤታቸው ውስጥ ሱፐር-ማርኬት ለከፈቱ ጨካኞች
Photo: Social media

አስገራሚ

መኖሪያ-ቤታቸው ውስጥ ሱፐር-ማርኬት ለከፈቱ ጨካኞች

መኖሪያ-ቤታቸው ውስጥ ሱፐር-ማርኬት ለከፈቱ ጨካኞች | አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ

በባለፈው የአዲስ አበባ ከንቲባ የሆኑት ኢንጂነር ታከለ ኡማ ‹‹የቤት አከራዮች አንጀት ለተከራዮቻቸው እንዲራራ የሚያሳስብ መልዕክት ከማስተላለፋቸው ጋር ተያይዞ፣ እኔም ‹‹የዚህ እድል ተጠቃሚ እሆናለሁ›› በሚል እምነት ኮንዶሚንየም ያከራየኝ ሰውዬ የሚደውልበትን ቀን በመጠባበቅ ላይ ሳለሁ አከራዬ ዛሬ ደወለ፡፡

‹‹ሄሌ ጋሽ ጌታቸው›› አልኩት ሊቀንስልኝ ይሆን በነጻ ሊያኖረኝ በማለት እያሰብኩ፡፡
‹‹እንዴት ነህ?››
‹‹እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ››
‹‹የደወልኩልህ ከንቲባው ያስተላለፉትን መልዕክት ሰምቼ ነው››
‹‹ምን አሉ›› አልኩት እንዳልሰማ ሰው ሆኜ
‹‹ምን እንዳሉማ ሰምተኻል! ይልቅ ያለንበት ጊዜ ዛሬ እንሙት ነገ የማይታወቅበት ስለሆነ ይሄ ኮሮና የሚባል በሽታ እስኪያልፍ ድረስ ከዚህ ወር ጀምሮ የቤት ኪራይ ክፍያ ቅድሚያ እንዲትከፍለኝ እፈልጋለሁ›› ብሎኝ አረፈ፡፡ ይሄንንም ስሰማ በጣም ተበሳጭቼ ‹‹እንዲህ አይነት ጭካኔ በከንቲባውም ሆነ በባላደራው ዘንድ ተቀባይነት የለውም›› አልኩት፡፡
እሱ ግን አልሰማኝም፡፡

‹‹የራሴ እና የቤተሰቤ አንሶኝ ያ ሰውየ የቤት ኪራይ ሳይከፍለኝ ይታመምብኝ ይሆን? እያልኩ መጨነቅ ስለማልፈልግ ኪራዩን ቀድመህ በአካውንቴ እንዲታስገባ ብየኻለሁ›› ብሎኝ ስልኩን ዘጋው፡፡

በዚህን ጊዜም ከንዴት ባለፈ የትኩሳት ስሜት ስለተሰማኝ አየር ልቀበል ወደ ደጅ ስወጣ ግራውንድ ላይ ዳንኤል ገመድ እየዘለለ አየሁት፡፡

እናም ኮሪደር ላይ ሆኜ ‹‹ሰላም ነው ዳኒ›› ስለው ኮሮና በመተያየት ይተላለፍ ይመስል እንደ መነጽር ግንባሩ ላይ ያደረገውን N-95 ማስኩን አውርዶ ፊቱን ከሸፈነ በኋላ ‹‹ሰላም ነው›› የሚል መልስ ሰጥቶኝ መዝለል ሲጀምር ወደ ላይ ካለው ቁመት ይልቅ ወደ ጎን ያለው ስፋት የሚረዝመው ወፍራም ሰውነቱ በውሃ የተሞላ ይመስል ይናጥ ጀመር፡፡

ዳኒ እኛ ብሎክ ላይ ባለሶስት መኝታ ኮንዶሚንየም ገዝቶ የሚኖር ወጣት ኮንትራክተር ሲሆን ከቤት መኪና በተጨማሪ ለጭነት የሚገለገልባት አንድ ፒክአፕ አለችው፡፡

