Connect with us

የዋቤ ላይ ሰዎች፤ የሀገር ልጅ ያበሰረው የወንዝ ቀዘፋ አዲስ የቱሪዝም ዓለም

የዋቤ ላይ ሰዎች፤ የሀገር ልጅ ያበሰረው የወንዝ ቀዘፋ አዲስ የቱሪዝም ዓለም
ሄኖክ ስዩም

ባህልና ታሪክ

የዋቤ ላይ ሰዎች፤ የሀገር ልጅ ያበሰረው የወንዝ ቀዘፋ አዲስ የቱሪዝም ዓለም

የዋቤ ላይ ሰዎች፤ የሀገር ልጅ ያበሰረው የወንዝ ቀዘፋ አዲስ የቱሪዝም ዓለም

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ኢትዮጵያኑ አስጎብኚዎች የሀገራቸውን ወንዞች ከቱሪዝም ስለማስተዋወቅ የጀመሩትን አዲስ ውጥን ለመታደም ወደ ዋቤ ሸለቆ ወርዶ የተመለከተውን እያካፈለን ነው፡፡ የዋቤ ላይ ሰዎች ካላቸው ወንዝ ቀዛፊዎች አንዱ የሆነበትን ጉዞ ትከታተሉት ዘንድ ትረካውን እንጋብዛችሁ፡፡)

(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)

የዋቤ ላይ ሰዎች ወንዙ ጀርባ ላይ ወጥተዋል፡፡ አብሬ አለሁ፡፡ እዣ ወረዳ ነኝ፡፡ ጉራጌዎች ምድር፡፡ ጀልባዋ የተነሳችው ከዳርቻ ቀበሌ ነው፡፡ ዳሩ ላይ ወደ ቆመችው ጀልባ ወጣን፡፡ ልቤ ፈርቷል፡፡ አዲስ ነገር ነው፡፡ ራሴ የምሳተፍበት መውረድ እንጂ መመለስ የሌለበት ዋቤ ወደ ኦሞ ሲሄድ በውሃ ላይ እንደ ወንዝ ፈስሼ የምሸኝበት ጉዞ፡፡

ዋናው ሰው ይበልጣል ጸዳሉ ነው፡፡ ሌሎቻችን አዲስ ነን፤ እንዲህ ያለውን ልምድ አልሞከርነውም፡፡ እሱ ግን ሀገሩ ላይ ታላቅ ዘጋቢ ፊልም ሲሰራ ካርቱም ድረስ በአባይ ገላ ላይ የተጓዘ የውሃ ቀዘፋ አስጎብኚ ነው፡፡ የ”Mystery of the Nile” ዘጋቢ ፊልሙ፤ የእኛው ሰው ይበልጣል፡፡

ዓለም ያበደበት የቱሪዝም ዘርፍ ነው፡፡ ከጀብድም ከውሃ ቱሪዝምም ዘውጎች ይቆራኛል፡፡ ወንዝ ቀዝፎ እንደ ወንዝ መፍሰስ ወንዞቿ ለበዙ ሀገር እንግዳ የቱሪዝም ዓይነት ነው፡፡ ያንን እንሰብራለን ብለው ኢትዮ ራፍት፣ ኤክስክሉሲቨ ኢትዮጵያና ኤንዲ ቱር በጋራ ተነሱ፤ እዚህ ደርሰው እኛም ግቤ ገላ ላይ ወጣን፡፡

ቀዘፋው ተጀመረ፡፡ travel251 የሚል ሎጎ የለጠፈችው ጀልባ ዋቤ ላይ ተንጎማለለች፡፡ ዋቤ ዋቢ ሸበሌ አይደለም፡፡ ዋቤ ከጉራጌ ዞን ደጋ ምድር ተነስቶ ግቤን በመቀላቀል ወደ ኦሞ የሚገባ ወንዝ ነው፡፡ አንዳንድ መረጃዎች የኦሞን ማህጸን ዋቤ ያደርጉታል፡፡

የመጀመሪያው ትዕይንት የሁላችንንም ቀለብ ወሰደው፤ ውሃው ላይ ተተራመስን፡፡ ከፍ ዝቅ ያለችው ጀልባ አንዳች ልብ የሚሰውር ስሜት እንዲሰማን አደረገች፡፡ ቀጠልን፡፡

የመጀመሪያው ዙር የውሃ ቀዘፋ ጉዞ አስራ አራት ኪሎ ሜትሮችን ርቀት ይሸፍናል፡፡ የዋቤ ወንዝ ዳርቻ ውብ ነው፡፡ አንዳንድ ቦታ ግራ የገባቸው ጉሬዛዎች ወንዙ ላይ ያለንውን እኛን በአግራሞት ይመለከታሉ፤ ሌላ ጊዜ ጦጣዎች ሲመለከቱን ዱሩን ያምሱታል፡፡

ዳርቻው ብዙ ጥናት ተደርጎበታል፡፡ በእነ ካቤታ ለገሰ የተሰራው ጥናት 12 አጥቢ እንስሳት መኖሪያ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ረዣዥም ዛፎች ዓይነተ ብዙ ናቸው፡፡ በዚያ ላይ ሀገር በቀል፡፡ የወፉ ድምጽ የአእዋፍ መናኽሪያ እንደሆነ ያሳምናል፡፡

ከባድ የሚባሉ ቦታዎች ገጥመውናል፡፡ ቀልባችን ቁልቁል በሚንደረደረው ጀልባና ጀልባዋን በሚያላጋው ውሃ ሲታመስ ድንጋጤው አይጣል ነው፡፡

የውሃ ቀዘፋ ቱሪዝም ግማሽ ምዕተ አመት የኖረ የዓለም መዝናኛ ነው፡፡ እውነት ለመናገር የተኬዜ የባሮ የአዋሽ የታላቁ አባይ ሀገር ኢትዮጵያ ባዕድ ናት፤ ኪሷን እንዲህ ካለው ጸጋ አላደለበችም፡፡ ልጆቿ የተራቡት ወንዞቿን ይህን ለመሰለው ለመስኖውም መዋል አቅቷቸው ነው፡፡

ወንዘ ብዙ ሀገር ግን ለወንዝ ቀዘፋ ቱሪዝም እንግዳ፤ የጉዞ ጋዜጠኛዋ እንኳን ለመጀመሪያ ጊዜ እየቀዘፈ ያለ፤ ስለ ሀገሬ አሰብኩ፡፡ ይህ ሥነ-ምህዳር በግቤ ሸለቆ ድንበርተኛ ነው፡፡ ሁለቱን መቀላቀል ከተቻለ ድንቅ ነገር ይሆናል፡፡ ዋቤ ግቤ ብሔራዊ ፓርክ እውነት አየው ይሆን?

 

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top