Connect with us

የጠ/ሚ ዐብይ አህመድ መልዕክት:-

የጠ/ሚ ዐብይ አህመድ መልዕክት:-
Photo: Social media

ማህበራዊ

የጠ/ሚ ዐብይ አህመድ መልዕክት:-

የጠ/ሚ ዐብይ አህመድ መልዕክት:-

እንኳን ለ1496 ኛው የመውሊድ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!!

መውሊድ አላህ በነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በኩል ለዓለም የሰጠውን በረከት የምናስብበት በዓል ነው። አንድን ነገር የምንጠብቀው፤ ጠብቀንም የምንጠቀምበት ምን እንዳገኘንና እንዴት እንዳገኘን በሚገባ ካወቅነው ብቻ ነው። ያገኘውን በትክክል ያላወቀ ሰው አዲስ ነገር ለማግኘት ሲል ያለውን ነገር ሲጥል ይኖራል።

የመውሊድ በዓል ፈጣሪ ለሰው ልጆች ምን ሰጠን? ፈጣሪስ ከሰው ልጆች ምን ይፈልጋል? የሚለውን የምናስታውስበት፤ ይሄንንም በልዩ ልዩ መንገድ የምንገልጥበት በዓል ነው። ፈጣሪ ማንም ከማይተካት ነፍስ ጀምሮ ለሰው ልጆች ብዙ ነገር ሰጥቷል። የፈጣሪን ስጦታ ከመዘርዘር ይልቅ አለመዘርዘሩ ይመረጣል። የትየለሌ ነውና። ይህ ስጦታ ግን ተሰጥቶ ብቻ የሚቀር አይደለም። የሰው ልጅም ለፈጣሪው የሚያደርገው ነገር አለ። እምነት ባለ ሁለት መንገድ በመሆኑ። ፍጡር ወደ ፈጣሪ – ፈጣሪ ወደ ፍጡር።

የመውሊድን በዓል ስናከብር የሰው ልጆች ለሌሎች የሰው ልጆች እያደረጉ ያሉትን እዝነት ማስታወስ አለብን። ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ያደረጉት ነገር ሁሉ ሌሎችን የሰው ልጆች ነጻ የሚያወጣ፣ የሚለውጥና ወደተሻለ ሕይወት የሚመራ ነው። ነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) በዚህ ዕለት የምናስታውሳቸው ከአላህ ተልከው ለሰው ልጆች በፈጸሙት መልካም የመልእክተኛነት አገልግሎታቸው ነው።

ሰው በምድር ላይ የሚፈለገውም፣ የሚታወሰውም በመልካም አገልግሎቱ ነው። የሰው ልጅ መልካም አገልግሎት ደግሞ መለኪያው ለሌሎች በተከፈለው የመሥዋዕትነት መጠን ነው። አገልግሎት ለራስ የሚሰጥ ስጦታ አይደለም። መሥዋዕትነት ተከፍሎም ቢሆን ለሌሎች የሚደረግ ነው። ሌሎችን ለመለወጥ፣ የሌሎችን ሕይወት ለማሻሻል፣ ሌሎችን ነጻ ለማውጣት የሚከፈል መሥዋዕትነት ነው።

መውሊድን የምናከብርበት ይህ ጊዜ የመውሊድን ዕሴቶች በእጅጉ የሚፈልግበት ጊዜ ነው። ለሌሎች የሚደረግን መልካም አገልግሎት ሀገራችን ትፈልጋለች። ወገኖቻችንን ነጻ ለማውጣት የሚከፈልን መሥዋዕትነት፣ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ለመርዳትና ለማቋቋም የሚደረግን መሥዋዕትነት፣ ሀገራችን በርሀብ እንዳትጠቃ በየማሳው የሚደረግን መሥዋዕትነት፣ መልካም አገልግሎት ለሕዝቡ ለመስጠት በየቢሮው የሚደረግን መሥዋዕትነት፣ ሀገራችን በእጅጉ ትፈልጋለች።

መውሊድ የነቢዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) መልካም አገልግሎት የምናስታውስበት ነው። ለሌሎች የተደረገና የተከፈለ መልካም አገልግሎት። ታሪክንና ማኅበረሰብን የለወጠ መልካም አገልግሎት። የሕዝብን አኗኗርና አስተሳሰብ የለወጠ መልካም አገልግሎት ይታሰብበታል። አዲሱን መንግሥት በድምፁ ያመጣው ሕዝብና አዲሱን አስተዳደር የመሠረተው መንግሥት እነዚህ ነገሮች በእጅጉ ያስፈልጓቸዋል። ታሪክንና ማኅበረሰብን የሚለውጡ አገልግሎቶች። የሕዝብን አኗኗርና አስተሳሰብ የሚለውጡ አገልግሎቶች ያስፈልጉናል።

