Connect with us

ሸለቆው ውስጥ ሞትን አገኘሁት!…

ሸለቆው ውስጥ ሞትን አገኘሁት!...

ማህበራዊ

ሸለቆው ውስጥ ሞትን አገኘሁት!…

ሸለቆው ውስጥ ሞትን አገኘሁት!…

(አንተነህ ይግዛው)

(43 ሰዎች የሞቱበት የአባይ በረሃ የመኪና አደጋ ማስታወሻ)
.
.

ከአራት አመታት በፊት…
በዛሬዋ ዕለት…
እግር ጥሎኝ አባይ በረሃ ሸለቆ ውስጥ ተገኘሁ…

ዛሬም ድረስ ከአእምሮዬ ካልጠፋ፣ መቼም ከማልረሳው፣ አንዳች አሰቃቂ ትዕይንት ጋር ተገጣጠምኩ…

43 ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት የዳረገውን፣ የ“ስካይ ባስ” አውቶቡስ አሰቃቂ አደጋ በአይኖቼ ተመለከትኩ…

ሸለቆው ውስጥ ሲሆን ያየሁትን፣ አይቼም የተሰማኝን፣ በወቅቱ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ እንዲህ ጻፍኩት…

ዕለቱን ለመዘከርም፣ ወዲህ አመጣሁት!…
.
.

መንገደኞች ነን፡፡

ወደ ሰሜን ልናቀና ጓዛችንን ጠቅልለን ከየቤታችን የወጣን…
ከንጋቱ 12 ሰዓት ላይ መስቀል አደባባይ ተገናኝተን፣ ወደ ጐንደር ለመጓዝ የተቀጣጠርን 12 መንገደኛ ጋዜጠኞች፡፡

“አደራ እንዳትቀሩ” ብላ ልካብናለች ጐንደር፡፡
ጥምቀትን አብረናት እንውል ዘንድ ጠርታናለች፡፡
ጥሪዋን አክብረን ልንሄድ ነው የተገናኘነው፡፡
ሄደን ልናያት፣ አይተን ልናጣጥማት፣ ተቀጣጥረን ተገናኝተናል፡፡

እኔ ሄኖክ፣ እነ እማዋይሽ፣ እነ መልካሙ፣ እነ ዳንኤል፣ እነ ሳሚ፣ እነ ነብዩ…
እኛ ሩቅ ተጓዥ ጋዜጠኞች…

ብዙዎቻችን እርስበርስ የምንተዋወቅ ነንና፣ ለመግባቢያ ብለን የምናባክነው ጊዜ የለንም፡፡
እንደተገናኘን ነው ሳቅ ጨዋታው የተጀመረው፡፡

የሪፖርተር ጋዜጣው ሄኖክ ያሬድ፣ በዚያ እርስበርስ በምንግባባበት፣ ወደ ደቡብ ስንዘልቅ፣ ወደ ድሬዳዋ ስንሻገር፣ ከዚህ በፊት አብረን ስንጓዝ በለመድነው ሰላምታ ነው የተቀበለን፡፡

“አባ መስቀላዬ!” እያለ…

ከባለስልጣኖቻችን በአንዱ ስም የሚጠራ ነጭ “ሚኒባስ” ተዘጋጅቶልናል፡፡

ይህ “ሚኒባስ” በባለስልጣኑ ስም የተሰየመበትን ምክንያት ለማሰላሰልና “ይሄ ነው” ለማለት፣ በቂ ጊዜ ወስዶ ጥናት ማድረግ ይጠይቃል፡፡

