የዓለም ኹሉ ቅርስ የኾነው በዓለ ጥምቀት የማንም ቅርስ እንዳይኾን የማድረግ ዘመቻ!?
- በዓሉ እንዳይከበር ከማስታጎል ጀምሮ የማክበሪያ ቦታዎችን መንጠቅ እየተለመደ መጥቷል፤
- ከአዲስ አባባ 78 የበዓሉ ማክበሪያዎች፣ ይዞታቸው በሕግ የተረጋገጠላቸው 38ቱ ብቻ ናቸው፤
- ለቀሪዎቹ 40 ማክበሪያዎች ካርታ እንዲሰጣት ቤተ ክርስቲያን ብትጠይቅም ምላሽ አላገኘችም፤
- በያዝነው ዓመት ብቻ፣ በልዩ ልዩ ክፍላተ ከተማ ከ6 በላይ የማክበሪያ ይዞታዎች ተነጥቀዋል፤
- ከ40 በላይ ገዳማት እና አድባራት የዘንድሮውን በዓለ ጥምቀት የሚያከብሩበት ቦታ የላቸውም፤
- በልማት እና በስፖርት ማዘውተሪያ ሰበብ፣ መንጠቅ እና ምትክ አለመስጠት ተባብሶ ቀጥሏል፤
- በማስተር ፕላኑ ታሳቢ ሳይደረጉ መንገድ የወጣባቸውና ጠፍ የኾኑ አብሕርተ ምጥምቃት አሉ፤
- መንግሥት ዝንፈቱን በጊዜ አርሞ ካላስተካከለ፣ የቅርሱን ደረጃ እና ህልውና አስጊ ያደርገዋል፤
- የቱሪስት መስሕብ የኾነውን ሳይጠብቁ ተመራጭ እና ቀዳሚ መዳረሻ መኾን እንደምን ይቻላል?
- ክብርት ም/ል ከንቲባዋ፣የጃንሜዳን ጽዳት በማስጀመር ላሳዩት ቁርጠኝነት ምስጋና እናቀርባለን፤
- ጃንሜዳን ጨምሮ የኹሉም ባሕረ ጥምቀት ይዞታዎቻችን ባለቤትነት በሕጋዊ ካርታ ይረጋገጥ፤
- ይዞታዎቹን መዳፈር የዓለም ቅርስ በዓለ ጥምቀት የማንም ቅርስ እንዳይኾን ማድረግ ነው!
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዐደባባይ ከምታከብራቸው ዐበይት በዓላት አንዱ፣ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት በዓል ነው። በየዓመቱ ጥር 10 ቀን ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው ወጥተው፣ በካህናት ሃሌታ እና በምእመናን እልልታ ታጅበው ወደ ባሕረ ጥምቀት ወርደው በጊዜያዊነት በዚያው ዓርፈው፣ ደማቅ እና ማራኪ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት የሚፈጸምበት፣ ልዩ እና ተናፋቂ ማኅበራዊ መስተጋብሮች የሚከናወኑበት ጥንታዊ እና ታሪካዊ በዓል ነው – በዓለ ጥምቀት፡፡
ከ1500 ዓመታት በላይ ሳይቋረጥ የተከበረው እና በመከበር ላይ ያለው፣ በአገራዊ ዕሴትነቱ እና የውጪ ጉብኝዎችን በመሳብ ወደር የማይገኝለት ሕብራዊው የጥምቀት – ከተራ ሥነ በዓል፣ የኢትዮጵያውያንና የመላው ዓለም የማይዳሰስ ቅርስ በመኾን፣ በ2011 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት፣ የሰው ልጆች ኹሉ መንፈሳዊ ሀብት ኾኖ ተመዝግቧል።
የጥምቀት በዓል፣ ለበዓሉ ማክበርያነት ተብሎ በፈለገ ዮርዳኖስ አምሳል በተከተረው ባሕረ ጥምቀት ዙሪያ መከበር የሚገባው ሲኾን፣ በቱሪስት መስብሕነቱ በምጣኔ ሀብቱ ዘርፍ ለሀገር የጎላ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ እና ሀገራዊ ዕሴት እና ቅርስ ነው፡፡ ይኹን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ፣ ይህ ታላቅ የዐደባባይ በዓላችን፣ ከባሕረ ጥምቀት ይዞታ እና ዝግጅት ጋራ በተያያዘ ዕንቅፋት እየገጠመው ነው፡፡ ይህም፣ የጥምቀትን ሥነ በዓል ከነሙሉ መንፈሱ እና ክብሩ ጠብቆ ለትውልድ ለማዝለቅ አዳጋች እያደረገው መጥቷል።
