ፓስወርዷን ያገኘሁ ቀን ያጣኋት እጮኛዬ…
(አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ)
ዓለም ላይ ካሉ ነገሮች ሁሉ አብልጣ ከምትወደኝና ከምወዳት ፍቅረኛዬ ጋር በዚህ ወር ሠርጋችንን ደግሰን ለመጋባት ከረዥም ጊዜ በፊት ወስነን ነበር፡፡ በዚህ መሃከል ግን ኮሮና የሚባል በሽታ በመምጣቱና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ እቅዳችን ከሸፈ፡፡
አዋጁም የሠርጋችንን ቀን እንደ ምርጫው ቀን ባስተጓጎለው ጊዜ በበኩሌ እንደ መንግሥት የደስተኝነት ስሜት ነበር የተሰማኝ፡፡ ምክንያቱም ሄለንን ስለምወዳትና ፍላጎቷን ማክበር ስላለብኝ እንጂ ከበፊትም ጀምሮ በርካታ ሰው ሰብስቦ የማብላት እቅድም ሆነ አቅም አልነበረኝም ነበር፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ ግን ኮሮና የፈጠረልኝን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የሰርግ ዝግጅት ትቼ የምወዳትን ሴት ሚስቴ በማድረግ ወደ ቤቴ ለማስገባት ስዘገጃጅ ‹‹ያለ ሰርግ ትዳር ከመመስረት ቆሜ መቅረትን እመርጣለሁ›› በማለት እጮኛዬ እንቢተኛ ሆነች፡፡
ይሄንንም ሐሳቧን ለማስቀየር ለኮሮና ክትባት እስኪገኝ ወይም ደግሞ አዋጁ እስኪነሳ ድረስ ተነጣጥለን ከምንኖር ጎጇችንን መሥርተን ብንኖርና ከዚያ በኋላ ሠርጋችንን ብንደግስ ይሻላል›› በማለት ላግባባት ብሞክርም ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ‹‹ያለ ምርጫ ቤተ-መንግሥቱን አታስቡት›› ብለው እነ ልደቱንና ጃዋርን እንደተቆጡት ሁሉ እሷም ‹‹ያለ ሠርግ ትዳርን አታስበው›› በማለት ርቀቷን ጠበቀች፡፡
በመሆኑም ኮሮና ባይመጣ ኖሮ ሚስቴን አቅፌ ያንን አስደሳች ነገሯን በየቀኑ እያጣጣምኩ ጫጉላ ከምገባበት ቤት ብቻየን ተወሽቤበት ስሰቃይ ከረምኩ፡፡
ባለፈው ሰንበት ታዲያ እጮኛዬ ወደ ቤቴ መጥታ የራበኝን ገላዋን የምጎበኝበትን እድሉን ፈጥራልኝ ነበር፡፡ ከአንድ ዙር ማሳጅ በኋላም እሷ ወደ ሻወር ቤት እንደገባች ከአጠገቤ አስቀምጣው የሄደችውን ሞባይል እንደ ቀልድ ብድግ አድርጌ ማስታወሻ የምትጽፍበት አፕሊኬሽን ስከፍተው የፌስቡክ አካውንቷ User name እና Password ዐይኔ ውስጥ ገባ፡፡ በዚያች ቅጽበትም ለበጎ ነገር ሲሆን በቂ ትኩረት የማይሰጠው ጭንቅላቴ እስከ ዘላለም ላይረሳው ፓስወርዷን ሸምደደው፡፡
እናም እጮኛዬን ከሸኘሁ በኋላ ልረሳው የምፈልገውን ፓስወርድ እያስታወሰ ‹‹አካውንቷን ከፍተህ የፍቅረኛህን ምንነት እወቅ እንጂ›› እያለ ይለምነኝ ጀመር፡፡ ለዚህም ልመናው ‹‹የእጮኛዬን ልብ ከእራሴ ልብ በላይ ስለማውቀውና ስለማምነው አካውንቷን መመልከት አይጠበቅብኝም›› ብዬ ብመልስለትም ‹‹የሰው ማንነት አካውንቱን በማየት እንጂ የሚያወራውን በመስማት አይታወቅም›› እያለ መናጢ ጭንቅላቴ ሲነዘንዘኝ የይለፍ ቃሉን አስገብቼ አካውንቷን ከፈትኩት፡፡
እናም ፈንጅ እንደሚረግጥ ሰው እየተሸበርኩ ‘ሜሴጅ’ የሚለውን ቁልፍ በተጫንኩት ጊዜም ‹‹ዶክተር በላይ አበጋዝ የልብ ህክምና ማዕከል›› ውስጥ ካሉ ታካሚዎች በቁጥር የሚበልጡ የልብ ሕመምተኞች ‹‹ልቤን! ልቤን! ልቤን!›› እያሉ ጠበቁኝ፡፡