እኔ ደግሞ ለጥናት የሚሆን በቂ ጊዜ የለኝም፡፡

ቸኩያለሁ፡፡

ሚኒባሱ ጉዞ የሚጀምርበትን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቅኩ ነው፡፡

ስለ “ሚኒባሱ” ስም ከማጥናት ይልቅ፣ ከጐኑ በተደረደሩ አውቶብሶች መቅናት ጀምሬያለሁ፡፡

ዘመናዊ አውቶብሶች መንገደኞችን ይዘው በየአቅጣጫው ጉዞ እየጀመሩ ነው፡፡
ወደ ባህርዳር፣ ወደ መቀሌ፣ ወደ ሐረር፣ ወደ ጐንደር…

በአውቶቡሶቹም በተሳፋሪዎቹም ቀናሁ፤ ቶሎ ጉዞ ጀምረው ቶሎ ያሰቡበት ይደርሳሉ፡፡

ከእነዚህ አውቶቡሶች አንዱ ወደ ጐንደር ነው የሚሄደው፡፡
እኛ ወደምንሄድበት አቅጣጫ ነው የሚያቀናው…
ከእኛ ቀድሞ ሲነሳ ሳየው፣ ከእኛ ቀድሞ እንደሚደርስ እያሰብኩ ነው በዚህ አውቶቡስ የምቀናው፡፡

የጐንደሩ አውቶቡስ ሄደ…
.

ከንጋቱ 12 ሰዓት ከ45 ደቂቃ…

ከፊታችን የሚጠብቀንን 750 ኪ.ሜ ያህል መንገድ፣ በሳቅ ጨዋታ ታጅበን ጀመርነው፡፡

ከጨዋታ አዋቂዎች ጋር ነኝ፡፡
ቀልደው ከሚያስቁ ባለለዛዎች ጋር ነው ጉዞዬ፡፡
ከመስቀል አደባባይ ተነስተን፣ በብሔራዊ በኩል ሽቅብ ወደ ፒያሳ እያመራን ነው፡፡

የቸርችል ጐዳናን ዳገት ልንጨርስ ጥቂት ሲቀረን ግን፣ ከመካከላችን አንደኛው ተጓዥ ወደ ውጭ እየጠቆመ በግርምት ማውራት ጀመረ፡፡

“ገና ሳይጀመር?!” አለ በጣቱ ወደ ውጭ እየጠቆመ፡፡

ጣቱን ተከትለን ወደ ውጭ ተመለከትን፡፡

ወደ ሰሜን ሊጓዝ ከመስቀል አደባባይ ቀድሞን የተነሳው፣ ዘመናዊ የስካይ ባስ አውቶቡስ፣ ከመንገድ አካፋይ የብረት አጥር ጋር ተጋጭቶ ቆሟል፡፡

“ቀድመውኝ ሊደርሱ ነው” ብዬ የቀናሁባቸው ተሳፋሪዎች፣ ከአውቶብሱ ወርደው ተመለከትኳቸው፡፡

“አቦ ይሄ እኮ ነው ‘ነጃሳ’ የሚባለው!… እኔ ጉዞ ልጀምር ስል እንደዚህ አይነት ነገር ሲገጥመኝ ይደብረኛል፡፡ ‘ምልኪ’ ሲባል ሰምታችሁ አታውቁም?…” ሲል ጠየቀን የሃሌታ ማስታወቂያው ካሜራ ማን ሳሚ፡፡

ሳሚ ስለ “ምልኪ” መተንተኑን፣ መኪናችን በደጐል አደባባይ ዞራ ወደ ጊዮርጊስ መክነፏን ቀጥለዋል፡፡

የእንጦጦን ዳገት ተያይዘዋል፡፡
ግራና ቀኙን ወደ እንጦጦ የሚሮጡ ስፖርተኞች ይታዩናል፡፡
ከእነዚህም መካከል አንዱ፣ ነገ ከነገ ወዲያ ራሱንም አገሩንም የሚያስጠራ፣ አትሌት ሊሆን ይችላል …

ዛሬ ግን፣ ለእኛ ለመንገደኞች ተጨማሪ ሳቅ የሚያመጣ ተተኪ የቀልድ መነሻ ሆኖናል፡፡

በመስኮት ያየውን ጀማሪ አትሌት መነሻ በማድረግ ገጠመኙን ጀመረ – ከመካከላችን አንዱ፡፡
.

