Connect with us

ከብዙ በጥቂቱ፦

ከብዙ በጥቂቱ፦
Photo: Social media

መዝናኛ

ከብዙ በጥቂቱ፦

ከብዙ በጥቂቱ፦

(ውድነህ ክፍሌ)

በቅርቡ ነው። ጭብጨባ ከጀርባ ይሰማል፡፡ በላብ ተጠምቆ ከመድረክ ጀርባ ተገናኘን፡፡ “አሌክስ የዛሬው ደግሞ ብሷል! ምንድነው ነገሩ?” አልኩት፡፡ አሌክስም “እኔም ገርሞኛል! ይሄ ሁሉ ሃይል ከየት መጣ?…ከኔ አይደለም! ከእሱ ነው!” አለና ወደፈጣሪው ቀና አለ፡፡ በደስታ ተውጦም “ለዚህ ተመልካችስ ምንስ ብትሰጥ ምን ይቆጫል! ከዚህ በላይ ደስታ ከየት ይገኛል?!” አለና ለቀጣዩ ትእይንት ሊዘጋጅ ወደመልበሻ ክፍሉ እየተጣደፈ አመራ፡፡ አሌክስና መድረክ ታወሱኝ፡፡

ሰበዝ 1

ሐረር፤ቀላድ አምባ የተወለደው አሌክስ አዲስ አበባ ሊማር የመጣው ጆግራፊ ወይም ኢኮኖሚክስ ነበር፡፡ አንድ አመት ተምሮ ምርጫውን ሊወስን ሲንደረደር ወሬ ሰማ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ትምህርት እንደሚሰጥ፡፡ ጊዜ አላጠፋም፡፡ 

ሐረር የሚገኙ የመድሐኒያለም ሁለተኛ ደረጃ መምህራኖቹን አማከረ፡፡ “ዩኒቨርስቲ የቴአትር ትምህርት ይሰጣል ልማር ወይ?” ሲል፡፡ እነሱ ደግሞ ትምህርት ቤት እያለ ፍላጎቱን አብጠርጥረው ያውቃሉና “አይንህን አትሽ! ንካው!” አሉት፡፡ ጥሪ ነዋ! ጥሪ ካለ አይቀርልህ! አሌክስ ሰተት አለ፡፡ ተውኔት ተዋናይዋን አገኘች፡፡ ተጀመረ፡፡

ደራሲው በሰማይ ቤት፤ ካሌጉላ፤ እስረኛው ንጉስ፤፤ከአድማስ ባሻገር፤ተውኔቱ፤የኮከቡ ሰው፤ኤዲፐስ ንጉስ…ኧረ ተዉኝ፡፡ ዩኒቨርስቲው ውስጥ የቴአትር ማዕበል ተነሳ፡፡ በእውነት ያ ዘመን ለአሌክስ ወርቃማ ዘመን ነበረ፡፡ እዚያው ዩኒቨርስቲ እያለ ዝናው መናኘት ጀመረ፡፡ ከእሱ ቀድሞት ስሙ ቴአትር ቤት ደረሰ፡፡ በሮቹም ለወጣቱ ብርቅዬ ተዋናይ ተከፍተው ነበር የጠበቁት፡፡ በፍጥነትም ነው ከታዳሚው ልብ ውስጥ የገባው፡፡

አርቲስት አለማየሁ ታደሰ ሁለመናውን መድረክ ላይ ሰጥቶ ሲሰራ ጉድ ያሰኛል፡፡ ንጉስ ነህ ካሉት እስከጥግ በቃ ንጉስ ነው፡፡ ይህንን በአንቲገን አይተነዋል፡፡ ክሪዮንን ሆኖ “ንጉስ ነኝ!” ሲል የክሪዮንን ንግስና ብቻ ሳይሆን የአሌክስን የትወና ንግስና እንቀበላለን፡፡ ከንግስናው ወርዶ ደግሞ “በእስረኛው ንጉስ” ቴአትር የንጉስ አጫዋች ሲሆን ንጉሱን ብቻ ሳይሆን እኛንም አፍ አላስከድን እያለ አድናቆት እንድንቸረው ያስገድደናል፡፡ 

