Connect with us

የከተማዋ ልጅ የከተማዋ አፍ የሆነበት የአዲስ አበባ ሹመት!

የከተማዋ ልጅ የከተማዋ አፍ የሆነበት የአዲስ አበባ ሹመት!...መልካም የሥራ ዘመን ለአቶ ዮናስ ዘውዴ፤
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የከተማዋ ልጅ የከተማዋ አፍ የሆነበት የአዲስ አበባ ሹመት!

የከተማዋ ልጅ የከተማዋ አፍ የሆነበት የአዲስ አበባ ሹመት!…መልካም የሥራ ዘመን ለአቶ ዮናስ ዘውዴ፤

(ስናፍቅሽ አዲስ ~ድሬቲዩብ)

አዲስ አበባ ካስቸግሯት የሚገርሙኝ ውሃ ማፋሰሻና አፍ የሚሆን ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ማጣት ነበር፡፡ ሁለቱም ቀላል ሆነው ሳለ የከተማዋ ራስ ምታት ሆነው ኖረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ልጅ እንደ ሙዱ የሚያናግረው የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ገጥሞት አያውቅም፡፡ እንደ ባቢሎን ከተማውና ነዋሪው ቋንቋው ለየቅል ሆኖ የኖረው አንድም ለዚህ ይመስለኛል፡፡

አቶ ዮናስ ዘውዴ እንዲያውም የአዲስ አበባ አንድ አፍ ናቸው፡፡ ባገኙት መድረክ ስለ ከተማዋ ያወራሉ፤ ከተማዋ ማረም ያለባትን ያርማሉ፤ ነዋሪው ማድረግ ያለበትን ያነሳሉ፤ የጋራ ሀገር እንዳለን ሳይደክሙ ከሚነግሩን ሰዎቻችን አንዱ ናቸው፡፡

የፍልስፍና መምህሩና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን እየሰሩ ያሉት አቶ ዮናስ ዘውዴ በትናንትናው የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ ምስረታ የአዲሱ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በአማካሪነት ከቆዩባቸው ጊዜያት በላይ በዚህ ሹመት ለከተማቸው ብዙ ነገር እንደሚሰሩ አምናለሁ፡፡

ከተሜነት የራሱ ዘይቤ አለው፤ ብዙ የሀገራችን ከተሞች እንዲመሯቸው ፓርቲው ሲመድባቸው ከኖሩት አመራሮች ጋር ጥሩ የማይባል ግንኙነት እንዲኖራቸው ያደረገው ስነ ልቦና ነው፡፡ የስነ ልቦናው ልዩነትና የከተሜውን ህይወት ዘይቤ አለመረዳት ነዋሪው ከተመሪው እንዲቃረን ያደርጋል፡፡

የአዲስ አበባ ህዝብ ከኢንጅነር ታከለ ጋር ያስማማ የታኬ የአራዳ ልጅነት ይመስለኛል፡፡ ከንቲባ አዳነች የከተማዋ ነዋሪ ሆነው ያሳለፉት ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ እድሜ ከተማዬ ምን ትፈልጋለች? ለሚለው አንዳች ነገር አግዟቸዋል፡፡ 

በኮታ ምደባ ብቻ ከየተገኘበት እየተለቀመ አዲስ አበባን የሚቀራመተው በብሔር ስም የሚሰገሰግ ቡድን ከተማዋን አስለቅሶ ራሱም ሳይደላው እንደ ሌባ ገብቶ እንደሌባ የሚወጣበት ዘመን አሁንም እድሜው አጭር እንዲሆን እመኛለሁ፡፡

የአቶ ዮናስና መሰሎቹ ሹመት ከመጡበት አካባቢ ብሔርና ሰፈር በላይ ለሚያውቁት ከተማ ምን መስራት አለብኝ እንዲሉ ያድርጋል፡፡ ብዙ የደከሙት ከንቲባ አዳነች ለአዲስ አበባ የወጡት ምኞት ይሳካ ዘንድ በድጋሚ መመረጣቸው እና የህዝብ ይሁንታ ያገኙ ከንቲባ መሆናቸው ለከተማዋ ስኬት ድርሻ ይኖረዋል፡፡

በዚሁ አጋጣሚ ምክትል ቢሮ ሃላፊዎች ሹመት ላይ ዓይኖች ወደ መዲናዋ ልጆች እንዲመለከቱ አደራ እላለሁ፤ ብሔሩ ሲፈለግ እንደ ወገኑ መሰለፍ የሚችል የአራዳ ልጅ አለ፤ ኦሮሞ ሆኖ አዲስ አበቤ፣ አማራ ሆኖ አዲስ አበቤ፣ ሲዳማ ሆኖ አዲስ አበቤ፣ ወላይታ ሆኖ አዲስ አበቤ፣ አፋር ሆኖ አዲስ አበቤ፣ ሱማሌ ሆኖ አዲስ አበቤ የትም ሆኖ አዲስ አበቤ አለ፡፡ ያን አዲስ አበቤ ምክትል ቢሮ ኃላፊነቱና ተቋማት መሪነቱ ላይ ማሳተፍ ቢቻል እንድትበለጽግ የተፈለገችዋን ከተማ እውን ለማድረግ ጉዞው አድካሚ አይሆንም፡፡

ለአዳዲሶቹ መሪዎቻችን መልካም የሥራ ዘመን እመኛለሁ፡፡

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top