አንድ ማለዳ ነው፡፡
ይሄው ወዳጃችን የሚሰራው ከእንጦጦ አቅራቢያ ነበርና፣ ወደ ቢሮው ሲያመራ አንድ ከሳ ያለ አትሌት ሩጫውን ገታ አድርጐ ይጠጋዋል፡፡

“ምን ልርዳህ?” አለ ወዳጃችን፡፡
“ይ… ይቅርታ… ካላስቸገርኩህ… በዚህ የሞባይል ቁጥር ሚስኮል ታደርግልኛለህ?…” በትህትና ጠየቀ ሯጬ፡፡

በሚሊዮን ዶላር የሚያገኝ ታዋቂ አትሌት ሊሆን የሚችል ሰው፣ እንዴት የ”ሚስኮል ያጣል?” ብሎ አዘነ፡፡ ሊረዳውም ሞባይሉን አወጣ፡፡

አውጥቶ ግን የተጠየቀውን አላደረገም፡፡ አሰበ እንጂ፡፡
ሯጩን እያየ ጥቂት አሰበ፡፡

አሰበና ሞባይሉን መልሶ ወደ ኪሱ ከተተና፣ አትሌቱን በቆመበት ትቶት ጉዞውን ቀጠለ፡፡

“ጥሩ አልሰራህም” አለ ከመካከላችን አንዱ፡፡
“ምን ነካችሁ! … ሚስኮል አድርግልኝ ብሎ ሞባይሌን ይዞ ቢሮጥስ! … በምን አቅሜ ልደርስበት ነው!… ሯጭ እኮ ነው!” የሚል ነበር መልሱ፡፡

በሯጩ ልጅ ቀልድ ያልሳቀው፣ ሯጩ ሚኒባስ ብቻ ነው፡፡

ሯጩ ሚኒባስ…

ዳገት ቁልቁለት የማይገደው፣ ድካም የማያዝለው፣ እስኪ ልረፍ የማይለው፣ ሽምጥ የሚጋልበው፣ ቢሮጥ የማያልበው ሯጩ ሚኒባስ…
.

ሚኒባሱ ይጋልባል …
ሱሉልታን ወደ ኋላው ትቶ፣ ጐርፎን ተሻግሮ፣ ጫንጮን አልፎ፣ ሙከጡሪና ደብረ ፅጌን አቆራርጦ ወደ ፍቼ ይገሰግሳል፡፡

የሰላሌን ሜዳ ሽምጥ የሚጋልበው ሰጋር ሚኒባስ፣ ለካ እሱም ማቆሚያ አለውና፣ ፍቼ ላይ ሲደርስ የብረት ልጓሙ ገታው፡፡

ፍቼ ላይ ቁርስ ቀማምሰን ቀጣዩን ጉዞ ተያይዘነዋል፡፡

ወደ ደገም… ወደ ገርበ ጉራቻ… ወደ ጐሃ ፅዮን…

እዚህ ይሳቃል፣ እዚያ ይቀለዳል፣ ከፊት ቁምነገር … ከኋላ ጨዋታ ደርቷል፡፡

ከረፋዱ 4 ሰዓት ከ20 ደቂቃ፡፡

አሁን የቅድሙ ሳቅ የለም፡፡

ይህ የፍርሃትና የስጋት ክፍለ ጊዜ መጀመሪያ ነው፡፡
አባይ በረሃው አፉን ከፍቶ ከፊታችን ተሰርጉዷል፡፡

ክንፍ አውጥቶ መብረር ሰላሌ ሜዳ ላይ ነው፡፡ ለጥ ያለ ሜዳ አብቅቷል፡፡ ጉዞው የገደል ነው፡፡ ጉዞው በሽምጥ ሳይሆን በምጥ መሆን አለበት፡፡
ሰላሌ ሜዳውን እንጂ፣ አባይ ሸለቆውን ሽምጥ አይጋልቡትም፡፡

እየተጠማዘዘ፣ ጋራ እየታከከ፣ እየጠበበ፣ እየኮረበ ቁልቁል ወደ በረሃው ስምጥ የሚዘልቀውን መንገድ ቀስ ብሎ ነው መውረድ… በመላ …

