በኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተቋቋመው የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ ጽ/ቤት በመሰብሰብ ነፃነት የጥናት ቡድን የተዘጋጀውን የመሰብስብ፣ ሰላማዊ ስልፍ የማድረግ እና አቤቱታ የማቅረብ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተጨማሪ ግብዓት ለመሰብሰብ ከዘርፉ ባለሙያዎችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የካቲት 7 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ውይይት አካሄደ፡፡
የመሰብሰብ ነፃነት የጥናት ቡድን አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር አብዲ ጂብሪል በውይይት መድረኩ እንደተናገሩት በአገራችን ለረዥም ጊዜ ግልጋሎት ሲሰጥ የነበረው የሰላማዊ ስልፍና ህዝባዊ ስብሰባ ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 3/1983 የነበሩበት መሰረታዊ ክፍተቶች የተጠቀሱ ሲሆን አዋጁ እውቅና የማያስፈልጉና የሚያስፈልጉ ሰልፎችን የማይለይ፣ የሰላማዊ ሰልፍ አዘጋጆች መብትና ኃላፊነት በግልፅ የማይደነግግ፣ የዜጎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ ብዙ ገደቦችን የሚያስቀምጥ መሆኑን ጠቁመው በአዲስ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 30 እና አገሪቱ በተቀበለቻቸው አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግጋት መሰረት በማድረግ ከአሁን በፊት በነበረው አዋጅ የታዩ ክፍተቶችን የሚፈታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል የጥናት ቡድኑ አባልና ረቂቅ አዋጁን ያቀረቡት ዶ/ር ቃልኪዳን ነጋሽ የአዋጁን አላማና ይዘት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ዜጎች ሰላማዊ በሆነ አግባብ የመሰብስብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና አቤቱታ የማቅረብ መብት ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚያበቃ ሁነኛ መሳሪያ መሆኑን ተናግረው አዋጁ በ7 ዋና ዋና ክፍሎች የተዋቀረ መሆኑን እና በአዋጁ ውስጥ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን የቤት ውስጥና የአደባባይ ስብሰባዎችን የማዘጋጀት፣ በስብሰባዎች ሰላማዊ በሆነ አግባብ እና መሳሪያ ሳይዝ የመሳተፍ መብት እንዳለውና ስብሰባዎችን ለማዘጋጀትም ሆነ በስብሰባዎች ለመሳተፍ የመንግሰት ፍቃድ እንደማይጠየቅ በመሠረታዊ መርህ የተካተቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ቃልኪዳን ነጋሽ አክለውም መንግስት በሕገ-መንግስቱ፣ በዚህ አዋጅ እና በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች መሰረት የመሰብሰብ ነፃነትን የማክበር፣ የማስከበር ግዴታዎች ያሉበት ሲሆን ለመሰብሰብ ነፃነት የሚደረግ ጥበቃ ሰላማዊ ስብሳቢዎችን የሚመለከት መሆኑንና በአዋጁ የስብሰባ ተሳታፊዎችና አዘጋጆች መብቶች፣ ግዴታዎች፣ የኃላፊነት ገደብ ያስቀምጣል፡፡
የአደባባይ ስብሰባ ለማዘጋጀት የሚያስብ ማንኛውም ሰው ከስብሰባው 5 ቀናት በፊት ለከተማው ወይም ለወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት የስብሰባውን ዓላማ ፣ቀን ፣ ሰዓትና የቆይታ ግዜ በጽሁፍ የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ በዝርዘር የተካተተ መሆኑን ገልጸው የፀጥታ ሃይሎች ሰላማዊ ስብሰባ መደገፍ፣ መጠበቅ፣ በስምሪት ወቅት ተገቢውን የደንብ ልብስ መልበስ እንዳለባቸው እንዲሁም ማንኛውም ግለስብ፣ ቡድን በግልም ሆነ በጋራ አቤቱታ የማቅረብ መብት ያለው መሆኑን ረቂቅ ሕጉ በግልጽ ይደነግጋል፡፡( ምንጭ፡-ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ)