በቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል የተጠረጠሩ በቁጥጥር ስር ዋሉ
በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፣ በቴሌኮም ማጭበርበር የተጠረጠሩ በርካታ ግለሰቦች ከነመሳሪያዎቻቸው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ አስታወቀ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው የቴሌኮም መሳሪያዎችን ወደ ሀገር በማስገባትና ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎች ኢትዮ ቴሌኮም በዘረጋው ኔትወርክ ሳይሆን ራሳቸው በዘረጉት መስመሮች ለደንበኞች ሲያቀርቡ መቆየታቸውን በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ምርመራ ዲቪዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር ሳሙኤል ሰለሞን ገልፀዋል።
ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ከኢንሳ፣ከኢትዮ ቴሌኮም፣ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ባደረገው ክትትል ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኢንስፔክተር ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ለዚህ ህገ-ወጥ ተግባር ሲጠቀሙባቸው የነበሩ 6 ጌትወይ፣ ከ570 በላይ ሲም ካርዶች፣ ቲፕሊንኮችና ሌሎች ህገ-ወጥ የቴሌኮሙኒኬሽን መሳሪያዎች መያዛቸውም ተገልጿል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በሁለቱ ክፍለ ከተሞች ከቴሌኮም እውቅና ውጭ ማሽኖቹን በመጠቀምና የራሳቸውን ኔትወርክ በመፍጠር የውጭ ሀገር ጥሪዎችን በማስተላለፍ በቴሌኮም ላይ ኪሳራ ሲያደርሱ መቆየታቸንውን ኢንስፔክተር ሳሙኤል ሰለሞን በመግለፅ ህብረተሰቡ ለፖሊስ ባደረሰው ጥቆማ መሰረት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁመዋል፡፡
የወንጀል ምርመራ ቢሮው ከፍርድ ቤት የብርበራ ትዕዛዝ በማውጣት ማሽኖቹን ከነ አክሰሰሪዎቹ በመያዝ በኢትዮ ቴሌኮም መሰረተ ልማት ላይ ተጠርጣሪዎቹ ያደረሱትን ኪሳራ ለማጣራት መሳሪያዎቹን ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት ልኮ የምርመራ ውጤቱን እየተጠባበቀ ይገኛልም ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡ ቤቱን ከማከራየቱ በፊት ስለ ተከራዮች ማንነት በቂ መረጃ በመያዝ በትክክል ማጣራት እንዳለበትና እንደዚህ አይነት ህግ-ወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ሲመለከት በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግም ኢንስፔክተር ሳሙኤል ሰለሞን ጥሪ አቅርበዋል፡፡(የፌደራል ፖሊስ)