ለመዘናጊያ የሚሆን ጊዜም ቦታም የለም፡፡

ለአፍታ መዘናጋት አጉል ነገር ያመጣል፡፡ ከሚኒባሱ ጐማዎች በጥቂት ሴንቲ ሜትሮች ርቀት ላይ፣ ሞት አፉን ከፍቶ አድፍጧል፡፡ ሞትና ህይወት በሴንቲ ሜትሮች ርቀት ቀጭን ጠመዝማዛ ድንበር አስምረው፣ ቁልቁል ወደ አባይ የሚወርዱበት የጭንቅ ሸለቆ ውስጥ ነው የምንገኘው፡፡

እዚህ መስጋት ይጀመራል፡፡
ቅድም የነበረው ሳቅ ይፈዝዛል፡፡
ቅድም ያልታሰበው ይታሰባል፡፡

“ሚኒባስ… ሾፌር በሚባል ጋላቢ የሚመራ ሰው ሰራሽ ፈረስ ነው” እያሉ ማሰብ ይጀመራል፡፡
ሾፌሩ የሚኒባሱን መሪ ብቻ ሳይሆን፣ የተሳፋሪዎቹን ዕጣ ይዞ የሚጓዝ ወሳኝ ሰው ስለመሆኑ ይታሰባል፡፡

“አይዞን!” ይላል አንዱ ተሳፋሪ ቅድም የዘነጋውን ሾፌር ለማበረታታት፡፡
.

አባይ በረሃ ውስጥ ነን….

በግራም በቀኝም ስጋት የሞላበት ጠመዝማዛ የቁልቁለት መንገድ ላይ ነን፡፡
በዚህ ጥቁር ቋጥኝ አይኑን አፍጥጦ “ልመጣ ነው” ይላል፡፡
ከእሱ ለመሸሽ አይንን ሰበር ቢያደርጉ ደሞ፣ በዚያ “ጭልጥ ያለ” ገደል “ልውጥህ ነው” እያለ አፉን እያዛጋ ይጠብቅዎታል፡፡

ቁልቁለቱን በምጥ ወርደው፣ የሸለቆው ወለል ላይ ሲደርሱ የአባይን ወንዝ ተሻግረው ሌላ ፈተና ይጀምራሉ – የአቀበት፡፡

እኛ ቁልቁለቱን እያገባደድን ነው፡፡
ድልድዩ ላይ ልንደርስ 500 ሜትሮች ያህል ይቀሩናል፡፡

ከግርጌያችን አባይ ብቅ አለ፡፡
አንዳንዶቹ የአባይን ወንዝ ፎቶ ሊያነሱ ካሜራዎቻቸውን አወጡ፡፡

ወደ ወንዙ አቅጣጫ በወደሯቸው ካሜራዎቻቸው ሌንስ ውስጥ ግን፣ “የደበዘዘ አባይ” ነበር የተመለከቱት፡፡

ጭስ ያጠየመው አባይ፡፡

በረሃው ውስጥ ደማቅ ጭስ ሽቅብ ይትጐለጐላል፡፡

ጭሱ የወትሮውን የአባይ በረሃ ከሰል አክሳዮች፣ የሳሳ የጉልጥምት ጭስ አይመስልም፡፡
ከጠባቧ ኩርባ በታች ካለው ገደል ውስጥ እየተጥመለመለ የሚወጣው ጭስ፣ የከሰል አይመስልም፡፡

የከሰል ጭስ እንዲህ ያለ ሽታ የለውም፡፡
የአክሳዩን አይን ቆጥቁጦ ትንሽ እንባ ቢያስነባ እንጂ፣ ይሄን አገር ሙሉ ሰው ዶፍ እንባ አያስለቅስም፡፡

አባይን ሊሻገር ጥቂት የቀረውም፣ አባይን ተሻግሮ ጥቂት የተጓዘውም…
ሂያጁም… መጪውም… ከመኪናው ወርዶ፣ እዚህ ገደል አፋፍ ላይ ተሰልፎ ቁልቁል እያየ የሚያለቅሰው፣ በከሰል ጭስ አይደለም፡፡

