ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት በኋላ በተነሳው ግርግር ምክንያት በቁጥጥር ሥር የዋሉት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አባሉ አቶ ጃዋር ሞሐማድ ተጨማሪ ቀጥሮ ተሰጥቷቸዋል።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በአቶ ጃዋር ሞሐመድና ሌሎች 13 ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ በተመለከተበት የዛሬ [አርብ] ችሎት በፌዴራል ፖሊስ የአዲስ አበባ ከተማ የማረሚያ ቤቶች ኃላፊ አስተዳዳሪ በፖሊስ ተይዘው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ ኃላፊው 24 ሰዓት ታስረው እንዲቀርቡ ነው ትዕዛዝ የሰጠው።
ይህ ትዕዛዝ የተሰጠው በእነ አቶ ጃዋር ሞሐመድ የክስ መዝገብ ውስጥ ያሉ የኦኤምኤን ጋዜጠኛ መለሰ ድሪብሳና ሌሎች አራት ሰዎች የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጎላቸው ውጤት እንዲያመጡ የተሰጠው ተደጋጋሚ ትዕዛዝ ተፈፃሚ ባለመሆኑ ነው።
ፍርድ ቤቱ ባለፈው ሳምንት [ነሐሴ 20/2012] በነበረው ችሎት ላይ ተጠርጣሪዎቹ ለምን የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንዳልተደረገላቸው ኃላፊው ፍርድ ቤት መጥተው ያስረዱ ቢልም አስተዳዳሪው ዛሬ በነበረው ችሎት ላይ አልቀረቡም፤ ተወካይም አላኩም ብሏል።
በሌላ በኩል የጃዋር ጠባቂዎች የነበሩ ግለሰቦችን ጨምሮ ከተራ ቁጥር 4 እስከ 14 የተዘረዘሩ ተጠርጣሪዎች የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጎላቸው ነፃ መሆናቸውን የሚገልፅ ውጤት የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለፍርድ ቤቱ ልኳል።
ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ቀጠሮ ይዞ የነበረው የአቃቤ-ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ነበር። ነገር ግን ከተራ ቁጥር 4 እስከ 9 ያሉ ተጠርጣሪዎች ከኮቪድ-19 ነፃ መሆናቸው ቢረጋገጥም ፍርድ ቤት አልቀረቡም።
ይህን ተከትሎም ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ለፊታችን ማክሰኞ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ ለነሐሴ 26/2012 በሰጠው ቀጠሮ ላይ 14ቱም ተጠርጣሪዎች እንዲቀርቡ ለፖሊስ ጠብቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ከዚህ በተጨማሪ አንደኛ ተጠርጣሪ አቶ ጃዋር “ከልጄ እና ከባለቤቴ ጋር በቪዲዮ ኮንፍረንስ እንድገናኝ ይፈቀድልኝ” ሲሉ ያቀረቡትን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ በሳምንት ሁለት ጊዜ በቪዲዮ ኮንፍረንስ እንዲገናኙ አዟል።
ፍርድ ቤቱ ይህንን ትዕዛዝ በሰጠበት ወቅት ፍርድ ቤት የሚሰጠው ትዕዛዝ አንድ ጊዜ ብቻ ተግባራዊ የሚደረግ ሳይሆን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር እስካሉ ድረስ የሚፀና ነው ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪ ፍርድ ቤቱ ለአቶ ጃዋር ሞሐመድ መጽሕፍት፣ እስርቢቶና ወረቀት እንዲቀርብላቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች ከዚህ በፊት ከደንበኞቻቸው ጋር በበቂ ሆኔታ እየተገናኙ እንዳልሆነ በመጥቀስ ቅሬታ ማቅረባቸው ይታወሳል። ይህን የተመለከተው ፍርድ ቤት በሳምንት ሦስት ቀናት እንዲገናኙ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ከዚህ በፊት አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ ከጓደኞቻቸው ጋር መገናኘት አልቻልንም ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ፍርድ ቤቱ በጓደኛ የመጠየቅ መብት ቢኖራቸውም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚከለክል በመሆኑ ውድቅ አድርጎታል።
12ኛ ተጠርጣሪ አቶ ሸምሰዲን ጣሃ ከዚህ በፊት በዋለው ችሎት ላይ በፖሊስ እንደተደበደቡና የሕክምና አገልግሎት አንድ ጊዜ ብቻ እንዳገኙ በመናገር ቅሬታ አቅርበው ነበር። ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪው በመረጡት ሆስፒታል እንዲታከሙ እንዲመቻችላቸውና ፖሊስ ይህን እንዲያስፈፅም አዟል።
ፍርድ ቤቱ አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ በአጠቃላይ 14 ተጠርጣሪዎች ላይ የሚመሰክሩ ቀሪ ምስክሮችን ለማድመጥ ለፊታችን ማክሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።(BBC)