Connect with us

መልከኛ አውራ ዶሮ – የበዓል ወግ

መልከኛ አውራ ዶሮ - የበዓል ወግ

መዝናኛ

መልከኛ አውራ ዶሮ – የበዓል ወግ

መልከኛ አውራ ዶሮ (የበዓል ወግ) \ አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ

ለበዓል የሚሆን ዶሮ ልገዛ ስወጣ ሰፈራችን ያለው አደባባይ የዶሮና የበግ መሸጫ ገበያ ሆኖ አገኘሁት፡፡ ሰው ደግሞ ‹‹ኮሮና ቢለክፈኝም መረቁን ጠጥቼ እድናለሁ›› ብሎ ነው መሰል አንድ ቦታ ላይ ክምችት ብሎ ይገበያያል፡፡

እናም ወደ ውስጥ ሳልገባ እርቀቴን ጠብቄ ዳር ዳሩን ስዞር… በርካታ ዶሮዎችን የያዘ አንድ ወጣት ላይ ዐይኔ አረፈና ወደዚያው በማምራት ‹‹አውራ ዶሮዎቹ ስንት ስንት ናቸው?›› አልኩት፡፡
‹‹የፈረንጅ ነው የሐበሻ?››
‹‹የሐበሻ››
‹‹የሐበሻ ስትል መልከኛ ነው የምትፈልገው ምን-ቅጡ?››
‹‹አልገባኝም?››

‹‹ምን-ቅጡ ማለት ለወጥነት የሚውል ዶሮ ነው፤ መልከኛ የሚባለው ደግሞ እንደዚህ ገብስማ ቀለም ያለውና ከወጥነት ባለፈ ለመድሃኒትነትም ጭምር የሚያገለግል ነው›› በማለት አንድ ዶሮ ብድግ አድርጎ አሳየኝ፡፡
‹‹እንዴት ሆኖ ነው መድሃኒት የሚሆነው?››
‹‹መልከኛ ዶሮ የታረደበት አካባቢ ማንኛውም በሽታ ዝር አይልም››
በማብራሪያው ፈገግ ብዬ ‹‹ዋጋቸው ስንት ስንት ነው?›› በማለት ስጠይቀው ‹‹መልከኛው ስድስት መቶ፣ ምን ቅጡው ደግሞ 500›› የሚል መልስ ሰጠኝ፡፡

እናም ጓንት በለበሰ እጄ ሁለቱንም አይነት ዶሮዎች አንጠልጥዬ ስመዝናቸው በመድሃኒትነቱ ሳይሆን በክብደቱ መልከኛ የተባለው ሻል ብሎ ስላገኘሁት ከጥቂት ክርክር በኋላ ለሳኒታይዘር የያዝኩትን በጀት ወደ ዶሮ ግዥ በማዛወር መልከኛ አውራ ዶሮዬን ገዝቼ ተመለስኩ፡፡

ከዚያም ምሳየን ከቀማመስኩ በኋላ ወደ ውጭ ስወጣ አውራ ዶሮዬ ብቸኝነት ባስከተለበት የስሜት መጎዳት ደብሮት አገኘሁት፡፡ በመሆኑም ሁለት እግሩ የታሰረበትን ገመድ ፈትቼ አንድ እግሩን ብቻ በረዥም ገመድ በማሰር እንዲጫወት ስፈቅድለት ተነስቶ በመንቀሳቀስ ፈንታ መቆም አቅቶት ይልፈሰፈስ ጀመር፡፡

ያም ሆኖ ታዲያ እግሩን ደንዝዞት እንጂ አሞት ስላልመሰለኝ ‹‹ወፌ ቆመች›› እያልኩ ስጠብቀው ብቆይም ‹‹በክራንች ካልሆነ በቀር አልቆምም›› ብሎ ይዘረር ያዘ፡፡ በዚህም ጊዜ ባለቤቴን ጠርቼ ስለሁኔታው ስነግራት ‹‹ፖሊዮ እንጂ ኮሮና እግርን አያጠቃም›› በማለት ልታጽናናኝ ብትሞክርም… ዶሮው ግን ከእግሩ በተጨማሪ ከሥጋና ከአጥንት የተሰራ አንገቱን እንደ አትክልት ያጠነዝለው ጀመር፡፡ ለመድሃኒት ሊሆነኝ ቀርቶ ለእራሱም መድሃኒት የሚያስፈልገው ሆኖ አረፈ፡፡