ሚኒባሱ ውስጥ የነበርን በሙሉ፣ በጥያቄ አይን ወደ ህዝቡ ተመለከትን፡፡

“ፎቶ ሊነሱ ይሆናል” አለ አንደኛው ከመካከላችን፡፡

ህዝቡ ከየመኪናው ወርዶ ከገደሉ አፋፍ የቆመበትን ምክንያት እየገመተ ነበር፡፡

እሱ ጥሩ ገማች አልነበረም፡፡
የእሱም…. የሌሎቻችንም ግምት ትክክለኛ አልነበረም፡፡

ሁላችንም ያልገመትነው ነገር ነው፣ ገደሉ ስርም ከገደሉ አፋፍም የሆነውና እየሆነ ያለው፡፡
ጭሱ ከሚቃጠል እንጨት የሚወጣ አልነበረም፡፡

በእሳት የሚለበለበው፣ ተንጨርጭሮ የሚቃጠለው፣ በረሃው ውስጥ የሚጨሰው እንጨት ሳይሆን አጥንት ነው፡፡

የበረሃው ንፋስ “እፍ” እያለ የሚያቀጣጥለው ፍም የሰው ስጋ ነው!…

አዎ!…

የገመትነው አይደለም የሆነውና እየሆነ ያለው፡፡

እኛም… ከገደሉ አፋፍ ቆሞ እሪታውን የሚያቀልጠው ህዝብም፤ ከገደሉ ስር ከፍም ተማግዶ በእሳት የሚጋየው ባለ መጥፎ ዕጣ መንገደኛም… ሁላችንም ይህ ይሆናል ብለን አልገመትንም፡፡

.

ከአዲስ አበባ ተነስቶ 47 ሰዎችን ጭኖ ወደ ጐንደር ጉዞ የጀመረው አውቶቡስ፣ መንገዱን ስቶ ገደል ገብቷል፡፡

ከገደሉ አፋፍ በግምት 80 ሜትር ያህል ወርዶ፣ ከአንዲት የበረሃ ዛፍ ስር ሰፊ ምድጃ ሰርቶ በእሳት ይጋያል፡፡

40 ሰው፣ መውጫ በሌለው እሳት ተማግዶ ይለበለባል፡፡

እጅግ አሰቃቂ ትዕይንት፡፡
ፍፁም ዘግናኝ ነገር፡፡

ከአውቶቡስ ሙሉ ሰው አምስት ያህሉ ብቻ፣ በአሰቃቂ ሁኔታ ቆስለው በህዝቡ ርዳታ ከገደሉ ወጥተዋል፡፡ ወደ ጐሃ ፅዮን ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡

ከሚኒባሳችን ወርደን ይህን ዘግናኝ ትዕይንት ቁልቁል እየተመለከትን፣ ዋይታውን ተቀላቀልነው፡፡

አውቶብሱ የብረት አፅሙ እስኪገጥ ተቃጥሏል፡፡
ውስጡ የነበሩ 40 ያህል መንገደኞች ወደ ፍምነት ተለውጠው ፀጥ ብለዋል፡፡

ከእነዚህ እሳት ከበላቸው መንገደኞች መካከል፣ ጭላጭ ትንፋሽ ያለው አንድ ሰው ብቻ ነው፡፡

ከገደሉ ስር በገበሬዎች እርዳታ ወጥቶ፣ በቃሬዛ ላይ ሆኖ ከእግር እስከ ራሱ በእሳት ተለብልቦ፣ በጣዕር ይቃትታል፡፡

የፖሊስ አባላትና ህዝቡ ተረባርቦ ከምድጃው ያወጣው ይህ ሰው፣ ቃሬዛው ላይ ተዘርሮ ኡኡ ይላል፡፡

“ውሃ… ውሃ… ውሃ ስጡኝ!…” ይላል፡፡

ህዝቡ በእንባ ይራጫል፡፡

“ከ… ከአውስትራሊያ ነው የመጣሁት… ለጥምቀት ወደ ጐንደር እየሄድኩ ነው…” እየቃተተ ይናገራል፡፡

ህዝቡ ወዬታውን ያስነካዋል፡፡

“በ… በ… በዚህ ስልክ ቁጥር ደውሉና… ለጴጥሮስ ንገሩልኝ…” አሁንም ይቃትታል፡፡

ህዝቡ ለዚህ ሰው ጥያቄ መልስ ከመስጠቱ በፊት… ስልኩ ከመደወሉ በፊት… ሰውዬው ራሱ፣ መልዕክቱን ሩቅ ወዳለው ወንድሙ “ይድረስ” ብሎ ተነፈሰ፡፡