አሌክስ ከእግር ጥፍሩ እስከራስ ጠጉሩ ለሚሰራው ገጸባህሪ ሁለመናውን ይሰጣል፡፡ መስሎ ሳይሆን ሆኖ ሲገኝ ነው ያየነው፡፡ መድረክና አሌክስ ድርና ማግ ናቸው፡፡ አርባ የሚጠጉ የመድረክ ተውኔቶችን ተጫውቷል፡፡ ለመጥቀስ ያህል አንቲገን፤የአዛውንቶች ክበብ፤ኤዲፐስ ንጉስ፤የቼዝ አለም፤የክፉ ቀን ደራሽ፤ ፤ፍርሃት፤የሚተኑ አበቦች፤መርዛማ ጥላ፤አብሮ አደግ፤ክሊዮ ፓትራ፤ ሚስጥረኞቹ፤ካሌጉላ፤ ባቢሎን በሳሎን…በርካታ ናቸው፡፡ አሌክስ ሁለገብም ነው፡፡

ይተውናል፣ያዘጋጃል፣ይጽፋል፣ይተርካል፣ያስተምራል፤ይዳኛል…አንድ ሆኖ ብዙ ነው፡፡ ሚስጥረኞቹ፤ያልተወለደው ልጅ፤የብእር ስምና ትዳር ሲታጠን ከጻፋቸው ተውኔቶች ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ ደመነፍስም የትርጉም ስራው ነው፡፡ በቲቪ ተከታታይ ድራማም በዋናነት የተወነባቸው ኤልዛቤል፤ግጥምጥም፤ፎዚያ፤ደርሶ መልስና መለከትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ፊልሞችም በርካታ ናቸው፡፡

ሰበዝ 2

አንድ ወቅት በሜጋ አንፊ ቴአትር የኪነጥበብ የሽልማት ስነስርአት ይተላለፋል፡፡ ድምጻውያኖች ስማቸው ተጠርቶ የተዋናይ ብቻ ቀረ፡፡ እናም ሰአቱ ደረሰና “የአመቱ ምርጥ ተዋንያን በቼዝ አለም ቴአትር አለማየሁ ታደሰ!” ተባለ፡፡ አሌክስ ስሙ ቢጠራም ወፍ የለም፡፡ እሱ እቴ! አገር ፍቅር ቴአትር ቤት ከወዳጆቹ ጋ ዝግጅቱን በቀጥታ ስርጭት እየተከታተለ አለሙን ይቀጫል፡፡ ድንገት ተሸላሚ መሆኑን ሲሰማ ደነገጠ፡፡ ደስታና ድንጋጤ ተቀላቅሎበት በወዳጆቹ ታጅቦ ወደ ሜጋ አምፊ ቴአትር ገሰገሰ፡፡ እያለከለከም የዝግጅቱ ፍጻሜ ላይ ደረሰ፡፡ በምርጥ ተዋናይነት የአስራ ስድስት ግራም ወርቅ አንገቱ ላይ አጠለቀ፡፡

የሽልማት ነገር ከተነሳ አሌክስ በሃገር አቀፉ የመገናኛና የኪነጥበብ የሽልማት ድርጅት በ1996 ዓ.ም እጩ ነበር፡፡ በለዛ አዋርድም የአመቱ ምርጥ ተዋናይ ተብሎ ተሸልሟል፡፡ የበጎ ሰው ሽልማት ድርጅትም እውቅና ሰጥቶታል፡፡ በመርዛማ ጥላ ቴአትርም በምርጥ ተዋናይነት ለተከታታይ አመት በካፒታል የእንግሊዝኛ ጋዜጣ አለማየሁ ታደሰ ምርጥ አክተር ተብሎ ስሙ ከፍ ብሏል፡፡

አርቲስት አለማየሁ ታደሰ ከሃያ አመት ያላነሰውን እድሜውን ለባቢሎን በሳሎን ቴአትር ሰጥቷል፡፡ ግንቦት 2/1992ዓ.ም የተከፈተው ባቢሎን በሳሎን ይኸው አለ፡፡ አሌክስ ታሞ ወገቡን አስሮ ሲሰራ አይቻለሁ፡፡ ድምጹ ተዘግቶ ከጉሮሮው ጋ ትንቅንቅ ፈጥሮ መድረክን የሙጥኝ ሲል ታዝቤአለሁ፡፡ ይህ ሁሉ ምንድነው!? ከመድረክ ላለመለየት የሚደረግ ስቃይ ነው፡፡

አሌክስ ከላይ የተናገረውን እደግመዋለሁ፡፡ እንደዚህ አለ “…ይሄ ሁሉ ሃይል ከየት መጣ?…ከኔ አይደለም! ከእሱ ነው!” አለና ወደፈጣሪው ቀና አለ፡፡ 

ለብርቅዬ አርቲስቶቻችን ክብር ይገባቸዋል፤የምናውቀውንም ልንመሰክርላቸው ይገባል፡፡ አሌክስ ከነመላው ቤተሰብህ ሰላምህ ይብዛ፡፡

 

Click to comment

More in መዝናኛ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top