#የቅዱስ_ሲኖዶስ መግለጫ
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ፀረ ሕዳሴ ግድብ ንግግር፣ “የጦርነት ጥሪ” በማለት አጥብቆ የተቃወመው ቅዱስ ሲኖዶስ፥ መንግሥት፣ ፖሊቲከኞች እና ኢትዮጵያውያን በሙሉ በአንድነት ለአገራቸው ህልውና እንዲቆሙ ጥሪ አቀረበ።
(የመግለጫውን ሙሉ ቃል ይመልከቱ)
ታላቁን የሕዳሴ ግድብ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
በአገራችን ኢትዮጵያ የሕዝባችን የዘመናት ድህነትና የኑሮ ጉስቁልና አስወግዶ ለአገራችንም ብልጽግና ሆነ ለሕዝባችን ዕድገት ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሥራው ተጀምሮ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ መድረሱ ከዚያም በላይ ከሦስት ወራት በፊት በግድቡ የመጀመሪያ ሙሌት ተደርጐ ለሕዝባችን የብስራት ድምጽ መሰማቱ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ደስታቸውን መግለጻቸው ይታወቃል፡፡
በቀጣይም የግድቡ የዕለት ከዕለት ሥራ እየተከናወነ ሕዝባችንም የተለመደ ድጋፉን እያደረገ ከሦስት ዓመታት በኋላ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚደርስ ተስፋ የተጣለበት መሆኑ ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ ሕዝባችን በዚህ ተስፋ ውስጥ በገንዘቡም በጉልበቱም በሙያውም የበኩሉን ድጋፍ እየተረባረበ ባለበት ወቅት ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በአገራችን ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ግድባችንን አስመልክቶ አገራትን ወደ ግጭትና አለመግባባት ውስጥ የሚከት የጥፋት መልዕክት ማስተላለፋቸውን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመታዊ ጉባኤው ላይ እንዳለ በሐዘን ተመልክቶታል፡፡
የተወደዳችሁ በአገር ውስጥ ሆነ በውጭው ዓለም የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን እና ሌላውም የዓለምም ሕዝብ
ታሪክ እንደሚያስታውሰን አገራችን ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ ታፍራና ተከብራ የኖረችውና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ምሳሌ የሆነችው አገሪቱ አገረ እግዚአብሔር ሕዝቡ ሕዝበ እግዚአብሔር በመሆኑና በዚህም የሰውና የእግዚአብሔር አንድነት አገራችን በእግዚአብሔር ተጠብቃ የኖረች አገር በመሆኗ ነው፡፡
ከዚህም ጋር በዘመናት አገሪቱን እንዲመሩ የተጠሩ መሪዎችና ሕዝቧ በአገራችን ላይ ይነሳሱ የነበሩ ወራሪዎች ያሰቡት ሳይሳካላቸው አገሪቱ ድንበሯ ከነክብሯ ተጠብቆ የኖረችና የሕዝባችን አገራዊ አንድነት ተጠብቆ የኖረ በመሆኑ ነው፤ ዛሬም ቢሆን ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ሆነ ከከሌሎች ተመሳሳይ አካላት በአገራችን ላይ እየተላለፈ ያለው የጥፋት ጥሪ መተዛዘቢያ ከሚሆን በስተቀር አገራችን ጠባቂዋ በሆነው እግዚአብሔርና በሕዝባችን አንድነት ተከብራና ተጠብቃ እንደምትኖር ሙሉ እምነታችን ነው፡፡
የተወደዳችሁ በአገር ውስጥ ሆነ በውጭው ዓለም የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን እና ሌላውም የዓለምም ሕዝብ
አገራችን ኢትዮጵያ ከአንድ መቶ ሚሊዮን ያላነሱ ልጆቿ እንደ የአካባቢያቸውና እንደ አደጉበት አካባቢ የተለያዩ ቋንቋ እየተናገሩ ባሕላቸውንና ሥርዓታቸውን ጠብቀው በመከባበርና በአንድነት መንፈስ እየተረዳዱ የሚኖሩበት እንግዳ በመቀበልና ቤት ያፈራውን ተካፍሎ በመኖር የሕዝባችን ልዩ መታወቂያው እንደሆነ ይታወቃል፡፡
– ፍትሐዊ
– የዓለምም ሕብረተሰብ
አሁንም ከኃያላኑ መሪዎችም ሆነ ሌሎች አገራችንን በሩቅ ሁነው ከሚጐመጇት አካላት እየተጐሰመ ያለው የጥፋት ጥሪ ኢትዮጵያን እንደትናንት አባቶቻችን በአንድነት በመከባበርና በመመካከር በመደማመጥም ጭምር መቆም ከቻልን ከአቅማችን በላይ የሚሆን ነገር እንደሌለ ከእኛ ይልቅ የአገራችንን እድገት የማይፈልጉ ከእኛ የበለጠ ይገነዘቡታል፤ ያውቁታልም፡፡
ዓለማችን በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ያጣችው ነገር ቢሆን ሰላምን ነው፡፡ ሰላም እንደሚታወቀው ከአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚገኝ ሳይሆን በጋራ ለአለም ሰላም መቆም ሲቻል ብቻ ነው፡፡
ስለዚህ ይህንን የአገራችን ሰላምም ሆነ ጥቅም ሊያሳጣ በሚችል መልኩ ጥቅምት 13 ቀን 2013ዓ.ም. የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአገራችን ላይ ያስተላለፉት የጦርነት ጥሪ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ ይቃወማል፡፡ መላውም የዓለም መንግሥታትና ሕብረተሰብ ችግሩን በጥልቀት እንዲገነዘቡት ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
በአገር ውስጥ ሆነ ከአገር ውጭ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን እንዲሁም አገር የመምራት ኃላፊነት የተጣለባችሁ የፌዴራልና የክልል መሪዎች ከዚህም ጋር በአገሪቱ ውስጥ የምትገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአሁኑ ጊዜ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን የትኛውንም የየግልና የቡድን አመለካከታችንን ወደጐን በመተው አንድነታችንን ልናጠናክርበት የሚገባ ወቅት መሆኑን በመገንዘብ ኢትዮጵያዊ አንድነታችሁን ከምንጊዜውም የበለጠ ጠብቃችሁ ለአገራችን ሕልውና እንድትቆሙ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤ ይቀድስ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አሜን::
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
(ሐራ ተዋህዶ)