በዓለ ጥምቀት፣ በዩኔስኮ የማይዳሰስ ዓለም አቀፍ ቅርስ ኾኖ ከተመዘገበ በኋላ፣ ለአከባበሩ ድምቀት ድርሻ ያላቸው አካላት፣ ካለፈው በተሻለ ሚናቸውን እየተወጡ ጥበቃ እና ክብካቤ ያደርጋሉ ተብሎ ነበር የተጠበቀው። በተፃራሪው፣ በዓሉ እንዳይከበር ከማስተጓጎል ጀምሮ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎችን እስከ መንጠቅ የደረሰ ድፍረት እየተለመደ መጥቷል። በክልል ከተሞች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎች፣ ቀበሌዎች፣ ጎጦች እና በአዲስ አበባ ከተማ ጭምር፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ አንዳንድ ባለሥልጣናት ሳይቀሩ፣ የማስተጓጎል ድርጊቱ አባሪ እና ተባባሪ እየኾኑ ይገኛሉ።
በዚኽ ረገድ፣ በአገራችን የጥምቀት በዓል በብሔራዊ ደረጃ የሚከበርበት የጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት፣ በይዞታ ባለቤትነት ያለበትን ችግር በአስረጅነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዓለ ጥምቀትን በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የአከባበር ናሙና ከተወሰደባቸው ቦታዎች ውስጥ አንዱ ነው – ጃንሜዳ። ከ11 በላይ ታቦታት ማደሪያ የኾነው የጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት፣ በዓሉ በታላቅ ድምቀት የሚከበርበት፣ ልዩ ልዩ ኢትዮጵያዊ የባህል ዕሴቶች ተሰናስነው የሚገለጡበት ታሪካዊ ቦታ ነው። ይኹንና፣ ቀደም ሲል የተረጋገጠው የቤተ ክርስቲያናችን የባለቤትነት ካርታ ተነጥቆ ለሌላ አካል ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡ ይልቁንም፣ ገጽታውን የሚያጠፋ የገበያ መዋያ ኾኖ ክብሩን ሲያጣና የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ለጉዳዩ የሰጠውን አነስተኛ ግምት ስንመለከት፣ “በእጅ ያለ ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል” ያሰኛል።
በተለይ፣ የአዲስ አበባ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የበዓሉን ማክበሪያ ቦታዎች ከማስጠበቅ ጀምሮ፣ በዓለም አቀፍ ቅርሱ ቀጣይ አያያዝ እና ክብካቤ ዙሪያ የሚጠበቅባቸውን ሓላፊነት በባለቤትነት መንፈስ ሲወጡ አይስተዋሉም። ሌሎች መንግሥታዊ አካላትም፣ በዓሉ እና የበዓሉ ማክበሪያ ቦታዎች ያላቸውን ሃይማኖታዊ ትስስር እና ክብር በውል ከመረዳት አኳያ ባለባቸው ውስንነት፣ ይዞታዎቹን እንዲዳፈሩና በዓሉ በሚገባው መጠን እንዳይከበር ምክንያት ኾነዋል፡፡
የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ኢትዮጵያን ከአምስት የአፍሪቃ ተመራጭ እና ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻዎች አንዱ ማድረግን ዋና ዓላማው አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጿል። ኾኖም፣ ለቱሪስት ፍሰት መስሕብ ለኾነው ቦታ እና ትዕይንት መጠበቅ ትኩረት ሳይሰጡ፣ የመዳረሻነት ግብን እንደምን በቀጣይነት ማሳካት ይቻላል? ጥምቀትን የመሳሰሉ የዐደባባይ በዓላት የማክበሪያ ቦታዎች ይዞታ በየሰበቡ እየተሸራረፈ እና እየተቀማ የሥነ በዓሉ ቀጣይነት አጠያያቂ ሲኾን፣ ቅርሶች ያሉበትን ተጨባጭ ኹኔታ በማጥናት እና በመገምገም የመጠበቅ፣ የመከባከብ እና ቀጣይ የማድረግ ግዴታ ያለበት ሚኒስቴሩ፣ እንደ ባለድርሻ አካል ድምፁን የሚያሰማው መቼ ይኾን? ቅርሶቹ በፈተና ውስጥ ውድቀው ከጠፉ በኋላ ወይም በመዘገባቸው አካል የመሰረዝ ዕጣ ፈንታ ሲገጥማቸው ነውን? ስለ ጃንሜዳ እና ጥምቀት በዓል አከባበር ምንም አለማለቱ እና በበዛ ዝምታ ውስጥ መሰንበቱ ለምን ይኾን?
በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙት 78 የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታዎች(የታቦታት ማደሪያዎች) መሀከል፣ በሕጋዊ ካርታ የተረጋገጠ ማስረጃ ያላቸው 38 ብቻ ሲኾኑ፣ ቀሪዎቹ 40 የማክበሪያ ቦታዎች፣ ካርታ እንዲሰጣቸው ቤተ ክርስቲያን ለከተማ አስተዳደሩ ጥያቄ አቅርባ እስከ አሁን ምላሽ አላገኘችም፡፡ አብዛኞቹ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ያልተሰጣቸው የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታዎች፣ በቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ተይዘው መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጥባቸው የኖሩ ናቸው፤ ቀሪዎቹም የዓመታት የአገልግሎት ዕድሜ የሚቆጠርላቸውና እስከ ዛሬም እየተገለገለችባቸው የሚገኙ ናቸው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ አንዳንድ የመንግሥት ተቋማት እና ልዩ ልዩ አካላት በሚያሳዩት የማናለብኝነት መንፈስ፣ ገሚሶቹ ተነጥቀዋል፤ ቀሪዎቹም አደጋ ተጋርጦባቸዋል። በተለይ ባለፉት ኹለት ዓመታት፣ ቤተ ክርስቲያንን ስትገለገልባቸው የነበሩ ይዞታዎቿ፣ በጠራራ ፀሐይ እየተነጠቁ ለግንባታ እና ሌላ ዓላማ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡ በያዝነው ዓመት ብቻ፣ በርእሰ መዲናዪቱ የተለያዩ ክፍላተ ከተማ፣ ከስድስት በላይ የባሕረ ጥምቀት ይዞታዎች በመነጠቃቸው፣ ከ40 በላይ ገዳማት እና አድባራት የዘንድሮውን በዓለ ጥምቀት የሚያከብሩበት ቦታ የላቸውም። ከወዲሁ አፋጣኝ መፍትሔ የማይሰጥ ከኾነም፣ መጪውን የጥምቀት በዓል የማያከብሩ አድባራት እና ገዳማት እንደሚኖሩ አያጠራጥርም።
በሌላ በኩል፣ ከአዲስ አበባ ከተማ መቆርቆር አስቀድሞ እና የማስተር ፕላን ጥናት ከመጀመሩ በፊት እንዲሁም ከከተማው ማስተር ፕላን ትግበራ በፊት አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩና ረጅም ዘመን ያስቆጠሩ የባሕረ ጥምቀት ይዞታዎች እንዳሉ ይታወቃል። በከተማዋ መመሥረት እና መስፋፋት ሒደት ግን፣ ለዘመናት የሚታወቁበት አገልግሎታቸው በማስተር ፕላኑ ታሳቢ ሳይደረግ፣ መንገድ የወጣባቸው እና ጠፍ የኾኑ አብሕርተ ምጥምቃት አሉ። በከተማዋ ማስፋፋት እና በልማት ስም በተለይ በስፖርት ማዘውተሪያነት ሰበብ የታቦት ማደሪያዎችን መንጠቅ እና ምትክ አለመስጠት ተባብሶ ቀጥሏል።
የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ ዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስ መመዝገቡን ታሳቢ በማድረግ፣ የከተማ አስተዳደሩ አስቀድሞ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የሰጣቸው የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታዎች እንዳሉ ቢታወቅም፣ በባሕረ ጥምቀት የይዞታ ካርታዎች ላይ ደርቦ ለሌላ አካል ተጨማሪ ካርታ መሰጠቱ ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ አሳዝኗል፡፡ ይህ ተግባር፣ የሥራ አፈጻጸም ክፍተት ብቻ ኾኖ ሊታይ አይችልም፡፡ ይልቁንም፣ የመላው ዓለም መስሕብ እና መንፈሳዊ ቅርስ የኾነውን በዓል፣ የሀገር ዕሴት እንኳን ኾኖ እንዳይቀጥል ከማጥፋት ተለይቶ የማይታይ ነው፡፡ በመኾኑም፣ የጉዳዩ አያያዝ ወዴት እያመራ እንዳለ በጥልቀት እንድንመረምር አስገድዶናል።
