ወ/ሮ አዳነች አበቤ ከ1973 እስከ 1981 አዲስ አበባን በከንቲባነት ያገለገሉትን ኢንጅነር ዘውዴ ተክሌን መኖሪያ ቤታቸው ድረስ በመሄድ እንኳን አደረሰዎት ብለዋል
የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ አዲሱን አመት ምክንያት በማድረግ ከአደረጓቸው ተግባራት አንዱ የማይጠበቅም የሚያስደስትም ሆኗል፡፡
ከንቲባዋ እንኳን አደረሳችሁ በማለት መኖሪያ ቤታቸው ድረስ በመሄድ መልካም ምኞታቸውን የገለጹላቸው አንዱ ሰው የቀድሞ የአዲስ አበባ ከንቲባ በከተማ ውበትና ጽዳት ስማቸው የሚነሳ የስራ ሰው የሚባሉት ኢንጅነር ዘውዴ ተክሌ ናቸው፡፡
ከ1973 እስከ 1981 ዓ.ም. አዲስ አበባን በከንቲባነት የመሩት ኢንጅነር ዘውዴ ተክሌ በከንቲባዋ በወይዘሮ አዳነች አበቤ የሚመራ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ መኖሪያ ቤታቸው ድረስ በመሄድ እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገርዎት ብለዋቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቀደመውን ረግጠህ አዲስ ታሪክ ፍጠር በሚል የፖለቲከኞች አባዜ ለሀገር በርካታ ስራዎችን የሰሩ ሰዎች የተለየ ክብር አይሰጣቸውም፡፡
ስራቸው የሚሸፈን ስማቸው እንዳይነሳ የሚደረግ መሆኑ ላይ ደግሞ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ጭምር የሀሳቡ ተጋሪ ሆነው ኖረዋል፡፡ አዳነች አበቤ ባልተለመደ መልኩ ያሳዮት ይህ ቀደምትን የማክበር ባህል የሚመሰገንና ሊቀጥል የሚገባው ባህል ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክረተሪያት የከንቲባዋን የአዲስ አመት የኢንጅነር ዘውዴን እንኳን አደረሰዎት የጥየቃ ዜና አስመልክቶ ባሰፈረው መረጃ ወይዘሮ አዳነች አበቤ “የከተማችንን ነዋሪ በቅንነትና በትጋት ስላገለገሉ እናመሰግናለን” በማለት ኢንጅነር ዘውዴ በከንቲባነት የስራ ዘመናቸው ለሰሩት ስራ እውቅናና ምስጋና አቅርበዋል፡፡
እንደ ፕሬስ ሴክረተሪያት ዘገባ ከሆነ ከንቲባዋ በቀጣይ ልምድም ምክር ለመውሰድ ወደ ታላቁ ቀደምት የከተማ ሙያ አባት ዳግም እንደሚመለሱ በእንኳን አደረሰዎት ጥየቃው ወቅት ገልጸውላቸዋል፡፡ የዚህ ዜና ምስልም የተገኘው ከፕሬስ ሴክረተሪያት ገጽ ነው፡፡