Connect with us

የካርቱምና ካይሮ አዲሱ መላ…

የካርቱምና ካይሮ አዲሱ መላ...
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የካርቱምና ካይሮ አዲሱ መላ…

የካርቱምና ካይሮ አዲሱ መላ…

(እስክንድር ከበደ)   

የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ የግብጽና  የኢትዮጵያ አቻዎቻቸው በታላቁ የህዳሴ ግድብ አሞላልና አስተዳደር ዙሪያ  በቪዲዮ ኮንፈረንስ በዝግ  እንምክር  በማለት  መጠየቃቸውን ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል፡፡የግብጽ ሚዲያዎች አራግበውታል፡፡  የሱዳን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣው መግለጫ  በሦስቱ ሀገራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች በ10 ቀናት በዝግ  እንዲያካሂዱ የሚጠይቅ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሱዳን የምታመጣው አጀንዳ የግብጽ መሆኑ ተደጋግሞ ይታያል፡፡ 

እ.ኤ.አ በ2015 ሦሰቱ ሀገራት የተፈራረሙት የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት  በመግቢያው የግብጽ፣የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ተሸጋሪ የውሃ ሀብታቸውን እና የናይል(አባይ)  ወንዝ ለህልውናቸውና ለህዝባቸው ልማት  ጉልህ ምንጭ መሆኑን  መግባባት ላይ መደረሳቸውን  ይገልጻል፡፡

ግብጽ፣ኢትዮጵያና ሱዳን (የሀገራቱ አደራደር ምናልባት የስማቸው ቅደም ተከተል በእንግሊዘኛ  ፊደል የተከተለ ይሆናል፡፡) ሦስቱ ሀገራት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ  ለመከተል ቁርጠኛ የሆኑባቸውን መርሆዎች በ10 አንቀጾች ያትታል፡፡

በአንቀጽ አንድ የትብብር መርሆዎቹ(Principle of Cooperation) ስር ሁለት ዋና ነጥቦች ይዟል፡፡ አንደኛው ሀገራቱ በጋራ መግባባት ፣ የጋራ ጥቅም ፣ በቅን መንፈስ፣ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበትና በዓለም አቀፍ የህግ መርሆዎች ላይ የተመሰረተ ትብብር ለማድረግ መስማማታቸውን ይገልጻል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የላይኛውንና የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት  ለተለያዩ  የውሃ ፍላጎት በመግባባት  የመተባበርን እንደ መርሆ ያስቀምጣል፡፡

የመርሆ መግለጫ  ስምምነት ሰነዱ በሁለተኛው አንቀጽ   ”የልማት፣የቀጠና ትስስርና ዘላቂነት ”  በሚል በሚያትተው አንቀጹ፤ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ አላማ ለሀይል ማመንጫ ፣ለኢኮኖሚ ልማት አስተዋጽኦ፣የድንበር ተሸጋሪ ትብብር ለማስፋፋት እና  አስተማማኝ  የንጹህ ኢነርጂ  አቅርቦት አማካኝነት አህጉራዊ ትስስር ማጠናከር እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡

ይህ ሰነድ ሦስቱ ሀገራት በግዛታቸው ውስጥ  የውሀ ሀብቶችን  ፍትሀዊና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ  መጠቀም እንዳለባቸውና  በጥቁር አባይ(ዋናው ናይል) አጠቃቀማቸው ጉልህ ጉዳት ማድረስ እንደሌለባቸው  በርካታ ንኡሳን ቴክኒካዊ ነጥቦችን ተዘርዝረው ይገኛሉ፡፡

የግድቡን የደህንነት መርሆ የሚጠቅሰው  በአንቀጽ  8  የመርሆዎች  ስምምነት መግለጫው፤  ስምምነቱ እስከተፈረመበት ድረስ  ሦስቱ ሀገራት  የአለምአቀፉ   የባለሞያዎች ፓናል ያቀረበውን ምክረ ሀሳብን ኢትዮጵያ  ተግባራዊ  በማድረግ ረገድ ማድነቃቸውን አስቀምጧል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ኢትዮጵያ  የዓለም አቀፉ የባለሞያዎች ቡድን በሪፖርቱ  ስለ ግድቡ ደህንነትና ጥንቃቄ  ያቀረባቸውን  ምክረ ሀሳቦች  ኢትዮጵያ  በተሟላ መልኩ  በቀና መንፈስ  ተግባራዊ እንድታደርግ ይመክራል፡፡

ሦስቱ ሀገራት  ልኡላዊነት እና የድንበር ነጻነታቸውን ጠብቀው  በልኡላዊ አቻ ሀገርነት ፣ግዛታቸው በሚያስጠብቅ ፣በጋራ ጥቅም እና ቀና መንፈስ በተገቢ መልኩ ውሃቸውን መጠቀም እና ለወንዙ በቂ ጥበቃ ማድረግን እንዳለባቸው ተግባብተዋል፡፡

