Connect with us

ነጭ ሳር ሜዳው ላይ፤  ሙሽራዋ አርባ ምንጭ

ነጭ ሳር ሜዳው ላይ፤

መዝናኛ

ነጭ ሳር ሜዳው ላይ፤  ሙሽራዋ አርባ ምንጭ

ነጭ ሳር ሜዳው ላይ፤  ሙሽራዋ አርባ ምንጭ፡፡
****
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ወደ ዜብራዎቹ መኖሪያ ወደ ነጭ ሳር ሜዳ ተጉዞ ነበር፡፡ ነጭ ሳር ሜዳው ላይ ሲል የእግዜር ድልድይ ማዶ ሆኖ የተመለከተውን እንዲህ ያጋራናል፡፡) | ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

አርባ ምንጭን ከሩቅ አየኋት፡፡ ሙሽራዋ ከተማ የሰርጓ ዋዜማ ላይ ያለች ትመስላለች፡፡ ጫሞ እንደ ምንጣፍ አባያ እንደ እንደ ቄጤማ የተነጠፈላት፡፡ ያለሁት ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ነው፡፡

ሜዳው ላይ ነኝ፡፡ የአማሮ ተራሮች እንደ ገጠር ጎረምሳ አናታቸው አጎፍሯል፡፡ ጎፈሬው የጥድ ዛፍ ነው፡፡ ወዲያ የጉጂን ምድር አድማስ ተዘርግቶበታል፡፡ ዓይንን ልኮ የሚያርፍበት አጣ ከማይባልበት አምባ ቆሜያለሁ፡፡ የተዘረጋው የነጭ ሳር ሜዳ ስሬ ተጋድሟል፡፡ ይህ የሀገሬ ዜብራዎች መፈንጫ ነው፡፡ ከነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ከግማሽ የሚበልጠው ክፍል ይህ የነጩ ሳር ሜዳ ነው፡፡

ሜዳው የሜዳ አህያ ብቻ አይደለም፡፡ የሜዳ ፍየሏም ሜዳውን ትጋልብበታለች፡፡ ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ በጎብኚዎች ቁጥር ቀዳሚ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፓርክ እየሆነ ነው፡፡ ደቡብ እና ኦሮሚያ ላይ ያረፈው ይህ ፓርክ የአርባ ምንጭ ከተማ የውበትም የህይወትም መሰረት ሆኗል፡፡

ጫሞ ዝም ብሏል፡፡ የጋንጁሌ ደሴት ሐይቁ ገላ ላይ የሚንሳፈፍ መርከብ መስሎ ይታያል፡፡ የሁሉ ውበት ግን እንደ ሳሩና እንደ ዜብራው ቀለም አልተመሳጠረም፡፡ ነጭ ሳር የስሙ መጠሪያ ይህ ገጽታው ነው፡፡ ገና አልነጣም፤ አረንጓዴው ሳር ዥጉርጉር አህዮች ዓለማቸውን ይቀጩበታል፡፡

ነጭ ሳር ትንሽ ቢመስልም ትልቅ ነው፡፡ አንድ ብሔራዊ ፓርክ አምስት ሥርዓተ ምህዳር፡፡ 514 ኪሎ ሜትር ስኩዬር በሚሰፋው ፓርክ የተንዠረገጉ ደኖች፣ የተፈጥሮ ምንጮች፣ ኮረብታዎች፣ የሐይቅ ዳርቻዎችና ሳራማ ሜዳዎችን ይዟል፡፡

የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ የግዛቱ አምባ ከባህር ጠለል በላይ 1625 ሜትር ከፍታ አለው፡፡ ያለሁት ከፍ ከሚሉት የፓርኩ ስፍራዎች በአንዱ ነው፡፡ ሩቅ ድረስ ውበት የሚታይበት፡፡ ዓይኔ ከአርባ ምንጭ ዓይኖች ጋር ተገናኘ፡፡ ይህቺን ሙሽራ ከተማ በዓይን ብቻ አናገርኳት፡፡ ሊያውም የተዘረጋው ጫሞ ሳያግደኝ፡፡

የእግዜር ድልድይ አባያና ጫሞን ለይቷቸዋል፡፡ ይህ የተፈጥሮ አምባ ነጭ ሳርን የሁለት ሐይቆች ባለ ጸጋ አድርጎታል፡፡
ደኑ ታየኝ፡፡ እዚያ ደን ውስጥ የማይጠገብ ህይወት አለ፡፡ የተፈጥሮ መዋኛ፡፡ አርባ ምንጭን የተሸከመ ግዝፈት፡፡ ምድርን የዱር አዳራሾች ያጎናጸፈ ውበት፡፡ ጫሞን ልጋልብበት ነው፡፡ ሜዳውን ትቼ ቁልቁለቱን ወረድሁ፡፡

Click to comment

More in መዝናኛ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top