Connect with us

በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመውን ዘር ተኮር ጥቃት የሚመረምር ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን

በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመውን ዘር ተኮር ጥቃት የሚመረምር ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን እንዲቋቋም ስለመጠየቅ፤
Photo: EPA

ህግና ስርዓት

በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመውን ዘር ተኮር ጥቃት የሚመረምር ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን

በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመውን ዘር ተኮር ጥቃት የሚመረምር ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን እንዲቋቋም ስለመጠየቅ፤
(ከያሬድ ኃ/ማርያም ~ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

የሃጫሉን ሞት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በብሔር እና ሃይማኖት ማንነት ላይ ያነጣጠረና በዘር ተኮር ጭፍጨፋ ሊፈረጅ የሚችል የጥቃት እርምጃ በተደራጁ እና በታጠቁ ኃይሎች መፈጸሙን የሚያሳዩ ማስረጃዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች በመውጣት ላይ ናቸው። አንዳንድ የመንግስት አካላትም በዚህ ጥቃት ዙሪያ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳትፎ እንደነበራቸው በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር ተገልጿል። በአንዳንድ ስፍራዎችም የክልሉ ታጣቂዎች መሳሪያቸውን ጭምር በሕዝብ ላይ ጥቃት ይፈጽሙ ለነበሩት ቡድኖች አሳልፈው በመስጠት ጥቃቱ እንዲፈጸም መደረጉም ተገልጿል። ይህም ብቻ አይደለም በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች ዘር ተኮር የሆነው ጥቃት እና ጭፍጨፋ ሲፈጸም በአካባቢው የነበሩ የመንግስት ባለሥልጣናት እና የጸጥታ ኃይሎች ዳር ቆመው ጭፍጨፋውን፣ የንብረት ማውደሙት እና የዝርፊያውን ተግባር ይመለከቱ እንደነበር እማኞች መስክረዋል።

እንዲ ባሉ አሰቃቂ እና ዘር ተኮር በሆኑ ጭፍጨፋዎች ላይ የመንግስት አካላት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳትፎ ከነበራቸው ይህ ጉዳይ በራሱ በመንግስት ሳይሆን በገለልተኛ ወገን ሊጣራ ይገባዋል። እነዚህ የክልል ባላሥልጣናት ለተፈጸመው ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑባቸውን መረጃዎች ቀድመው ሊደብቁ የሚችሉበት እድል ሰፊ ነው። ስለሆነም ጉዳዩ ከመንግስት ነጻ በሆኑ እና ከፍተኛ የሙያ ብቃት ባላቸው ሰዎች ሊጣራ ይገባል። ቀደም ሲል የጋንቤላውን እልቂት እና ከዛም በኋላ የምርጫ 97ቱን ግጭት ተከትሎ የተቀሰቀሱትን ግጭቶች እና የደረሰውን የጉዳት መጠን የሚያጣሩ ኮሚሽኖች መሰየማቸው ይታወሳል። በተለይም የምርጫ 97ቱን ግጭት ያጣራው እና በዳኛ ፍሬህይወት ይመራ የነበረው አጣሪ ኮሚሽን የእነ መለስ ዜናዊን ጫና እና ማስፈራሪያ ተቋቁሞ ያከናወነው ምርመራ ታሪክ ሁሌም የሚያነሳው ነው።

አሁንም መንግስት ጊዜ ሳይወስድ እና መረጃዎች ተዳፍነው ሳይጠፉ በፊት በኦሮሚያ ክልል፣ በአዲስ አበባ እና በሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች የተፈጸሙትን ዘር ተኮር ጭፍጨፋ እና ስለደረሰው የንብረት ውድመት የሚያጣራ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን እንዲያቋቁም ማሳሰብ እፈልጋለሁ። ይህን ሃሳብ የምትጋሩ ፍትህ ፈላጊ ወገኖች ሁሉ በሁሉም መድረክ ይህን ሃሳብ እንድታንጸባርቁ እና መንግስት በአፋጣኝ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን እንዲያቋቁም ጫና እንድትፈጥሩ በአክብሮት እጠይቃለሁ።

በዘር ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እና ጭፍጨፋዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው፣ በቂ ምርመራ ተደርጎባቸው በድርጊቱ ላይ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉ በአፋጣኝ ለፍርድ ካልቀረቡ አገሪቱን ወደከፋ አደጋ ይከታታል።

ፍትህ በማንነታቸው የጥቃት ሰለባ ለሆኑ ሁሉ!

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top