በመርሆዎች የስምምነት መግለጫ ሰነዱ የመጨረሻ አንቀጽ 10  ፤   ሦስቱ ሀገራት በስምምነቱ ትርጉም እና አተገባበር ላይ የሚነሱ ውዝግቦችን በመግባባትና በቀና መንፈስ   በሰላማዊ መንገድ እንደሚፈቱ  ያስቀምጣል፡፡  በመመካከርና መግባባት  መፍታት ካልቻሉ ግን በጋራ  ለመሪዎች  ለውሳኔ እንደሚያቀርቡ ተስማምተዋል;፡፡ሦስቱ ሀገራት ውዝግባቸውን በመመካከር ወይም በድርድር መፍታት ካልቻሉ ፤   በሽምግልና   ወይም  በግልግል ጉዳዩ እንዲታይ   አልያም ለሦስቱ  ለሀገራቱ ርእሰ በሔሮች ወይም  ለሀገራቱ ርእሰ መስተዳደሮች  በጋራ ማቅረብ እንደሚችሉ  ይገልጻል፡፡

በኮንጎ ኪንሻሳ  የተካሄደው  ድርድር  ያለውጤት ከተበተነ ተከትሎ  ሱዳንና ግብጽ የተለያዩና የተለመዱ የሚዲያ ዘመቻዎችን በኢትዮጵያ ላይ ሲያካሂዱ ነበር፡፡  ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ማአቀፍ  ውስጥ የድርድሩ  ውዝግቦች  መፈታት እንደሚችሉና  ለአህጉራዊ  መፍትሄዎች ቁርጠኛ መሆኗን  ስትገልጽ ቆይታለች፡፡  

ኢትዮጵያ ሦስቱ ሀገራት   እ.ኤ.አ በ2015 የተፈራረሙት የመርሆዎች  መግለጫ  መነሻ ድርድሮች መካሄድ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥታ ትከራከራለች፡፡ በግብጽና በሱዳን በኩል በተለያዩ ጊዜያት አዳዲስ አጀንዳዎች በማቅረብ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ብዙ ለፍተዋል፡፡

የሱዳን የሚኒስትሮች ምክር ቤት  መግለጫ  በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚካሄደው  የሦስቱ ሀገራት ድርድር  አልተሳካም ብሎ የሚደመድም ሲሆን፤በሶስቱ ሀገራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች በቪዲዮ ኮንፈረንስ በዝግ እንዲካሄድ ይጠይቃል፡፡  የመግለጫው  የሦስቱ ሀገራት  ጠቅላይ ሚኒስትሮች ድርድሩን  በ10 ቀናት  ውስጥ መካሄድ አለበት ብሎ ፤ የዚህ ጥያቄን መነሻ ደግሞ ሀገራቱ  እ.ኤ.አ  በ2015 የተፈራረሙትን የመርሆዎች መግለጫ እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡  የተሰጠው ጊዜ ቁርጥ ያለበት ምክንያት ይኖረዋል፡፡ ከግድቡ ሙሌት በፊት አስገዳጅ የሚባል ስምምነት እንዲፈረም ጫና ለመፍጠር መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ  መጋቢት 28 /2013 ባወጣችው መግለጫ ፤ ኢትዮጵያ ፍትሐዊና ምክንያታዊ የሆነ የአሁን የወደፊት ውሃ የመጠቀም መብቷን  የሚያቅብ  ማናቸውም  አይነት ስምምነት አትፈርምም ”ብላለች፡፡ ኢትዮጵያ በዚሁ መግለጫ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የሚካሄደው ድርድር እንዲቀጥል ፍላጎና ቁርጠኛ መሆኗን ገልጻለች፡፡

የሱዳን  አዲስ ጥያቄ  በደብዳቤ  ለኢትዮጵያና ለግብጽ የቀረበ  ሲሆን  ግብጽም  የምትደግፈው ግልጽ ነው፡፡ የዚህ ጥያቄ መነሻ ችግሩን በመሪዎች ደረጃ መፍታት ይቻላል ከሚል መነሻ አለመሆንን የሁለቱ ሀገራት የሰሞኑን አካሄድ  አይቶ መገመት አይከብድም፡፡  ሱዳን ”በዝግ መሪዎቻችን ይመካከሩ” ብላ ሀሳብ ስታቀርብ ፤ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ የድርድሩን ሂደትና አለመሳካቱን የሚያትት ደብዳቤ  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ ጽፋለች፡፡

የግብጽና የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ካይሮ በተገናኙ ወቅት ፤የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቫሮቭ  የሀገራቸውን አቋም አስታውቀዋል፡፡ በተ.መ.ድ የጸጥታው ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣን ከላቸው አምስቱ ሀገራት አንዷ የሆነችው  ሩሲያ አቋም ግብጽ እንዳልወደደችው ግልጽ ነው፡፡ ሩሲያ   የሦስቱ ሀገራት ጥቅምን  በሚያስከብር መልኩ እንዲደራደሩ ብሎም  የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካ እንዲፈታ ሀገራቸው ያላትን አቋም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ ታዲያ የሱዳን አዲሱ በዝግ እንምከር ጥያቄ የ2015 የመርሆ መግለጫ ሰነድ ውጪ የድርድሩን አቅጣጫ የማሳት መላ መሆኑን ኢትዮጵያ አውቃ ወጥመዳቸውን  በብልሀት ማለፍ ይጠበቅባታል፡፡

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top