ሀገራችን የገጠማትን ሦስት ፈተናዎች በቶሎ ፈትተን ወደምንፈልገው የብልጽግና ምእራፍ ለመድረስ ቁልፉ በመሥዋዕትነት የታሸ መልካም አገልግሎትን ዛሬውኑ ለመስጠት መቻል ነው። የሀገራችንን የውስጥ ጠላቶች በፍጥነት አሸንፈን የኢትዮጵያን ኃያልነት ማስፈን አለብን። በዲፕሎማሲው ረገድ የገጠመንን ፈተና እውነትንና ጥበብን ይዘን ማሸነፍ አለብን። የሕዝባችንን የኑሮ ውድነት በላቀ የአመራር ክሂሎት መጀመሪያ ማሻሻል፣ ቀጥሎም መቅረፍ አለብን።

እነዚህን ሦስት ፈተናዎች በድል ለመወጣት ሲቪሉም ሆነ ወታደሩ መሥዋዕትነት ያለበትን መልካም አገልግሎት መስጠት አለበት። ፈተናችን ሁለንተናዊ ነው። አገልግሎታችንም ሁለንተናዊ መሆን አለበት። እንዲሁ የሚተው ሽንቁር መኖር የለበትም። ይሄኛው አይጎዳንም፤ ይሄኛው ምንም አያመጣም፤ ይሄኛው የነ እንትና ነው፤ ይሄኛው ያልቅስ፣ ያኛው ይሙት፤ ያኛው ይፍረስ፣ ይሄኛው ይለቅ፣ ተብሎ የሚተው የሀገር ችግር መኖር የለበትም።

 ሁለንተናዊ ሰላምና ብልጽግና የሚመጣው ሁሉንም ዓይነት ፈተናዎች እንደየመልካቸው በማሸነፍ ነው። አንዲት ትንሽ የሰውነት አካል እስከታመመች ደረስ ጤነኛ ሰው መሆን አይቻልም።

ሦስቱን ፈተናዎች ከመፍታት አንጻር ሦስቱ መንገዶች እንደየሁኔታው ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው። ጦርነቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በድል ማጠናቀቅ፤ ይቅርታንና አሳታፊ ውይይቶችን ማካሄድ፤ የኢኮኖሚ ፈተናዎቻችንን የሚፈቱ የማክሮና የማይክሮ ኢኮኖሚ ውሳኔዎችን ማሳለፍ። ለየትኛው ፈተና በመቼ ጊዜ የትኛውን መፍትሔ እንጠቀም? የሚለውን አመራሩ በላቀ ጥበብና ክሂሎት ከፍጥነት ጋር ተግባራዊ ማድረግ አለበት። ሕዝቡም ከችግሩ ጋር ሳይሆን ከመፍትሔው ጋር መቆም ይገባዋል።

ኢትዮጵያ በፈተና ብቻ የተከበበች አይደለችም። ኢትዮጵያ በተስፋም ብቻ የታጀበች አይደለችም። የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ በእነዚህ ሁለቱ ዕድሎች የሚወሰንም አይደለም። የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው እኛ ከሁለቱ ለየትኛው እየሠራን ነው? በሚለው ነው። ለተስፋዋ ከሠራን ተስፋዋ ያሸንፋል። ለፈተናዋ ከሠራን ፈተናዋ ይበረታል። ‹ብርሃን የሚመጣው ተሠርቶ ነው፤ ጨለማ ግን ብርሃን ባለመኖሩ ብቻ ሊመጣ ይችላል› ይባላል። ብርሃን የሥራ ጨለማ የስንፍና ውጤት ነው። ተስፋ የሚገኘው በሥራ ነው። ፈተና ግን ተስፋ ባለመኖሩ ብቻ ሊመጣ ይችላል። ተስፋ የሥራ፣ ፈተና ግን የስንፍና ውጤት ሊሆን ይችላል።

የምናስበው፣ የምናወራውና የምንሠራው በተስፋችን ላይ ከሆነ ተስፋው ዕውን ሆኖ የምናይበት ጊዜ ቅርብ ነው። የምናስበው፣ የምናወራውና የምንሠራው ስለ ፈተናችን ከሆነ ግን ፈተናችንን ጥልቅና ሩቅ ያደርገዋል። በመንገድ ላይ ስለገጠመው ነፋስና ፀሐይ የሚጨነቅ ሯጭ፣ ወደ ሜዳልያው የሚቀርብበትን ሰዓት ያስረዝመዋል። ወደ ሜዳልያው መቅረቡን እያሰበ የሚሮጥ ሯጭ ግን፣ የገጠመውን ነፋስና ፀሐይ የሚቋቋምበት ዐቅም ከውስጡ ያገኛል።

የዛሬውን የመውሊድ በዓል ስናከብር ‹በመሥዋዕትነት የታጀበ፤ ሕዝብን ሊለውጥ የሚችል መልካም አገልግሎት መስጠት› የሚለውን የመውሊድ ዋናውን ዕሴት በማሰብ እንዲሆን በድጋሚ ለማስታወስ እወዳለሁ። ይሄንን ዕሴት ሀገራችን ዛሬ በእጅጉ እንደምትፈልገውም ለማስታወስ እፈልጋለሁ።

በድጋሚ ለመላው ሕዝበ ሙስሊም፣ መልካም የመውሊድ በዓል ይሁን!!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

 

Click to comment

More in ማህበራዊ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top