በሰንበት ት/ቤቶች አንድነት እምነት፣ በጥቂት ሹማምንት እና አበሮቻቸው ጥቅመኝነት እና ጽንፈኝነት በመነጨ ማናለብኝነት እየተከሠተ ያለው ይህ ዓይነቱ አሠራር፣ ለአገራችን ሰላም እና ልማት ቀጥተኛ አደጋ የሚጋርጥ ነው፡፡ መንግሥት ዝንፈቱን በጊዜ አርሞ እስካላስተካከለው ድረስ፥ የአምልኮ ነፃነትን የሚፃረር እና የኦርቶዶክሳውያንን ትዕግሥት የሚፈታተን ብሎም የዓለም አቀፉን መንፈሳዊ ቅርስ ደረጃ በሒደት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ እንዳይኾን አስቸኳይ እልባት እንዲሰጠው እንጠይቃለን፡፡ በዋና ከተማዪቱ እና በሌሎችም ክልሎች፣ በጥንታዊቷ እና ታሪካዊቷ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየተፈጸመ የሚገኝ መዳፈር በመኾኑ፣ አንድነቱ ፈጽሞ እንደማይታገሠው ለማሳሰብ እንወዳለን።
በዚህ አጋጣሚ፣ የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር፣ ቀደም ሲል የጥምቀት ማክበሪያ ይዞታዎችን በካርታ አረጋግጦ ለመስጠት የሔደበትን ርቀት እናደንቃለን፡፡ አኹንም ታሪካዊውን ጃንሜዳን ጨምሮ ጥያቄ ለቀረበባቸው ሌሎችም ቦታዎች፣ ከመጪው የጥምቀት በዓል በፊት ምላሽ እና መፍትሔ በመስጠት፣ ሀገር ለኾነችው እናት ቤተ ክርስቲያን ያለውን ክብር እና ለዓለም አቀፉ የሰው ልጆች መንፈሳዊ ሀብት መጠበቅ ተቆርቋሪነቱን በተግባር በማሳየት ግዴታውን እንደሚወጣ ተስፋ እናደርጋለን።
በመጨረሻም፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አበቤ፣ የጃንሜዳን ባሕረ ጥምቀት ክብር በማይመጥንና ከቤተ ክርስቲያን ዕውቅና ውጪ ለአትክልት ሽያጭ ሥራ የዋለበት ኹኔታ እንዲስተካከል ላሳዩት ትጋት ምስጋናችንን እንገልጻለን፡፡ በአንድ ሳምንት ውስጥ የአትክልት መሸጫዎቹ ፈርሰው እና ተወግደው ለበዓሉ ዝግጁ እንዲኾን መመሪያ በመስጠት እና የጃንሜዳን ጽዳት በማስጀመር ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ ምክትል ከንቲባዋ ያሳዩት ቁርጠኝነት፣ የጥምቀት በዓል እንደቀደሙት ጊዜያት ኹሉ በዓይነተኛ ይዘቱ እና ገጽታው ለማክበር፣ ዓለም አቀፋዊ ቅርስ የኾነበት ደረጃው እና ድምቀቱ ተጠብቆ ለትውልድ ለማሰተላለፍ የሚያስችል ሓላፊነትን የመወጣት ጅማሮ ነውና ቢዘገይም የሚያስመሰግን ተግባር ነው።
በቀጣይም፣ የበዓሉን ቀን መቃረብ ታሳቢ በማድረግ፣ ቦታው ለቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንዲመቻች ያደርጉልን ዘንድ ጥያቄአችንን እናቀርባለን፡፡ በራሱ ታሪክ የኾነውን ጃንሜዳን ጨምሮ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ጥያቄ የቀረበባቸውን የባሕረ ጥምቀት ይዞታዎች እንዲሁም አላግባብ በመነጠቃቸው ሳቢያ የበዓል ማክበሪያ ቦታ ለሌላቸው ገዳማት እና አድባራት ከበዓሉ በፊት ምትክ በመስጠት እና በሕጋዊ ካርታ በማረጋገጥ ይዞታቸውን የማጽናት ታሪካዊ ሥራ እንዲሠሩ፣ በመላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ስም በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት
አዲስ አበባ
(#ሐራተዋህዶ)