ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ
ከአክመል ነጋሽ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኮኖሚስትነትን ከነጋዴና ቢዝነስ-ማን ጋር አምታተው ማቅረባቸው ስህተት ነው ወይስ ኾነ ብለው ያደረጉት ነው ለሚለው መልስ የለኝም፡፡ አንድ በኢኮኖሚክስ ፒ.ኤች.ዲ ያለው ምሁር ኢትዮጵያ ውስጥም ኾነ ሌላ ሀገር በተማረበት ሞያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያስተምራል፣ የምርምር ጽሑፍ ያዘጋጃል፣ የፖሊሲ ማማከር ወዘተ ሥራ ይሠራል እንጂ እንደ ‹‹ሳሚ ሰንሻይን›› ኮንዶ ሠርቶ አይሸጥም፣ እንደ አብነት ሆቴል ገንብቶ አያከራይም፡፡ ነጋዴም የራሱ ሥራ አለው፣ ምሁርም የራሱ ሥራ አለው፡፡ የአንድ ኢኮኖሚስት ስኬት የሚለካው በገዛው መኪና ወይም ባለው ሀብት መጠን ሳይኾን በሠራው ጥናትና ባስመዘገበው አዲስ የዘርፉ ግኝት ወይም መፍትሔ ነው፡፡
አንድ የኢኮኖሚክስ ፒ.ኤች.ዲ ያለው ጓደኛዬ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች በአንዱ በትልቁ ያስተምራል፡፡ ደሞዙ ግን 12 ሺህ ብርም አይሞላም፡፡ የእርሶ መንግሥት የሚሰጠው ደሞዝ ለቤት ኪራይ እንኳ የሚኾን አይደለም እንኳን ለመኪና፡፡ በእርግጥ ይኼ ጓደኛዬ ትምህርቱን ትቶ የኦሕዴድ ካድሬ ቢኾን ኖሮ ስንት መሬት አየር ላይ ቸብችቦ ቢጠሩት የማይሰማ ሀብታም ይኾን ነበር፡፡ ለአንድ ኢኮኖሚስት መጠየቅ ያለቦት ጥያቄ ስንት ጥናት ሠርተሀል? ስንት ተማሪ ለስኬት አብቅተሀል? ብለው ነው፡፡ ስንት መኪና አለህ ብለው መጠየቅ ያለቦት የኦሕዴድ ካድሬዎችን ይመስለኛል፡፡ ሁሉንም በየሞያው እንጂ፡፡
በእርሶ አመክንዮ
.
.
.
ሼክስፒር የሮሚዮን ዓይነት ጣፋጭ ፍቅር ካላሳለፍ ምኑን ደራሲ ኾነው፣
የባንክ አካውንታንት በየቀኑ የሚቆጥረው ብር የእሱ ካልኾነ ምኑን አካውንታንት ኾነ፣
ሐኪም በሽታ ከያዘው ምኑን ሐኪም ኾነ ወዘተ ዓይነት ኾኖብኛል ንግግርዎ፡፡
.
.
.
.
የፖለቲካ ሳይንሱም በተመሳሳይ መልኩ ነው የሚታየው፡፡
.
ክቡር ጠ/ሚኒስትር የኢኮኖሚስት ሥራ የባለ-ሀብት ባዮግራፊ መጻፍ አይደለም፣
ክቡር ጠ/ሚኒስትር የፖለቲካ ሳይንስ ባለሞያ ሥራ የፖለቲከኛ ባዮግራፊ (የእርሶን ባዮግራፊ የጻፈው ጋዜጠኛ ነው) መጻፍ አይደለም፣
ክቡር ጠ/ሚኒስትር ቢልጌትስና ዙከርበርግ የፊደል ሽፍታ የሚባሉ ሰዎች አይደሉም፣
አልጨረስኩም ግን ጨርሻለሁ፡፡
***
ከአዘጋጁ
ጠ/ሚ ዓብይ አሕመድ ምንድነው ያሉት?
ጠቅላይ አብይ አህመድ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ዕለት ምሽት በሚሊኒየም አዳራሽ በነበረውና ከአንድ ቢልየን ተኩል በላይ ብር በተሰበሰበበት የብልጽግና ፓርቲ የገንዘብ መዋጮ ስብሰባ ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ንግግር ….አብዛኞቹ የሀገራችንም ሆኑ የአፍሪካ ምሁራን በግርድፉ ያገኙትን እውቀት በመጻፍና በመተረክ ብቻ ነው ፒ.ኤችዲ ያገኙት። ብዙዎቹ የፖለቲካ ሳይንቲስት ነኝ የሚሉ አካላት አንዲት ትንሽዬ ቀበሌ እንኳ አስተዳድረው አያውቁም በማለት የምሁራን ሚና አናሳ መሆን አስረድተዋል።
ይህ ንግግር በተለይ በማህበራዊ ሚድያ የድጋፍም የተቃውሞ ሀሳቦችን እያስተናገደ ይገኛል።