Connect with us

ደመናው አልፎ ብሩህ ቀን ይመጣል …

ደመናው አልፎ ብሩህ ቀን ይመጣል
Photo Facebook

ወንጀል ነክ

ደመናው አልፎ ብሩህ ቀን ይመጣል …

ደመናው አልፎ ብሩህ ቀን ይመጣል፡፡ ያኔም ዳግም እንገናኛለን፡፡ በሄዳችሁበት ሁሉ ራሳችሁንና ወገኖቻችሁን ጠብቁ፡፡” – የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ልብ የሚነካ መልዕክት፤

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን በየትውልድ ስፍራቸው ሊያደርስ ነው፡፡ እዚያ እነሱን በሚወስድ መኪና ወደ ጎንደር የሚመጡ ካሉም ለማምጣት ወስኗል፡፡
****
ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

ስለ ኮሮና ብዙ ማለት ያልቻልኩት ሁሉም ሁሉን ነገር እያለ ስለኾነ ማድመጡ ይበልጣል ብዬ ነበር፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንቅልፍ አጥቼ ያደርኩበትን መልዕክት ለተማሪዎቹ ተናገረ፡፡ ራሴን ከአንዱ ዶርም ሻንጣ ተሸክሞ እንደሚወጣ አንድ ተማሪ አየሁ፡፡ መልእክቱ ልብ ይነካል፡፡

“ደመናው አልፎ ብሩህ ቀን ይመጣል፡፡ ያኔም ዳግም እንገናኛለን፡፡ በሄዳችሁበት ሁሉ ራሳችሁንና ወገኖቻችሁን ጠብቁ፡፡”

ደመናው ከምወደው ግቢ ያለ ቀጠሮዬ ወደ ቀያዬ እጓዝ ዘንድ ሲያስገድደኝ ታየኝ፡፡ ተቋም እንደ ከንፈር ወዳጅ በስስት ሲሸኘኝ አሰብኩት፤ የዚያች ውብ ከተማ ቅጥሮች የናፍቆት አይናቸው እንባ አቅርሮ ተመለከትኩ፤ ደግሞ መልሼ እንዲህ አሰብኩ፤ ብሩህ ቀን ይመጣል፡፡

እራሴን እንደ አንድ ተማሪ መልእክቱ ልቤን እስኪኮረኩር ሀሳቡ በትዝታ ይዞኝ ጭልጥ እስኪል ያደረሰኝ ምኞቱ ነው፡፡ ያኔ ዳግም የመገናኘቱ ምኞት፡፡

እርግጥ ነው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን በየትውልድ ስፍራቸው ሊያደርስ ነው፡፡ እዚያ እነሱን በሚወስድ መኪና ወደ ጎንደር የሚመጡ ካሉም ለማምጣት ወስኗል፡፡ አስቀድሞ ኮሮና ስሙ ከተነሳ ጀምሮ በቅጥሩ ጠብቄ ክፉውን ቀን እሻገራለሁ ያለ ተቋም በስጋቱ ተሸንፏል፡፡ መልካሙ ቀን እስኪመጣ ደመናው እስኪገፈፍ መለያየትን መርጧል፡፡ ብዙ የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ይሄንን ውሳኔ እየተገበሩ ነው፡፡

በዚህ መልእክት የተሸኘ ተማሪ ዳግም ጎንደር መምጣት ይፈልጋል፡፡ ደመናው እስኪያልፍ ሰማዩን አይቶ ምልክቱን በመገመት ክፉውን ቀን ማሳለፍ ደግ ነው፡፡ እንደ ዩኒቨርሲቲው ለሀገሬና ለዓለም ይህ ደመና ይገልጥ ዘንድ የስጋት ጭጋግ ይወገድ ዘንድ እናፍቃለሁ፡፡ እናም እራሴን እንደሚሸኝ ተማሪ ቆጠርኩት፡፡

አሜን አልኩ ዩኒቨርሲቲዬን፤ አሜን አልኩ ከተማዬን፡፡ ቅጥሮችሽን ዳግም አያቸዋለሁ፡፡ ዳግም ዋርካዎችሽ ጥላ እገባለሁ፡፡ ዳግም ጀግናሽ ሐውልት ስር ፎቶ እነሳለሁ፡፡ ቀጠሮዬ እንደተጠበቀ ነው እመጣለሁ የምርቃቴ ፎቶ እነዚያ ውብ የሀገሬ ቅርሶች ቅጥር ይደምቃል፡፡ ፒያሳሽን ሽር ብትን እልበታለሁ፤ አራዳሽን እውልበታለሁ፤ ቅዳሜ ገበያሽን ዳግም ቅዳሜ ብቅ እልበታለሁ፡፡ ቆብ አስጥል እመጣለሁ፡፡ ምኞቴ ብቻ ሳይሆን ጥንቃቄዬ ከዚህ ደመና ያስጥለኛል፡፡

እራሴን እንደ አንዱ ተማሪ አይቼ እንዲህ እላለሁ፤ ልብ ለሚነካው መልእክት መልስ እሰጣለሁ፡፡ እናንተ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለውብ ከተማችሁ፣ ለምትወዱት ቅጥር ለምትናፍቁት ተቋም እንዲህ የሚል መልስ ስጡ፡፡

“ደመናው አልፎ ብሩህ ቀን እንዲመጣ መናፈቅ ብቻ ሳይኾን እንጥራለን፡፡ ያኔ ዳግም እንመጣለን፡፡ በሄድንበት ሁሉ ራሳችንንም ወገናችንንም እንጠብቃለን፡፡ ብርሃን ሲሆን የብርሃን ከተማ በኾነችው ጎንደር የደመናውን ዘመን ትዝታዎች እናወጋለን፡፡”

Click to comment

More in ወንጀል ነክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top