ከወደ ናይጄሪያ የተሰማ የአንድ ስኬ ታማ ግለሰብን ታሪክ ልናስነብባችሁ ወደናል። ኢንተለጀንስ ዶት ኮም እንዳስነበበው ግለሰቡ አብራሪ የመሆን ህልሙን የጀመረው ከአውሮፕላን የፅዳት ሰራተኝነት ተነስቶ ሲሆን አሁን ላይ የንግድ አውሮፕላን አብራሪ ለመሆን በቅቷል። የዚህ ስኬታማ ሰው አጭር የስኬት ታሪክ እንደሚከተለው ነው።
ናይጀሪያዊው መሀመድ አቡበከር ከዛሬ 24 አመታት በፊት የአውሮፕላን ፅዳት ሰራተኛ ሆኖ ነበር ካቡ ኤር በተባለ ኩባንያ የተቀጠረው። በካዱና ፖሊ ቴክኒክ ለመማር አመልክቶ የትምህርት ማስረጃዎቹን በጊዜው ባለማስገባቱ ተቀባይነት ሳያገኝ የቀረው መሀመድ ምንም እንኳን የስራ ምርጫው ባይሆንም ለረጅም ጊዜ ያለስራ መቀመጥን ባለመምረጥ ነበር በካቡ ኤር ውስጥ ለመቀጠር የወሰነውና በአውሮፕላን የፅዳት ሰራተኝነት ስራ የጀመረው።
የመሀመድ ደመወዝ እጅግ ዝቅተኛ ማለትም በቀን 200 የናይጀሪያ ናይራ ወይም 0.5 የአሜሪካን ዶላር በመሆኑ ማንም ሰው በስራው ላይ ይቆያል ብሎ አልገመተም ነበር፤ ነገር ግን ይህ ባለሩቅ ተስፋ ሀልመኛ ወጣት በስራው በመግፋት ብቻም ሳይሆን ውጤታማ ሰራተኛ በመሆን ከጊዜ ቆይታ በኋላ በሜዱግሪ ኤር በግራውንድ ስታፍነት ተቀጠረ።
ራሱን በዲሲፕሊን የታነፀና ውጤታማ ሰራተኛ ያደረገው መሀመድ በአቪየሽን ዘርፍ በርካታ እውቀቶችን እንዲያካብት አስቻለው። በቀጣይም መሀመድ በካቦ ኤር የበረራ አባልነት ላይ የማመልከት እድል አግኝቶ ስራውን መስራት ጀመረ። በዚህ ስራም ስምንት አመታትን በወር 17 ሺህ ናይራ ወይም 47 የአሜሪካን ዶላር እየተከፈለው ሰራ። ከዚህ በኋላም በበረራ ተቆጣጣሪነት ወደ ኤሮ ኮንትራክተርስ ተዛወረ።
የስራ ታታሪነቱና ፈጣን አዕምሮው በድርጅቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ትኩረትን መሳብ የቻለው መሀመድ ወርሀዊ ደመወዙ በወር ወደ 170 ሺህ ናይራ ወይም 469 የአሜሪካን ዶላር ከፍ አለ። ይህንን ማመን ያቃተው መሀመድ የመጀመሪያ የደመወዝ ክፍያ ቼኩን ሲቀበል ገንዘቡን ለመመለስ ሞክሮ እንደነበር ተገልጿል።
የሚያገኘውን ደመወዝ በዋዛ ፈዛዛ ማጥፋት ያልፈለገው መሀመድ ቁጠባ በመጀመር አብራሪ የመሆን ህልሙን እውን ለማድረግ ጉዳዩን ለዋና ዳይሬክተሩ አስረዳ፤ ዳይሬክተሩም የመሀመድን ሃሳብ በመደገፍ ድጋፍ ተደርጎለት በካናዳ የግል አብራሪነት ፈቃድ ለማግኘት ትምህርቱን ጀምሮ በስኬት አጠናቀቀ።
መሀመድ ወደ ናይጀሪያ ከተመለሰ በኋላ የንግድ አብራሪነት ፈቃድ መያዝ ቢፈልግም በቂ ገንዘብ ስላልነበረው ይህንን ማሳካት አልቻለም፤ ይሁን እንጂ ችግሩ ይህንን ህልሙን እና ጠንካራ መንፈሱን ሳይጎትተው ወደ ፊት በመገስገስ የድርጅቱን ም/ዋና ዳይሬክተር ድጋፍ በመጠየቅ ታማኝነቱና ስራ ወዳድነቱ በኩባንያው ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግለት ረዳው።
ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ካናዳ በመሄድ የንግድ አውሮፕላን አብራሪነት ስልጠናውን አጠናቆ ወደ ትውልድ ሀገሩ ናይጀሪያ ተመለሰ። ከ24 አመታት ጠንካራና ውጤታማ የስራ ጊዜያት በኋላ መሀመድ በአዝማን ኤር ውስጥ የአውሮፕላን አብራሪ ሆኖ በመቀጠር ህልሙን እውን አደረገ። አሁን መሀመድ በዚህ አየር መንገድ ውስጥ በአብራሪነት ስራውን እየሰራ ይገኛል፡