ከሰሞኑን ታዲያ ከበሽታ በተጨማሪ ድርቅ ይከሰታል የሚል ስጋት አለው መሰል ከሱፐር ማርኬት ውስጥ ያየውን ቁሳቁስ ሁሉ በጅምላ እየገዛ በዚች መኪናው ሲያመላልስ ነበር፡፡ በመሆኑም የሚኖርበትን ቤት ‹‹ሸዋ ሱፐር ማርኬት›› ለማድረግ የቀረው ነገር ንግድ ፍቃድ ማውጣት ብቻ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከምግብ ቁሳቁስ ባለፈ ደግሞ ‹‹መኖሪያ ቤቱ ውስጥ ያሉት የህክምና ቁሳቁሶች ጤና ጣቢያ ያስንቃል›› ከሚል ንግግር ጋር እነ አሜሪካ ለኮሮና ታማሚዎች የሚሠጧቸውን መድሃኒቶች አዘጋጅቶ… የሚሸጥ ቬንትሌተር የሚያገኝበትን እና የሚታመምበትን ቀን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል›› እያለ የቅርብ ጎረቤቱ ሲያወራ ሰምቻለሁ፡፡

በበኩሌ ግን ዳኒ ከእሱና ከሚስቱ ውጭ ያለው የቤተሰብ አባል አንድ ብላቴና ቢሆንም የከዘነው ጤፍና የምግብ ቁሳቁስ ግን የብሎካችንን ነዋሪ ለወራት ማብላት እንደሚችል ካየሁት ተነስቼ መናገር እችላለሁ፡፡

በባለፈው ለምሳሌ በካርቶን በካርቶን እያደረገ ያስገባው የሊፕቶሚልና የኒዶ ወተት ብዛት ኤክስፓየርድ ካላደረገበት በቀር ለተወለደው ልጁ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ለሚወልዳቸውም ጭምር እንደሚበቃው አልጠራጠርም፡፡

የሆነ ቀን ደግሞ አንድ መኪና ዳይፐር ጭኖ ሲመጣ ከተመለከቱ የብሎካችን ነዋሪዎች መሃከል አንዳንዶቹ ‹‹በአገራችን የተከሰተው በሽታ ኮሮና ነው ወይስ አተት?›› በማለት ሲጠይቁ፣ የተወሰኑት ደግሞ ‹‹መቼም ይሄን ሁሉ ዳይፐር የገዛው ለልጁ ብቻ ሳይሆን ለእራሱም ጭምር መሆን አለበት›› እያሉ ሲያንሾካሹኩበት ነበር፡፡ ከእኛ ቀጥሎ ካለው ብሎክ የመጠጥ መሸጫ ሱቅ ያላት ወ/ሪት አስካች ደግሞ በግሮሰሪዋ ውስጥ ያለውን ውስኪና ወይን ልቅምቅም አድርጎ ሲገዛት ‹‹ኮማሪ’ስ ትፈልጋለኽ ወይ? ብላ ስትጠይቀው ሰምቻለሁ›› በማለት የኮንዶሚንየማችን ጥበቃ አጫውቶኛል፡፡

የሆነው ሆኖ ግን
የጎረቤቴና የአከራዬ ገድል-
በወግ ተጀምሮ በግጥም ሲጠቃለል
አንዳንድ ሰው አለ- አንዳንድ ግለሰብ
‹‹ሞት መጣልህ›› ሲባል-
ንስሐ እንደመግባት- የሚያከማች ቀለብ
ቤቱን አትረፍርፎ- ወገኑን የሚያስርብ
እንዲንረዳዳ፣ እንዲንተጋገዝ
የሚያስገድድ መቅሰፍት- ሕዋውን ሲመርዝ፣
እሱ ብቻ ሊድን-
እሱ ብቻ ሊተርፍ- ብቻውን ሊበላ
ለካች አምና ቀለብ
የእለት ጉርስ ሰብስቦ- ቤቱን የሚሞላ፤
እናም ወዳጄ ሆይ…
በአልጠግብ ባይነት- በመስገብገብ ጣጣ
በሕመም ላይ እራብ
ያንዣበበበት ሕዝብ- የሚጎርሰው ሲያጣ፣
እንዳትቀየው…
አጣናውን ይዞ- ሊዘርፍህ ቢመጣ፡፡

Click to comment

More in አስገራሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top