የግል ዩኒቨርሲቲው ~ ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሰጠው አስገራሚ ድጋፍ
(በድሬቲዩብ ሪፖርተር)
ነገሩ እንዲህ ነው። ቅዳሜ መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የተነሱ ሁለት አውቶቡሶች አዲስ አበባ አየር ጤና እና ኃይሌ ጋርመንት አካባቢዎች የጫኗቸውን ተማሪዎች አወረዱ። በወቅቱ በአውቶቡሱ ሾፌሮችና በተማሪዎች መካከል አለመግባባት ተከስቶ ነበር። አውቶቡሶቹ “አድርሱ የተባልነው አዲስ አበባ ድረስ ብቻ ነው” በማለት ተማሪዎቹን አውርደው ነጎዱ። የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመግታት ሲባል ተማሪዎች ወደቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ መንግሥት በወሰነው መሰረት ወደአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች መሄድ የነበረባቸው የሚዛን ቴፒ ተማሪዎች በአዲስ አበባ በማያውቁት አካባቢ ከምሽቱ 2:00 ሰዓት ገደማ ከአውቶቡሶቹ እንዲወርዱ ሲደረግ ወዲያውኑ ችግር ላይ ወደቁ።
በተለይ በኃይሌ ጋርመንት አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች እንዲሁም የንፋስ ስልክ ላፍቶ የወረዳ 01 ፖሊስ አስተዳደር ተማሪዎችን በመረከብ አስፈላጊውን የማረፊያ እና የምግብ ወጪዎችን ለመሸፈን ሩጫ ውስጥ ገቡ።
አቶ ታፈሰ ሳህሌ እና ጓደኞቻቸው በየፊናቸው እርዳታ ለማሰባሰብ ሙከራ አደረጉ። ይህን የተማሪዎች ችግር እሁድ ዕለት ጠዋት የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩኘ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር እና የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኘረዝደንት ዶ/ር አረጋ ይርዳው ሰሙ።
ዕርዳታም ያደርጉ ዘንድ ከአካባቢው ህብረተሰብ እና ከፖሊስ ወገናዊ ትብብር ተጠየቁ። ዶ/ር አረጋ ለጥያቄው መልስ የሰጡት ያለአንዳች ማንገራገር ወዲያውኑ ነበር። ለተማሪዎቹ የምግብ እና የመኝታ ወጪዎች በሙሉ እንዲሸፈኑ አደረጉ። በመቀጠልም ሁለት አውቶቡሶችን በመከራየት በሁለት አቅጣጫ ተማሪዎቹ ወደአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲሸኙ አድርገዋል።
በዶ/ር አረጋ መልካም ፈቃድ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲም ለተማሪዎቹ የሁለት ቀናት የምግብና የመኝታ ወጪ ከመሸፈኑ በተጨማሪ ለእያንዳንዱ ተማሪ ለምሳ የሚውል አበል በመስጠት አሸኛኘት አድርጓል።
የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሆኑት እነዚሁ 82 ተማሪዎች በሠላም ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘታቸውንም አቶ ታፈሰ ማረጋገጣቸውን ገልፀዋል።
ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የሚዛን ቴፒ ተማሪዎች የገጠማቸውን ጊዜያዊ ችግር “እኔን አይመለከተኝም” ሳይል ፈጥኖ በማስተካከል የግል እና የመንግሥት የትምህርት ዘርፍ አጋርነቱን በተግባር በማሳየቱ በብዙዎች ዘንድ አድናቆት ተችሮታል።