Connect with us

በትግራይ ክልል ከሚፈለጉ ወንጀለኞች 225 ያህሉ አልተያዙም

በትግራይ ክልል ከሚፈለጉ ወንጀለኞች 225 ያህሉ አልተያዙም
የፌ/ጠ/ዐቃቤ ህግ

ዜና

በትግራይ ክልል ከሚፈለጉ ወንጀለኞች 225 ያህሉ አልተያዙም

በትግራይ ክልል ከሚፈለጉ ወንጀለኞች 225 ያህሉ አልተያዙም

በትግራይ ክልል ስለተፈጸሙ ወንጀሎች እና ስለተከናወኑ የወንጀል ምርመራ ተግባራት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት በኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የሙስና እና የተደራጁ ወንጀል ጉዳዮች ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ፍቃዱ ጸጋ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል እና የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ዘላለም መንግስቴ ናቸው፡፡

መግለጫው ሊሰጥ የቻለው በትግራይ ክልል ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዙ አባላት እና በሌሎች አካባቢዎች የተፈጸሙ ጥቃቶችን ተከትሎ መንግስት በወሰደው የህግ ማስከበር ስራ በወንጀል አፈጻጸም ውስጥ የተሳተፉ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሎ በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራው በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መረጃን ለህዝብ ለመስጠት በማለም ነው፡፡

በክልሉ በተፈጸሙ ወንጀሎች የተጠረጠሩ እና የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸው ሰዎች ብዛት 349 መሆናቸውን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግስቴ ከነዚህ ውስጥ 96 የሚሆኑት የህወሃት ቁልፍ አመራሮች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡  

በአሁኑ ጊዜም ተፈላጊ ከሆኑት አጠቃላይ ተጠርጣሪዎች 124 የሚሆኑት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ሲሆን ሌሎቹን በቁጥጥር ስር አውሎ በህግ ለመጠየቅ ከመከላከያ እና በአካባቢው ካሉ የጸጥታ ኃይሎች ጋር በጥምረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የወንጀል ምርመራ ስራው ሰፊ በመሆኑ ጥልቅ የሆነ ምርመራ መከናወኑት የገለጹት ም/ል ኮሚሽነር ጄኔራሉ ተጠርጣሪዎቹ በወንጀል መሳተፋቸውን የሚያመላክቱ እና የሚያረጋግጡ ከ 680 በላይ የሰው እና የሰነድ ማስረጃ የማሰባሰብ ስራም መሰራቱን አስረድተዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ  አቶ ፍቃዱ ጸጋ በበኩላቸው የወንጀል ቡድኑ ዋናውን ወንጀል ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ይፈጽመው እንጂ ላለፉት 27 ዓመታት ይዞት ከነበረው ስልጣን ለቆ ወደ ትግራይ ክልል ከተመለሰበት ጊዜ ጀምሮ በከፍተኛ የዝግጅት ሂደት ውስጥ የቆየ መሆኑን ገልጸው ከፌዴራሉ መከላከያ ሰራዊት አወቃቀር ጋር የሚመሳሰል አደረጃጀትን በመዘርጋት ለውጊያ ብቁ የሆኑ የልዩ ሀይል አባላትን ሲመለምል እና ሲያሰለጥን መቆየቱን አረጋግጠዋል፡፡ 

በ2011 እና በ2012 ዓ.ም ብቻ ከ84 ሺ በላይ የሚሆኑ የልዩ ኃይል አባላትን መልምሎ ለውጊያ አዘጋጅቶ እንደነበር አክለው የገለጹት አቶ ፈቃዱ አባላቱን በ8 እዞች፣ 23 ሬጅመንቶችን በቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባል የነበሩ ጡረተኞችን በማካተት የዝግጅት ስራ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በትግራይ የሰሜን ዕዙን ጥቃት ጨምሮ፣ የመሰረተ ልማት ማፈራረስ፣ ከተቀመጠው ገደብ በላይ ገንዘብ ከባንኮች እንዲወጣ ማድረጉ፣ የሮኬት ጥቃት ማድረሱ ሲፈጸም የስራ አስፈጻሚው አባላት በጋራ ተቀምጠው ተወያይተው የሚወስኑት ጉዳይ እንደነበር ከተሰበሰቡት የሰው እና የሰነድ ማስረጃ መረዳት ይቻላልም ብለዋል፡፡ 

