Connect with us

በማይካድራ የተገደሉ ሰዎች ‘የጦር ወንጀል’ ሊሆን እንደሚችል ተመድ ጠቆመ

በማይካድራ የተገደሉ ሰዎች 'የጦር ወንጀል' ሊሆን እንደሚችል ተመድ ጠቆመ
FBC

ወንጀል ነክ

በማይካድራ የተገደሉ ሰዎች ‘የጦር ወንጀል’ ሊሆን እንደሚችል ተመድ ጠቆመ

በማይካድራ የተገደሉ ሰዎች ‘የጦር ወንጀል’ ሊሆን እንደሚችል ተመድ ጠቆመ

 

በትግራይ ክልል ማይካድራ ከተማ በርካታ ዜጎች ተገድለዋል የሚል ሪፖርት መውጣቱን ተከትሎ “ግድያዎቹ መረጋገጥ ከቻሉ እንደ ጦር ወንጀል ይቆጠራል” በማለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አስጠንቅቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ሚሼል ባችሌት በማይካድራ ከተማ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ተገድለዋል የሚለው ሪፖርትም እንዲጣራ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጭፍጨፋውን የፈፀሙት የህወሓት ታጣቂዎች ናቸው ቢሉም የትግራይ ክልል ባለስልጣናት በበኩላቸው በግድያዎቹ እጃችን የለበትም በማለት ውድቅ አድርገውታል።

የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶክተር) ውንጀላዎቹ “መሰረት” የሌላቸው ናቸው ማለታቸውንም አጃንሰ ፍራንስ ፕሬስ እሳቸውን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በበኩላቸው የፌደራል መንግሥት የምዕራብ ትግራይን “ነፃ ካወጣ” በኋላ የህወሓት ታጣቂዎች በማይካድራ ከተማ በርካታ ንፁሃን ዜጎችን “በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለዋል” ብለዋል።

የማይካድራ ከተማ በትግራይ ክልል ደቡብ ምዕራብ ዞን ትገኛለች።

የግድያውን ሪፖርት ያወጣው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ግድያውን ማን እንደፈጸመው ለማረጋገጥ አለመቻሉን አመልክቷል። ነገር ግን ያነጋገራቸው የአይን እማኞች ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ጋር የሚዋጉትን የህወሓት ታማኝ ኃይሎች ጥቃቱን እንደፈጸሙ ይከሳሉ።

ግድያዎቹ መረጋገጥ ከቻሉም በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል በተነሳው ጦርነት የተገደሉ በርካታ ንፁሃን ዜጎች ያደርጋቸዋል።

ከሳምንት በላይ ባስቆጠረው ግጭት በትግራይ ክልል የስልክም ሆነ የኢንተርኔት አገልግሎት ባለመኖሩ ስለ ግጭቱ መረጃ ለማግኘት አዳጋች አድርጎታል።

ሚሼል ባችሌት እንዳሉት በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው ሁኔታ ስጋት እንደፈጠረባቸው ጠቅሰው “ከዚህ በበለጠ ግፎች ከመፈፀማቸው በፊት ለመከላከል ያስችል ዘንድ የውጊያው መቆም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው ብለዋል።(BBC)

 

Click to comment

More in ወንጀል ነክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top