“ቻ… ቻው ጴጥሮስ!… በቃ… አልተገናኘንም!…”

ይህ የሰውዬው የመጨረሻ ቃል ነው፡፡

በዚህች ቅፅበት ፍም የነበረ አካላቱ፣ ወደ በረዶነት ተቀየረ፡፡
.

ይነድዳል!…
ይሄው ሸለቆ ስር ድንገት የተጫረው
እሳቱ ይነድዳል…
አጥንት እንደ ጉልጥምት በገፍ ተቆስቁሶ
ከእሳት ይማገዳል
ይከስላል ያምዳል!…
.
ይጨሳል!…
ከበረሃው ግርጌ ምድጃ ላይ ወድቆ
አርባ ሰው ይጨሳል
በእቶን ይጠበሳል…
ከሸለቆው መሃል ያርባ ሰው ብዙ ህልም
ጭስ ሆኖ ይነሳል
በንፋስ ይሳሳል!…
መንገዱን የሳተ እሳት የበላው ህልም
ጉም ሆኖ ይተናል
ሽቅብ ይበተናል!…
.
ያፈስሳል!…
ወገን ሲለበለብ ሲቃጠል እያየ
እንባውን ያፈስሳል
ቋሚ ካፋፍ ሆኖ እሳት ስለበላው
ስለ ሟች ያለቅሳል!…
.
ይፈስሳል!…
“ውሃ ጠማኝ” ሲለው ወገን ከሳት ወድቆ
መቼ ይመልሳል
አባይ አባ ጨካኝ ጥርኝ ውሃ ነፍጎ
ዝም ብሎ ይፈሳል!…
ከውሃ ዳር ወድቆ ወገን ውሃ ናፍቆት
እየተወራጨ
በፍም ይጠበሳል
አባይ ውሃ ሙላት ሰው ከሚከስልበት
ከምድጃው ግርጌ
የራሱን ይፈስሳል!…
.
.

አሰቃቂው ትዕይንት ቀጥሏል፡፡

ሊያዩት የሚያሳቅቅ “ትራጄዲ” በረሃው ውስጥ እየተከናወነ ነው፡፡
አውቶቡሱ ምድጃ ሆኖ ከገደል ስር የአጥንት ፍም ታቅፏል፡፡

የበረሃው ንፋስ “እፍ” እያለ የሚያግለበልበው ፍም፣ የእሳት አለንጋ ፈትሎ ዙሪያውን ይወነጨፋል፡፡
ነበልባሉ ይጋረፋል፡፡

ወገነኑን ከምድጃ ነጥቆ ለማትረፍ ከአፋፍ ወደ ገደሉ የወረደውን ሁሉ፣ “እንዳትጠጉኝ” እያለ ያስፈራራል፡፡

እሳቱ ይነድዳል…
.

እኛ ግን ጉዟችንን ልንቀጠል ነው…

እንዲህ ዘግናኝ ነገር ታክሎበት ይቅርና፣ አባይ በረሃ ድሮም በፍርሃትና በጭንቀት የሚያርድ ቦታ ነው፡፡

እንኳን እሳት ነዶበት፣ ድሮም አባይ ቋያ ነው፡፡

ተፈጥሮ ከጐሃጽዮን ጓሮ እስከ ደጀን ደጃፍ አጥልቃ የማሰችው፣ ጭው ያለ ገደል ነው – አባይ በረሃ!

