በሀገራችን በትዳር አለም ብዙ መቆየት ለታላቅ ክብር ያበቃል። 25ኛ አመት ፣50ኛ አመት እያሉ በጋብቻ የቆዩባቸውን አመታት የሚያከብሩ ጥቂቶች ቢሆኑም ከእነሱ ግን ብዙ መማር ይቻላል።በአንጻሩ ደግሞ እንደተጋቡ ተፋቱ የሚባሉ ትዳሮችንም እናያለን፤ እንሰማለን።
ጃፓናዊቷ ሞዴሊስት ካቶ ሳሪ የቅንጦት ሕይወት በመምራት ትታወቃለች። በጣም ውድ የፋሽን ልብሶችንና ጌጣጌጦችን በመጠቀምም ትታወቃለች። ይህ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቀው የጃፓናዊቷን ኑሮ በቅርቡ የመሰረተችው ትዳር እንዲፈርስ ምክንያት ሆኖባታል ይለናል የኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ መረጃ።
ከአንድ ሰባት እድሜ ያልዘለለው የሞዴሊስቷ እና ስሙ ያልተጠቀሰው ባለቤቷ ትዳር ፣ ለፍሬም ሳይበቃ ብቻ አይደለም የጫጉላ ወገንም በቅጡ ሳያይ በአጭሩ ለምን ተቀጨ ታዲያ። ለእዚህ ምክንያት የሆነው ሞዴሊስቷ የሚያስፈልጋት ወጪ ከፍተኛ መሆኑ ነው።
የ29 አመቷ ካቶ ሳሪ ባለቤቷ ወጪዋን እንድትቀንስ በተደጋጋሚ ያሳስባታል። ባለቤቷ የሚያስፈልጋት ወጪ ያን ያህል የተጋነነ እንደማይሆን አስቀድሞ ይገመት እንደነበር መረጃው ጠቅሶ፤ ወጪዋ ስራውን አደጋ ውስጥ እየጣለ መምጣቱን ሲረዳ ግን ማሳሰቢያውን ማስተላለፉን ይጠቁማል።
ስሙ ያልተጠቀሰው ባለቤቷ ውድ ባለቤቱን ካቶ ሳሪን ማግኘት የጀመረው በግንቦት ወር 2019 ነበር። ከዚያ ጊዜ አንስቶ ባሉት ሶስት ወራት ተኩል ጊዜያት ብቻ ካቶ ሳሪ አንድ ቢሊዮን የን ወይም ከ9 ሚሊየን ዶላር በላይ ለተለያዩ የሞዴል ልብሶችና ለመሳሰሉት አውጥታለች።ይህ ሁሉ ሆኖም ባለቤቷ ትዳር መመስረቱን አልጠላውም፤ጋብቻው ይፈጸማል።ጋብቻው በተፈጸመ የመጀመሪያው ሳምንትም ባለቤቱ ወጪዋን እንድትቀንስ ቢያሳስባትም ይህ ማሳሰቢያ ግን ካቶ ሳሪን አልተመቻትም ፤እንዲያውም ጋብቻው እንዲፈርስ ትጠይቃለች።
‹‹እሱን የማግባቴ ፋይዳው ምኑ ላይ ነው›› ያለችው ካቶ ሳሪ፣አሳስቶ አስፈርሞኛል ስትልም ትገልጻለች። ፍላጎቷን ከሚገድብ መናጢ ድሃ ጋርም በትዳር ለመቆየት እንደማትፈልግ በማረጋገጥ ፍቺውን ራሷ ጠይቃለች።
ለአድናቂዎቿ ስትናገርም ግለሰቡን ያገባችው ለገንዘቡ ስትል መሆኑን ጠቅሳ፤ የባለቤቷን ሀብት ውድ መኪናዎችን፣ ጌጣጌጦችን፣ ልብሶችን ፣ካልገዛችበት ለእሷ ምንም ፋይዳ እንደሌለው ትገልጻለች። ሴቶች በእርግዝናና በልጅ ማሳደግ ብዙ ጊዜያቸውን እንደሚያ ሳልፉም ጠቅሳ፤ ወንዶች ለቤተሰቡ በቂ ገንዘብ ለማግኘት መድከም እንዳለባቸውም ትናገራለች። ባለቤቷ ይህን የሚያደርግ አይነት ባለመሆኑም አዝናለች።
የሞዴሊስቷ ውሳኔ ብዙዎችን አነጋግሯል። አንድ አስተያየት ሰጪ ‹‹በርካታ መጥፎ ባህሪ ያላቸው ሴቶች እንዳሉ ጠቅሶ፤ የሞዴሊስቷ ግን የተለየ ነው ሲል በዩቲዩብ ገልጾታል። ይህች ሴት በጣም ታሳዝናለች ያለው ሌላ አስተያየት ሰጪ ግልጽ የሆነውን ሕይወት አታውቀውም ሲል ጽፏል።
ከየአቅጣጫው የሚሰጡ አስተያየቶች ሞዴሊስቷን አላሸበሯትም፤ ይልቁኑም ጠንካራ እንድትሆን አድርገዋታል።ከታላላቅ ሰዎች ጋር በመሆን ፎቶ እየተነሳች በኢንስታግራም መልቀቋን ተያይዛዋለች። በዚህም የከሸፈውን ትዳሯን እየረ ሳችው መጥታለች ይላል መረጃው።