የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከ2 ሺህ 700 በላይ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ሥር አዋለ
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በመዲናዋ በመኖሪያ ቤቶች፣ በተቋማትና በተሽከርካሪዎች ላይ ከጥቅምት 25 እስከ ሕዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው ብርበራና ፍተሻ ከ2 ሺህ 700 በላይ የጦር መሳሪያዎችና ከ80 ሺህ በላይ ጥይቶችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገለጸ።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት መሳሪያዎች የእጅ ቦምቦች፣ ፀረ ተሽከርካሪ ፈንጂ፣ የእጅና የጦር ሜዳ የረጅም ርቀት የትከሻ የሬዲዮ መገናኛዎች፣ ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎች፣ ላውንቸሮች፣ ሽጉጦችና ጠመንጃዎች ይገኙበታል።
መሣሪያዎቹና ጥይቶቹ የተያዙት ኮሚሽኑ ከፌዴራል ፖሊስና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ባደረገው ብርበራ መሆኑ ተገልጿል።
ኮሚሽኑ በተለይ ከህወሃት ጁንታ ጋር ግንኙነት ያላቸውና የቡድኑን ተልዕኮ ለመፈፀም የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኃይሎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ጥብቅ ፍተሻ ማድረጉን ጠቅሷል።
ከጥቅምት 25 እስከ ሕዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም በሕዝብ ጥቆማና በፀጥታ አካላት በተጠረጠሩ መኖሪያ ቤቶች፣ ተሽከርካሪዎችና ተቋማት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብርበራ ተካሂዷል።
በዚህም 60 የእጅ ቦምቦች፣ አንድ ፀረ ተሽከርካሪ ፈንጂ፣ ከ141 በላይ የእጅና የጦር ሜዳ የረጅም ርቀት የትከሻ የሬዲዮ መገናኛዎች፣ 809 ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎች፣ ሁለት ላውንቸሮች፣ 976 ሽጉጦችና 924 ጠመንጃዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
1 ሺህ 312 የፀጥታ አካላት የደንብ ልብሶችና በርካታ ወታደራዊ ቁሳቁሶች በፍተሻው መገኘታቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በተጨማሪም 1 ሺህ 799 አዳዲስ ሲም ካርዶች፣ 6 የውጭ አገር ስልክ መጥለፊያ መሳሪያዎች፣ 629 ተንቀሳቃሽ ስልኮችም ተገኝተዋል።
የተለያዩ የባንክ ሂሳብ ደብተሮችና ማህተሞች እንዲሁም በፀጥታ ሃይሎች እጅ ብቻ ሊገኙ የሚገባቸው በርካታ ቁሳቁሶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ነው ኮሚሽኑ የገለጸው፡፡
በሌላ በኩል የህወሃት ጁንታ ተላላኪዎች ለጥፋት ተግባር ያዘጋጇቸውን የተለያዩ አይነት የጦር መሳሪያዎች በየቦታው እየተጣሉ መሆናቸውን አስታውቋል።
የጥፋት ኃይሎች በሕዝብ ላይ ጉዳት ለማድረስና ከሕግ ተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ ያደረጉት ቢሆንም ኮሚሽኑ ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ዕቅዳቸውን ማክሸፉን ገልጿል።
በኅብረተሰቡ ጥቆማ 25 የእጅ ቦምቦች፣ 4 የተለያዩ ፈንጂዎች፣ 11 ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎች፣ 40 ሽጉጦች፣ 6 የተለያዩ ጠመንጃዎች ከመሰል 914 ጥይቶቻቸው ጋር ከተጣሉበት ሥፍራ በፀጥታ አካላት ተነስተዋል።
በሌላ በኩል በሕግ ማስከበር ሥራ ከ4 ሚሊዮን 300 ሺህ በላይ ብር፣ 248 ሺህ 941 የአሜሪካ ዶላር፣ 3 ሺህ 172 ዩሮና ከ192 ሺህ በላይ የተለያዩ አገራት ገንዘብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ጠቅሷል።
178 ሺህ 265 ብር፣ 181 ሺህ 900 የአሜሪካ ዶላርና 200 ዩሮ ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶች ከነተጠርጣሪዎቹ ተይዘው በምርመራ ላይ እንደሆኑም ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በህወሓት ጁንታና ተላላኪዎቹ ላይ እየተወሰደ ባለው እርምጃም በመዲናዋ ከተጠረጠሩ 1 ሺህ 127 ግለሰቦች መካከል 1 ሺህ 88 በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጿል።
ከእነዚህም መካከል በ1 ሺህ 938 የክስ መዝገቦች ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝም ዘርዝሯል፡፡
ኅብረተሰቡ ለፀጥታ ስጋት ይሆናሉ ተብለው በተጠረጠሩ መኖሪያ ቤቶች፣ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ በሚያደርገው ብርበራና ፍተሻ ድጋፍ እንዲያደርግ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።
የመዲናዋን ሠላምና ጸጥታ ለመጠበቅ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከሌሎች የፀጥታ አካላትና ከኅብረተሰቡ ጋር እየሰራ መሆኑንም ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።(ኢዜአ)