Connect with us

የፈጣን አውቶብስ መስመር  የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት  የወሰን ማስከበር ችግር ገጥሞታል

የፈጣን አውቶብስ መስመር የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት የወሰን ማስከበር ችግር ገጥሞታል
Photo: Social media

ዜና

የፈጣን አውቶብስ መስመር  የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት  የወሰን ማስከበር ችግር ገጥሞታል

የፈጣን አውቶብስ መስመር  የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት  የወሰን ማስከበር ችግር ገጥሞታል

በ2012 በጀት ዓመት መጨረሻ አካባቢ የመሰረት ድንጋዩ የተቀመጠው የፈጣን አውቶቢስ መስመር (BRT) የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ላይ ያጋጠመው የወሰን ማስከበር ችግር ትኩረት እንደሚሻ ተገለፀ፡፡

ይህ ቢ2 ኮሪዶር ተብሎ የሚጠራው የፈጣን አውቶቢስ መስመር 19 ነጥብ 2 ኪ.ሜ ርዝመትና 23 የአውቶቢስ መጠበቂያ ጣቢያዎች ያሉት ሲሆን 7 ሜትር የጎን ስፋት አለው፡፡  ፕሮጀክቱ ከዊንጌት ተነስቶ በአውቶቢስ ተራ አድርጎ በተክለ ሀይማኖት በሰንጋ ተራ ሜክሲኮ፤ ከሜክሲኮ በቡልጋሪያ ቄራ አድርጎ  ወደጎፋ በመሻገር በጀርመን አደባባይ ጀሞ የሚዘልቅ ነው፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የፈጣን አውቶቢስ መስመሩን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ የወሰን ማስከበር ስራዎችን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡ ይሁንና የግንባታ ስራውን ለማስጀመር የሚያስችል የወሰን ማስከበር ስራዎች በሚፈለገው ደረጃ እየተከናወነ አለመሆኑ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የወሰን ማስከበር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አንዳርጌ ክፈተው ተናግረዋል፡፡ እነዚህ የወሰን ማከበር ስራዎች በሚፈለገው ፍጥነት የማይከናወኑ ከሆነ የግንባታ ስራውን  ሊያጓትት ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው አቶ አንዳርጌ አክለዋል ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ባለስልጣኑ ለይቶ ከያዛቸው አጠቃላይ የወሰን ማስከበር ስራዎች መካከል 773 በከፊልና በሙሉ የሚነሱ ቤቶች፣ 933 የመብራት ምሶሶዎች በግንባታ ክልል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በቀጣይ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በክፍለ ከተማ በኩል የልማት ተነሺዎች ምትክ የቀበሌ ቤትና ቦታ በወቅቱ እንዲያገኙ የሚያስችል ስራዎችን እንዲያከናውኑ መመሪያ መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም የመሰረተ ልማት ዘርጊ ተቋማት ከባለስልጣኑ ጋር በመናበብና የጋራ እቅድ በማዘጋጀት ስራዎችን የሚከናወኑ ይሆናሉ፡፡ የተከናወኑ ስራዎችንም በየጊዜው የሚገመገምበትና የመፍትሄ አቅጣጫ የሚቀመጥበት አሰራር መዘርጋቱን አቶ አንዳርጌ ገልፀዋል፡፡

ይህ ለከተማችን ብሎም ለሀገራችን የመጀመሪያ የሆነው የፈጣን አውቶቢስ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመታት የሚያስፈልጉ ሲሆን  ራዜል – ቢኢሲ /RAZEL-BEC የተባለ ዓለም ዓቀፍ የፈረንሳይ የስራ ተቋራጭ የግንባታ ስራውን ያከናውነዋል፡፡ የማማከርና የግንባታ ቁጥጥር ስራውን ሳፌጅ /SAFEGE- የተባለ አማካሪ ድርጅት ከሌሎች ሁለት አማካሪ ድርጅቶች ጋር በጥምረት የሚከናወን ይሆናል፡፡ ለዚህ ኮሪደር ግንባታ የሚውል ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተይዞለታል፡፡

ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ሲጠናቀቅ  በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ ዝቅተኛ፣ መካከለኛ ገቢ ያላቸው እና በአዲስ አበባ ዙሪያ  ሚኖሩ ዜጎች በስፋት እንዲጠቀሙበት ታሳቢ ተደርጎ የሚገነባ  የብዙሀን ትራንስፖርትን ማሳለጫ መስመር  ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ በአዲስ አበባ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቅረፍና ዘመናዊ የብዙሀን ትራንስፖርትን ለማስፋፋት ትልቅ እገዛ ይኖረዋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ (የአ/አ መንገዶች ባለስልጣን)

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top