Connect with us

ንብረታቸው የወደመባቸው ወገኖች ድጋፍ ይደረግልን አሉ

ንብረታቸው የወደመባቸው ወገኖች ሕዝብና መንግሥት ድጋፍ ያድርጉልን አሉ
Photo: EPA

ህግና ስርዓት

ንብረታቸው የወደመባቸው ወገኖች ድጋፍ ይደረግልን አሉ

ባለፈው ሰሞን በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች የንብረት ውድመት የደረሰባቸው ወገኖች፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ይታደጉን ሲሉ ጥሪ አቀረቡ፡፡ እስካሁን ያሉትም ግለሰቦች በሚያደርጉላቸው ድጋፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የድምፃዊ ሃጫሉ ድንገተኛ ግድያ ከተፈጸመ በኋላ ባልጠበቁትና ባላሰቡት ሰዓት በደረሰባቸው ጥቃት የቤተሰቦቻቸውን አባላት በሞት የተነጠቁና ንብረታቸው የወደመባቸው ግለሰቦች፣ ሕዝብና መንግሥት በፍጥነት ካልደረሱላቸው ጎዳና ላይ ወድቀው እንደሚቀሩ ተናግረዋል፡፡

በሻሸመኔ ከተማ መኖሪያ ቤቶች፣ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮች፣ ሆቴሎችና የተለያዩ ተሽከርካሪዎች የተቃጠሉባቸው ሰዎች ተወካዮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለበርካታ ዓመታት ያፈሩዋቸው ንብረቶች እንዳሉ ወድመዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ከለበሷቸው አልባሳት በስተቀር ምንም ነገር ስለሌላቸው የሕዝብና የመንግሥት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ብዙዎቹ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ በመሆናቸውና የሚያገኙት ገንዘብም እዚያው በዚያው የሚገላበጥና በሥራ ላይ ስለሆነ፣ በባንክ ሒሳባቸው ውስጥ እዚህ ግባ የሚባል ገንዘብ ስለሌላቸው መልሰው ለመቋቋም እንደሚቸገሩ ተወካዮቹ ተናግረዋል፡፡

በዝዋይ (ባቱ) እና በአርሲ ነገሌ ከተሞች ውስጥ ንብረቶቻቸው የወደሙባቸው ሰዎች ምንም የቀራቸው ነገር ስለሌለ፣ እነሱም የሕዝብና የመንግሥት ድጋፍ ካልተደረገላቸው መልሰው ማገገም አይችሉም ተብሏል፡፡

በሻሸመኔ፣ በዝዋይና በአርሲ ነገሌ ከተሞች በተለያዩ ሥፍራዎች በጊዜያዊነት ተጠልለው የሕዝብና የመንግሥትን ምላሽ የሚጠብቁት እነዚህ ወገኖች፣ ወቅቱ ክረምት እንደ መሆኑ መጠን አፋጣኝ ድጋፍ እንሻለን እያሉ ነው፡፡

ከማክሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2102 ዓ.ም. ንጋት ጀምሮ በሦስቱም ከተሞች በተቀራራቢ ሰዓት በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካቶች ሲገደሉ፣ ከፍተኛ የሆነ ሀብት ወድሟል፡፡ መኖሪያ ቤቶች፣ ሆቴሎች፣ የንግድ መደብሮች፣ ሕንፃዎች፣ የአበባ እርሻዎችና ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል፡፡ የመንግሥት ተቋማትም በቃጠሎ ወድመዋል፡፡

በባሌና በአርሲ ዞኖች በተፈጸሙ ጥቃቶችም በርካቶች ተገድለው ከፍተኛ ንብረት ሲወድም፣ ክሊኒኮችና ጤና ጣቢያዎችን ጨምሮ የመንግሥት ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል፡፡ በባሌ ዞን በአጋርፋ ወረዳ ውስጥ መኖሪያ ቤቶች፣ ሆቴሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሲወድሙ፣ በአርሲ ዞን ገደብ አሳሳ ከተማ ተመሳሳይ ውድመት መድረሱ ታውቋል፡፡ የንብረቶቹ ባለቤቶችም ባዶ እጃቸውን ቀርተው የመንግሥትን ድጋፍ እየተጠባበቁ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማም የንግድ መደብሮች፣ ሆቴሎችና የባንክ ቅርንጫፎች ጥቃት የተፈጸመባቸው ሲሆን፣ ከ250 በላይ ተሽከርካሪዎች መሰባበራቸው ይታወሳል፡፡ የጉዳቱ መጠን ምን ያህል እንደሆነ በውል ባይታወቅም፣ በሚሊዮን ብሮች እንደሚገመት ፖሊስ ለፍርድ ቤት ካቀረበው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡(ሪፖርተር)

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top