በመሆኑም ሕመሙ ኮሮና ከሆነ በሚል ግምት በሳኒታይዘር የተፈተፈተ የነጭ ሽንኩርትና የፌጦ ፍትፍት እንዲመጣለት አደረኩኝ፡፡ እርሱ ግን የቀረበለትን ፍትፍት መብላት ሲገባው እንደ አክፋይ ‹‹ጾሙ በሌላ ዶሮ ካልተፈሰከልኝና የመረቅ ፍትፍት ካልቀረበልኝ በቀር እህል የሚባል አልቀምስም›› ብሎ አመጸ፡፡

እሜቴን ‹‹ምን ይሻላል?›› በማለት ስጠይቃት ‹‹ኮሮና እኮ ጩኸት አይወድም›› ከሚል የባለሙያ ምክር ጋር ተንደርድራ ወደ ቤት ከገባች በኃላ ወጥ-እንጨት እና ባዶ ብረት ድስት ይዛ በመመለስ እሱን እያንኳኳች ለአፍታ ያክል ጃዝ ስትጫወትለት ብትቆይም የስሜት ለውጥ ሳይታይበት ቀረ፡፡ ይልቅስ ‹‹የባሕል መድሃኒት የሚያውቅ ደብተራ ካልተጠራልኝ ወይም ደግሞ ቬንትሌተር ካልመጣልኝ በቀር መሞቴ ነው›› እያለ ዐይኑን መግለጥ ይሳነው ጀመር፡፡

በመሆኑም በስድስት መቶ ብር የገዛሁት ዶሮዬ ዐይኔ እያዬ ቢሞት ጸጸቱን ስለማልችለው ካደረበት የጤና እክል በቢለዋ ልፈውሰው አስቤ ‹‹ካራ አምጭልኝማ?›› በማለት እሜቴን ስጠይቃት ‹‹ምን ልታደርግበት?›› አለቺኝ፡፡
‹‹ላርድበት ነዋ! መቼስ አላስፈራራበት››
‹‹የታመመ ዶሮ ማን ሊበላ ነው የምታርደው?››
‹‹ደክሞት እንጂ አሞት አይደለም! ስለዚህ ድካሙ ሳይገለው በፊት ቢለዋውን አምጪልኝና ልቅደመው›› ባልኳት ጊዜም ከዱባይ የሚመጣ የሐበሻ አውራ ዶሮ ያለ ይመስል ‹‹አይሆንም አልኩህ እኮ! የጉዞ ታሪኩ ያልተጣራና የጤና ምርመራ ያላደረገ ዶሮ አልበላም!›› በማለት በአቋሟ ጸናች፡፡ አስከትላም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተከራይንም ሆነ አውራ ዶሮን ከቤት ማስወጣት እንደሚከለክል እያወቀች ‹‹ይህ ዶሮ ወደ ቤቴ ገብቶ በሽታ እንዲያስይዘኝ ስለማልሻ ወስደህ የምትጥልበት ጣል››የሚል ትዕዛዝ አስተላለፈች፡፡

በዚህን ጊዜም ‹‹ይህ ዶሮ ገና ወጣት ስለሆነ ተዛማጅ በሽታ ከሌለበት በቀር ምንም ስለማይሆን እስኪያገግም ድረስ…›› በማለት ላስረዳት ስሞክር ‹‹እሱ እስኪያገግም ፋሲካ ይራዘም?›› ከሚል የሹፈት ጥያቄ ጋር አምሳያውን ለመግዛት ነጠላዋን አጣፍታ ልትወጣ ስትል… የታመመው አውራ ዶሮዬ አክቲቪስት ያሳደገው ይመስል ከተኛበት ተነስቶ ‹‹መንገድ በመዝጋት›› የቀረበለትን ፍትፍት ይበላ ጀመር፡፡

መልካም በዓል!

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in መዝናኛ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top