እኛ ደግሞ…
እዚህ አስፈሪ ገደል ውስጥ አሰቃቂ ነገር የገጠመን መንገደኞች ነን – የፈራን መንገደኞች፡፡

ገደሉ ስር አመድ ሆነው የቀሩ 40 መንገደኞች ዕጣ እንዳይደርሰን የሰጋን መንገደኞች ነን፡፡
ስለሞታቸው ስናነባ ቆይተን፣ ስለሞታችን ማሰብ የጀመርን፡፡

ከግርጌያችን በአባይ ወንዝ ላይ የተዘረጋውን ዘመናዊ ድልድይ በጥርጣሬ የምናይ፣ አባይን ተሻጋሪ፣ እስከ ደጀን አፋፍ ያለው ጠመዝማዛ የአቀበት መንገድ የሚጠብቀን መንገደኞች ነን፡፡

የበረሃው ወለል ስር እየተጠማዘዘ ቁልቁል የሚፈሰውን አባይ አሻግሬ እመለከተዋለሁ፡፡

አባይን ፈራሁት፡፡

ክቡር ዶ/ር ሐዲስ አለማየሁ፣ በፍቅር እስከመቃብር እንዲህ ሲሉ የገለፁትን አባይ…

“…አባይ በረሃ የሲኦልን ግርማ ተጐናጥፎ እስሩ የአባይ ወንዝ የአናቱና የጅራቱ መጨረሻ እንደማይታይ ዘንዶ ተጋድሞ…”

አባይን ፈራሁት፡፡
አሻግሮ የሚወስደውን መንገድ ተጠራጠርኩት፡፡
ልቤ መፍራት ጀምሯል፡፡
በወገኖቼ የደረሰ መከራ፣ እነሱን ጨርሶ ወደ እኔ ስላለመሻገሩ በምን እርግጠኛ መሆን እችላለሁ?…

“…አባይ ለቆላው የመኪና መንገድ፣ ለወንዙ ድልድይ ሳይሰራለት ከጐጃም ወደ አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ ወደ ጐጃም የሚሄድ መንገደኛ ሁሉ ጐሃጽዮን ወይም ደጀን እስኪደርስ ድረስ ልክ የመከራ ትንቢት እንደተነገረበት ሰው ከአሁን አሁን መከራው ደረሰብኝ ብሎ ልቡ እየፈራና እየራደ የሚያልፍበት ቦታ ነበር፡፡…” ብለዋል ደራሲው፡፡

“ነበር” ባሉት አልስማማም፡፡
አባይ አሁንም እሳቸው እንዳሉት ሆኖብኛል፡፡
እሳቸው ያሉት የቀድሞው ድልድይ ከተሰራ በኋላ ነው፡፡

የ”ህዳሴው” ድልድይ ከጐኑ ከተነጠፈ በኋላ፣ ኮረኮንቹ በጃፓን እጅ አስፓልት ከለበሰ በኋላ… ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላም… አሁንም አባይ እንደዛው ነው – ለእኔ!…

ድልድዩን አልፌ፣ ዳገቱን ተሻግሬ፣ አፋፍ እስክወጣ… ደጀን እስክደርስ… እኔ፣ የመከራ ትንቢት እንደተነገረበት ሰው ነኝ፡፡

“ከአሁን አሁን መከራው ደረሰብኝ” ብሎ ልቡ እየፈራና እየራደ ቀጣይ ጉዞውን ሊጀምር፣ ወደ ሚኒባሱ ገብቶ የተቀመጠ ፈሪ መንገደኛ ነኝ እኔ፡፡
.

ዝም ሚኒባሷ…
12 ጋዜጠኞችን ይዛ ከአዲስ አበባ የተነሳችው ነጯ ሚኒባስ …
ከፊቷ የነበረው አውቶቡስ የሄደበትን የገደል መንገድ በፍርሃት እያየች ዳር ይዛ ቆማ የቆየች ሚኒባስ…
አስራ ሁለት ጋዜጠኞችን መልሳ የጫነች የእኛ ሚኒባስ፣ እንደገና ጉዞ ጀምራለች፡፡

አስራ ሁለት ዝምታ ጭና ቁልቁል በቀስታ ትጓዛለች፡፡
ሚኒባሷ ውስጥ ነን፡፡
የየግል ዝምታ ሆነን፡፡
የየራስ ፍርሃት፡፡
የየራስ ስጋት፡፡
የየራስ ጭንቀት ሆነን!…

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ማህበራዊ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top