Connect with us

ኢዜማ በመሬት ወረራና በኮንደምኒየም ህገወጥ እደላ ያቀረበውን ክስ በተመለከተ

ኢዜማ በመሬት ወረራና በኮንደምኒየም ህገወጥ እደላ ያቀረበውን ክስ በተመለከተ ኢንጅነር #ታከለ_ኡማ ተከታዩን ማስተባበያ ሰጥተዋል።
Photo: Social Media

ህግና ስርዓት

ኢዜማ በመሬት ወረራና በኮንደምኒየም ህገወጥ እደላ ያቀረበውን ክስ በተመለከተ

ኢዜማ በመሬት ወረራና በኮንደምኒየም ህገወጥ እደላ ያቀረበውን ክስ በተመለከተ ኢንጅነር #ታከለ_ኡማ ተከታዩን ማስተባበያ ሰጥተዋል።

***
“…. የመሬት ወረራ የመላው የኢትዮጵያ ከተሞች ችግር ነው። በተለይ በአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ ችግሩ የከፋ ነው። በአዲስ አበባ ብቻ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰነድ አልባ የመሬት ይዞታዎች (ሕገወጥና አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድላቸው) የተያዙ መሬቶች አሉ። ይህ ጥናት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሳይቀሩ አጥንተው ከንቲባ ጽሕፈት ቤትና ሌሎችም የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ገብቷል። ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ካቀረብናቸው የከተማው ችግር ውስጥ አንዱ የመሬት ወረራ ጉዳይ ነው። ችግሩን ለመቅረፍም የሕግና የመዋቅር፣ እንዲሁም የቴክኖሎጂ አቅም ይፈልጋል። ምን ለማለት ነው? በአዲስ አበባ ያለው የመሬት ወረራው ፓርቲው ካቀረበው ሪፖርት ባላይ ነው።

ነገር ግን ወደ አንድ ወገን ወይም ወደ አንድ ብሔር ማላከክ አደገኛ የፖለቲካ አዝማሚያ ነው። ‹‹ፍትሕን አሰፍናለሁ፣ ለሁሉም ዜጎች እኩል እታገላለሁ›› ከሚል ቡድን እንደዚህ ዓይነቱን ጥልቅ ጥላቻ ስታይ የአገራችን ፖለቲካ ከጥላቻና ከእግር ጉተታ አለመውጣቱን፣ እንዲሁም አሁንም ገና ረዥም ርቀትና ትጋት ከሁላችንም እንደሚጠበቅ ነው ያስተዋልኩት።

በቤቶች ላይ ላቀረቡት ሪፖርት በእርግጠኝነት መረጃ የሰጣቸው ሰው በግልጽ እንዲሳሳቱ ለማድረግ የፈለገ ይመስላል። በመጋቢት 2011 ዓ.ም. ወር ዕጣ የወጣላቸው የቤቶች ቁጥር 51 ሺሕ አካባቢ ነው። የእነሱ ‹‹የጥናት ሪፖርት›› ግን የሚለው ሌላ ነው። በነገራችን ላይ አዲስ አበባ የምትተዳደረው ከተማው በሚያወጣቸው ሕጎች ብቻ አይደለም። የፌዴራል መንግሥት በሚያወጣቸው ሕጎችም ጭምር እንጂ። ሕጎችና አሠራሮች ደግሞ ከጊዜና ከሕዝብ ጥቅም ጋር የሚሄዱ ካልሆኑ፣ በማንኛውም ጊዜ ሊሻሻሉ ወይም ሙሉ በሙሉ ሊሻሩ ይችላሉ። የቤቶች ግንባታ የተጀመረው ከ15 ዓመታት በፊት ሲሆን፣ እስካሁ ተገንብተው ከተላለፉት፣ እየተገነቡ ካሉትና ዕጣ ሊወጣባቸው ከታቀዱት ከ300 ሺሕ በላይ ቤቶች ውስጥ በከተማው ካቢኔ የተወሰነው ለ20 ሺሕ አርሶ አደሮች ነው።

እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎች አሁን የተጀመሩ አይደሉም። ከዚህ በፊትም (በቀድሞዎቹ አስተዳደሮች) ለመምህራንና ለጤና ባለሙያዎች፣ ለፓርላማ አባላት፣ እንዲሁም ለአገር መከላከያ ሠራዊት የጦር ጉዳተኞች በተመሳሳይ ውሳኔ ሲሰጥ ነበር። የአርሶ አደር ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲ አጀንዳ የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም። አርሶ አደር በመሆናቸው በደሉን ተሽክመው ይኑሩ የሚል ጭፍን ፍርድ ከሌለ በስተቀር። አርሶ አደሩ እኮ ለብዙ ዓመታት ከራሱ መሬት፣ ከራሱ የእርሻ ማሳ ‹‹በልማት›› ምክንያት (በሪል ስቴት፣ በኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ) ምክንያት ከመሬቱ ተነቅሏል። እኛ ያደረግነው ምንድን ነው? በአጠቃላይ ከስድስት ክፍላተ ከተሞች ከኑሮአቸው ስለተፈናቀሉ እንዲቋቋሙ ስለተፈለገ በካቢኔ አስወሰንን።

ይህም ማለት ከአጠቃላይ የቤቶች ግንባታ ስድስት በመቶ ለተፈናቀሉ አርሶ አደሮች እንዲሰጥ ነው የወሰንነው። ከ20 ሺሕ ውስጥ አርሶ አደር ያልሆኑ ሰዎች አሉ፣ በጥናታችን ለይተናል ካሉ ደግሞ ይህ ሥራቸው ያስመሠግናቸዋል። ነገር ግን ይህንን ጥናት ያሉትን ነገር ይፋ ለማድረግ ለምን የአመራር ሽግሽግ ወቅት ጠበቁ? ለምን አሁን? እኔ ወደ ሌላ ኃላፊነት እየሄድኩ ባለበት ወቅትና የቀረበውን ትችት መልስ ለመስጠት በማልችልበት ወቅት ለምን ለማቅረብ መረጡ የሚለውን ጥያቄ አንስቼ መልሱን ለራሳቸው መተው እፈልጋለሁ።

ድራማውን የሚረዳ ሰው ትወናውን በደንብ ይገነዘባል። ዳሩ ግን ድራማው በከሸፈ ዳይሬክተር የተዘጋጀ፣ በከሸፈ ድርሰት ላይ የተመሠረተ፣ በከሸፈ ትወና የቀረበ ነው። እነዚህ ሰዎች በአንድ በኩል የከሸፉ ‹‹ባለቅኔዎች›› ስብስብ መሆናቸውን፣ በሌላ በኩል በግርግር ወይም በመመሳጠር በሚሠራው የአማተር ፖለቲካ ጊዜያዊ የፖለቲካ ግለት ከመፍጠር ባለፈ፣ ለአገር ግንባታ ፋይዳ እንደሌለው ያየሁበት ነው።” (ምንጭ:- ሪፖርተር)

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top