በርሜል ሙሉ ገንዘብ ተገኘ መባሉን ፖሊስ አስተባበለ
~ የተገኘው 45ሺ ብር ነው፣
በአራዳ ክፍለ ከተማ በልመና በሚተዳደሩ አንዲት ግለሰብ ቤት ውስጥ ከ45 ሺህ ብር በላይ መገኘቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ፡፡ በርሜል ሙሉ ገንዘብ ተከማችቶ ተገኘ በሚል በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች እየተላለፈ ያለው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታዉቋል፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 አትክልት ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በልመና የሚተዳደሩት፣ ምንም አይነት ረዳትም ሆነ ልጅ በአጠገባቸው የሌላቸው የአይምሮ ህመም ያለባቸው ወ/ሮ በሪያ አህመድ በመኖሪያ ቤታቸው በርካታ የተቋጠሩ ፌስታሎች ተጠራቅመው መገኘታቸው ስጋት ያሳደረባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ መሰረት ፖሊስም ከወረዳው አስተዳደር ጋር በመሆን ሁኔታውን ለማረጋገጥ ወደ ስፍራው ማምራታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡
በቦታው ላይ በተደረገው የማረጋገጥ ስራ በግለሰቧ መኖሪያ ቤት ውስጥ በርካታ የተቋጠሩ ፌስታሎች እና ሌሎች ቆሻሻ ዕቃዎች ተከማችተው የተቀመጡ ሲሆን ከተቋጠሩት ፌስታሎች መካከል ገንዘብ ያለባቸው እንደተገኙም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም በልብስ መዘፍዘፊያ ፕላስቲክ የተወሰኑ ብሮች ተቀምጠው እንደነበር የገለፀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከአካባቢው ነዋሪዎች ታዛቢዎችን በመጨመር ፖሊስ እና የወረዳው አስተዳደር ባደረጉት ቆጠራ በየፌስታሉ እና በልብስ መዘፍዘፊያው ፕላስቲክ ተቀምጦ የተገኘው ገንዘብ 45 ሺህ 858 ብር ሆኗል፡፡
ፖሊስ ኮሚሽኑ እንዳስታወቀው ከተገኘው ገንዘብ ውስጥ አንድ ሺህ ብር ግለሰቧ ለዕለት ወጪያቸው እንዲጠቀሙበት የተሰጣቸው ሲሆን የወረዳው አስተዳደር እና ፖሊስ ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር ተነጋግረው አንድ ሺህ ብር ወጪ በማድረግ እና የጉልበት ሰራተኛ በመቅጠር በግለሰቧ መኖሪያ ቤት የተከማቹት ቆሻሻዎች እንዲወገዱ እና አካባቢያቸው እንዲፀዳ ተደርጓል፡፡
ቀሪው 43ሺህ 858 ብር ደግሞ በግለሰቧ ስም የባንክ የሂሳብ ቁጥር ተከፍቶ ገንዘቡ ገቢ እንደተደረገላቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስረድቷል ፡፡
ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች በሙሉ ለፖሊስ መረጃ መስጠቱ የሚበረታታ መሆኑን የገለፀው ኮሚሽኑ ይሁን እንጂ ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ አንዳንድ የመገናኛ ዘዴዎች በአዲስ አበባ በበርሜል ሙሉ ብር ተከማችቶ ተገኘ በሚል ያሰራጩት ዘገባ የተሳሳተ መሆኑን ህብረተሰቡ ሊገነዘብ ይገባል ብሏል፡፡(አ/አ ፖሊስ ኮምሽን)