Connect with us

ቦምብ በመወርወር የሽብር ወንጀል የተከሰሱ አምስት ተከሳሾች ጥፋተኛ ተባሉ

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተካሄደ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ቦምብ በመወርወር የሽብር ወንጀል የተከሰሱ አምስት ተከሳሾች ጥፋተኛ ተባሉ
Photo: Addis Standard

ወንጀል ነክ

ቦምብ በመወርወር የሽብር ወንጀል የተከሰሱ አምስት ተከሳሾች ጥፋተኛ ተባሉ

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተካሄደ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ቦምብ በመወርወር የሽብር ወንጀል የተከሰሱ አምስት ተከሳሾች ጥፋተኛ ተባሉ

ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተካሄደ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ቦምብ በመወርወር የሽብር ወንጀል የተከሰሱ አምስት ተከሳሾች የጥፋተኝነት ፍርድ ተፈረደባቸው።

ተከሳሾቹ ጌቱ ቶሎሳ፣ ብርሃኑ ጃፋር፣ ጥላሁን ጌታቸው፣ ደሳለኝ ተስፋዬ እና ባህሩ ቶላ ሲሆኑ የጥፋተኝነት ፍርዱን የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የወንጀል ችሎት ነው ያስተላለፈው።

የዐቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመላክተው ተከሳሾቹ ወንጀሉን የፈጸሙት ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አባባ መስቀል አደባባይ ከረፋዱ አራት ሰአት ላይ በ40 ሜትር ርቀት አካባቢ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ቦንብ በመወርወር ነው።

ተከሳሾቹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1ሀ እንዲሁም አንቀጽ 38 እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ፤ በሃገሪቱ ያለውን ለውጥ ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመራ መንግስት መኖር የለበትም በሚል የራሳቸውን አላማ ለማራመድ በማሰብ መንቀሳቀሳቸውን ዐቃቤ ህግ በክሱ አመላክቷል።

በዚህም ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያሉ ተከሳሾች ከሱሉሉታ ከተማ መነሻቸውን በማድረግ በስልክ በመደዋወልና በአካል በመገናኘት በድጋፍ ሰልፉ ላይ እንዴት ቦምብ መወርወር እንዳለባቸው ሲዘጋጁ ቆይተዋልም ነው ያለው ዐቃቤ ህግ፡፡

በዚህ መልኩ በ1ኛ ተከሳሽ ቤት ቡራዩ በማደር 2ኛ ተከሳሽ በሚያሽከረክረው ተሽከርካሪ 2ኛ ተከሳሽ ያዘጋጀውን ኤፍ1 ቦምብ በመያዝ ከ3 እስከ 5ኛ ያሉ ተከሳሾች ጋር ከፒያሳ ወደ ቴድሮስ አደባባይ በመምጣትና የድጋፍ ቲሸርት ልብስ ገዝተው በመልበስ ተመሳስለው መግባታቸው ተጠቅሷል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር ካደረጉ በኋላ ተከሳሾቹ በ40 ሜትር ርቀት ላይ ቦምብ የወረወሩ ሲሆን በዚህም የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ከ163 በላይ ሰዎች ላይ ደግሞ ከከባድ እስከ ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውም ዐቃቤ ህግ አስረድቷል፡፡

የዐቃቤ ህግን የሰነድና የሰው ምስክር እንዲሁም የተከሳሾችን መከላከያ የመረመረው ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹን በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ብሏቸዋል።

በተከሳሾቹ ላይ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠትም ለጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

እስከ ጥቅምት 17 ድረስ ግን የቅጣት ማቅለያዎችን ማቅረብ እንደሚቻል ትዕዛዝ ሰጥቷል።(FBC)

Click to comment

More in ወንጀል ነክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top