ከእነዚህም መሃከል መጀመሪያው ረድፍ ላይ ያገኘሁትን ‘ቻት ሩም’ ከፍቼ ስገባ ያጋጠመኝ የልብ ታማሚ ገጣሚ ቢጤ ነው መሰል…
‹‹አንቺን ካየሁ ወዲህ በዐይኔ በብረቱ፣
የልቤ በሽታ ታጣ መድሃኒቱ›› የሚል ኑዛዜውን በግጥም ልኮላት አገኘሁ፡፡
ለዚህም ግጥሙ…
‹‹የልብህ በሽታ ገዝግዞ እስኪገድልህ፣
እንደ መድሃኒቱ ጠፍቶ ይቅር ዐይንህ›› የሚል መልስ ጽፌ ልልክለት ስል ‹‹እኔን በማየቱ የታመመ ልብህ፣ አንድ ቀን ይድናል በእጆቼ ሳሻሽህ›› በማለት መልሳለት አገኘሁ፡፡
ይሄንንም መልሷን ሳነብ የተገለጸልኝ ነገር ኮሮና የሚባለው በሽታ ከንክኪና ከትንፋሽ በተጨማሪ የሰው አካውንት በመፈተሸ እንደሚተላለፍ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ አደገኛ በሽታ ተለክፌ ሰውነቴን ይጎንፈኝ፣ እራሴን ይወቅረኝ፣ ደረቴን ያፍነኝ ጀመር፡፡
የሚገርመው ነገር ደግሞ እጮኛዬ እስካሁን እኔ ሳላውቅ የተጀነጀነችው አንሶ አሁንም ኦንላይን ሆና ካናዳ አገር ከሚኖር ከአንድ ዲያስፖራ ጋር እየተጻጻፈች መሆኑ ነው፡፡ እናም ከዚህ ሰው ጋር የተጻጻፉትን ሜሴጅ ወደኋላ እየገለጥኩ ሳነብ አንድ ቦታ ላይ ‹‹አንቺን የመሰለች ሴት ፍቅረኛ እንደሌላት ሳስብ እስካሁን ድረስ ይገርመኛል›› በማለት ለጻፈላት ሜሴጅ ‹‹ነገርኩህ እኮ የሆነ ሰዓት ጠብሼ ነበር! ግን ከትዳር በፊት ክብረ ንጽህናየን ለመውሰድ ጓጉቶ ‘አብረን እንደር’ እያለ ሲያስቸግረኝ አትሆነኝም ብዬ ተውኩት›› የሚል መልስ ሰጥታዋለች፡፡ (ድንቄም ክብረ ንጽህና! የዛሬ ዓመት ከእኔም ጋር ለመጣበስ ስናስብ ድንግል መሆኗን ነግራኝ ነበር፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን አልጋዬ ላይ አጋድሜ በስድስተኛ የስሜት ሕዋሴ ነገርዮውን ሳማስል ከቆየሁ በኋላ ‹‹የት አለ ድንግልናው?›› በማለት ስጠይቃት የሰጠችኝ መልስ ‹‹ጣትህን አስገብተህ ፈልገው›› የሚል ነበር፡፡
የሆነው ሆኖ የተጻጻፉትን ሳነብ ጉሮሮየ ተዘግቶ መተንፈስ ስለቸገረኝ አንገቴን በመስኮት ብቅ አድርጌ ምድር ምድር እያየሁ የወደቀ ቬንትሌተር እፈልግ ጀመር፡፡ ልቤም ለተወሰነ ጊዜ ያህል ደም መርጨቱን ትቶ ቂም ሲያመነጭ ቆየ፡፡
እናም ከመሞቴ በፊት ሜሴጁን ወደኋላ ገለጥ ገለጥ ሳደርገው እጮኛየና ዲያስፖራው በአንዱ ምሽት አልጋቸው ላይ እርቃናቸውን ሆነው መባለጋቸውን የሚገልጹ ቃላቶች ተደርድረው ጠበቁኝ፡፡ ይሄንንም በማነብበት ወቅት ልክ እንደ እኔ ስክሪኔም ላብ ያመነጭ ያዘ፡፡
ከዚህ ባለፈም፣ ጭንቅላቴ ማሰቡን፣ ሰውነቴ መንቀሳቀሱን፣ ሳንባዬ መተንፈሱን፣ ልቤ መምታቱን አቁሞ ከመላው ሰውነቴ ውስጥ በሕይወት ስለመኖሬ ፍንጭ የሚሰጥ ነገር ብልቴ ብቻ ሆነ፡፡
በመሆኑም ከሌሎች ጋር የተጻጻፈችውን ቀርቶ ከዚህ ዲያስፖራ ጋር ቻት ያደረገችውን የምጨርስበት ብርታት ማግኘት አልቻልኩም፡፡ እናም ‹‹ኮሮና እንዳለፈ ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ካገባሁሽ በኋላ ወደ ካናዳ እስክወስድሽ ድረስ ድንግልናሽንም እራስሽንም ጠብቂልኝ›› የሚል ማሳሰቢያውን አንብቤ ስጨርስ ‹‹ሎግ አውት›› የሚለውን ቁልፍ ተጭኜ የእጮኛዬን ትክክለኛ ማንነት ያገኘሁበትን አካውንት ለቅቄ ስወጣ እሷም ከገባችበት ልብና ጭንቅላት ትወጣ ጀመር፡፡