የተንታኝ ግሽበት የተግባሪ እጥረት ያየንበት ኮሮና
የለአንዱ ጥንቃቄ ሁላችንም በማንድንበት ወረርሺኝ የግለሰብ ግዴለሽነት የሀገር ክህደት ወንጀል ነው፡፡
****
ከሄኖክ ስዩም
እንደ ዓለም ጎዳናዎች ጎዳናችን ጭር አላለም፤ እንደ ሌላው ሀገር ቀብር አላጣደፈንም፡፡ ሌላው ሀገር ዛሬ እንዲህ ከመኾኑ በፊት ችግሩ ዜናው ነበር፡፡ እኔ የበሽታውን ሁኔታ አልዘረዝርም፤ ሁሉም ሰው በቅጡም ያለ ቅጡም ዘርዝሮታል፡፡ በኮሮና የታዘብኩት አንድ ነገር በኢትዮጵያ ተንታኝ መጋሸቡን ነው፡፡ በታፈነ ጠባብ ኢንተርኔት ቤት ሆኖ ስለ መራራቅ የሚጽፍ ዜጋ ባለባት ሀገር እኖራለሁ፡፡
ከፍተኛ ሹማምንቶ ተጠጋግተው መራራቅን እየሰበኩን ምን ሊገባን እንደሚችል አላውቅም፡፡ ሁሉም ሰው ሁሉም ነገር ላይ ጠቢብ በሆነባት የኔ ሀገር ዛሬም ግን እጅ መታጠብ የሚቀሰቀስ ተግባር ነው፡፡ ተግባሪው የለም እንጂ ተንታኙ ብዙ ነው፡፡ የተንታኝ ግሽበት ያየንበት ኮሮና፤
አንድ ሰው ግድ የለሽ ቢሆን የሁላችን ጥንቃቄ አያድነንም፤ ሁላችንም መዳን የምንችለው ሁላችንም ንቁ ስንሆን ነው፡፡ የድርሻችንን የምንወጣው ለራሳችን ብለን አይደለም፤ ለሀገር ነው፡፡ ከእያንዳንዱ ሰው ጥንቃቄ ጀርባ ሀገርን ከማጥ የማውጣት ተግባር አለ፡፡
እንዲህ ባለው አጣብቂኝ ወቅት ልዩነት ሀገር ያጠፋል፤ ምን አገባኝ ባይነት ጦሱ ከራስና ከቤተሰብ የሚያልፍ ነው፡፡ መንግስትና ህዝብ እንዲህ ባለው የጭንቅ ሰዓት ግዴለሹን መመልከት ያለባቸው እንደ ሀገር ከሃዲ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ግዴለሽነት የሀገር ክህደት ወንጀል ነው፡፡
አዲስ አበባ ታክሲ ትርፍ ከጫነ አንድ ሺህ ብር ይቀጣል ተብሎ ተነግሮናል፡፡ ይሄንን ራሱ የሰማነው በታጨቀ ታክሲ እየሄድን ነው፡፡ አሁንም ጥንቃቄዎች ያሹናል፡፡ አሁንም አካባቢያችንን በተለየ ዓይን መመልከት አለብን፤
በእኔ እምነት የዜጋችን ብዙ እጥፉ በዕለት ገቢ የሚኖር ሆኖ ሳለ እንደ ሞላለት ሰው እቤት መዋልን ብቻ ብንሰብክ አንዱንም አናሳካውም፡፡ ይልቁንም አስቸኳይ ስራ የሌላቸው በቤታቸው ሆነው ስራቸውን መስራት የሚችሉ ስራቸው በቴክኖሎጂ መቅለል የሚችል ወገኖች ከብዙውን ሰዓት እቤት የማሳለፍ ሥርዓት እንዲከተሉ ማድረጉ አዋጪ ነው፡፡
ትምህርት ቤት ዘግተን ፑል ቤት በሚውሉት ልጆቻችን በሽታውን እንቆጣጠረዋለን ማለት ሞኝነት ነው፡፡ የገበያ ቦታዎች መተፋፋግ አሁንም ቀጥሏል፡፡ የባንክ ኤቲኤም ማሽኖች ከወትሮው በተለየ መልኩ ያለ ችግር እንዲሰሩ ማድረግ ይገባል፡፡ የባንክ ውስጥ መጨናነቅ ግን አሁንም ያው ነው፡፡
የሚሆነው ነገር እንደማይበጀን እያየን መሳቁ አብሮ ከማልቀስ በቀር የሚያመጣልን ትርፍ የለም፤ ድሮም ሀበሻ ብሎ መቀለድ ከሀበሻ ጋር አብሮ ይጎዳን እንደሁ እንጂ እኛ የነቃን ስለሆንን የምናመልጠው መከራ የለም፡፡ የገባው ያልገባውን ሳይንቅ ሁላችንም አንድ ነገር እንዲገባን መፍትሔው መተግባር ነው፡፡ ማውቅ ብቻውን ከንቱ ነውና፤