የወንጀል ቡድኑ በትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች ምክንያት የሚሆኑ ረብሻዎችን በገንዘብ ሲደግፍ የነበረ ሲሆን የገንዘብ አደጋገፉም በዘፈቀደ የሚደረግ ሳይሆን የሁከት ፈጠራው ውጤታማነት ተመርምሮ እና ሁከቱን ለማድረግ ያቀደው እና የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄ ያቀረበው ግለሰብ ወይም ቡድን በአካል ቀርቦ አብራርቶ ሲታመንበት የሚፈቀድ ነበር ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ፡፡

ከማይካድራው ዘግናኝ ጥቃት ጋርም በተያያዘ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ሲገልጹ ብሄርን መሰረት ባደረገ መልኩ በተፈጸመው የሰዎች ግድያ የተሳተፉ 279 ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን ከተሰበሰቡ ማስረጃዎች መረዳት የተቻለ ሲሆን አብዛኛው ተጠርጣሪዎች ወደ ሱዳን ያመለጡ እና 36 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራቸው ተጠናቆ የክስ ዝግጅት የሚቀረው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ጥቃት ጋር በተያያዘ የሟቾች ቁጥር ከጤና ሚኒስቴር የተላከው የሀኪሞች ቡድን ከ117 ጉድጓዶች የተገኙ አስክሬኖችን መርምሮ የሟቾቹን ብዛት እና የሞት ምክንያት እስኪያሳውቀን ድረስ ትክክለኛው በጥቃቱ የሞቱ ሰዎችን ብዛት መግለጽ ለጊዜው ባይቻልም መሬት ባለው እውነት እና በየሚዲያው በተገለጸው መካከል ልዩነት እንዳለ አቶ ፈቃዱ በማብራሪያቸው አስረድተዋል፡፡ 

መረጃዎቹን በሰጡ የሚዲያ ተቋማት ዘጋቢዎች ጋር በተደረገ የማጣራት ስራ በወቅቱ አስክሬኖች ይሸቱ ስለነበር ተጠግቶ ለመቁጠር የማይቻል በመሆኑ ቁጥሩን የገለጽነው በግምት ነበር ብለው እንደተናገሩም አክለው ተናግረዋል፡፡

አቶ ፍቃዱ የምርመራውን ስፋት እና ሁኔታ ሲያብራሩም የወንጀል ምርመራው ከጥቅምት 24 ቀን  2013 ዓ.ም በኋላ የተፈጸሙትን ወንጀሎች ብቻ ሳይሆን ተጠርጣሪዎቹ በስልጣን ላይ በነበሩባቸው 27 ዓመታት የፈጸሟቸውም ወንጀሎች የሚጣሩ ሲሆን በህይወት በተገኙት ላይ የህግ ተጠያቂነትን ለማሰፈን እንዲሁም በሞቱት ላይ ደግሞ ምርመራው ቀጥሎ ነገር ግን ለጥናት እና ምርምር ስራዎች ወይም ለዕርቀ ሰላም ጉዳዮች ስራ እንዲውል ታሪክን ለማኖር ጥረት ይደረጋለ ብለዋል፡፡

በስተመጨረሻም ጋዜጠኞች ላነሷቸው ጥያቄዎች የስራ ኃላፊዎቹ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ቀጣይ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው የመከላከል መብታቸው ተጠብቆላቸው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ የጋራ ጥረት ይደረጋል ተብሏል፡፡(የፌ/ጠ/ዐቃቤ ህግ)

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top