ኢትዮጵያ ሰላም ናት ወይ!
(አሳዬ ደርቤ ~ ለድሬ ቲዩብ)
‹‹ሰላም ናት ኢትዮጵያ›› የሚል መልዕክት ያዘለ ኮንሰርት በመጭው ቅዳሜ ሊዘጋጅ መሆኑን የሚገልጽ ዜና እየተንሸራሸረ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሄን ኮንሰርት የሚያዘጋጁትም ሆነ በኮንሰርቱ ላይ የሚሳተፉት አርቲስቶች ሰላምንም ሆነ ኢትዮጵያን የማያውቁ የሌላ ፕላኔት ከያኒያን ካልሆኑ በቀር ከሦስት ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎች ከቀያቸው በተፈናቀሉበት፣ ሦስት ዞኖች በአሸባሪዎች ቁጥጥር ስር በዋሉበት፣ በመላው ኢትዮጵያ የሰላም አየር በነጠፈበት፣ ማንነትን መሠረት ባደረገ ጥቃት የንጹሐን ሕይወት እንደ ጤዛ በሚረግፍበት፣ የጥይት ጩኸት ርችት ሆኖ በየስፍራው በሚሰማበት ሁኔታ ‹‹ሰላም ናት ኢትዮጵያ›› የሚል ኮንሰርት ማዘጋጀት በአገር ፍርሰት እና በዜጎች ሕይወት ላይ እንደ መጨፈር የሚቆጠር ነው፡፡
በደዌ ተለክፋ የተኛች እናትን ማሳከምና ማስታመም ባይቻል እንኳን ሕመሟን መጋራት ሲገባ ከተኛችበት አልጋ ወርውሮ፡-
‹‹ታምማለች እያለ – ቢያወራም ጎረቤት
እንቅልፍ ይዟት እንጂ- እናቴ ሰላም ናት›› እያሉ አልጋዋ ላይ ከመጨፈር አይተናነስም፡፡
ወይ ደግሞ በመጭው ቅዳሜ አርቲስቶቹ የሚቃርቡት ዘፈን “ዶንት ወር ቢ ሃፒ” እንደሚለው ሙዚቃ እንዲህ የሚል ግጥም የያዘ መሆን አለበት፡፡
በፈርዖን ድጋፍ- ግድቡን ሊያከሽፍ- በተነሳ ሽፍታ
ቤኒሻንጉል ክልል- መተከል ድባጤ- ቢነጥፍም ጸጥታ
ኢትዮጵያን ለማፍረስ- በተደራጀ አንጃ
በወለጋ ምድር- ዜጎች ቢቀጠፉም- በፈሪ ጠመንጃ
ትግራይ፣ አማራ፣ አፋር- አሸባሪ ቡድን- ባስነሳው ጦርነት
የብሱ ቢታመስም- ሕዋዉ ቢታረስም- በታንክ እና ሮኬት
የእኛ ኢትዮጵያ ግን- አሁንም ሰላም ናት፡፡›› ክክክክ
በበኩሌ ግን ኪነ ጥበብ እውነትን መናገር ቢሳናት እንኳን ውሸትን ይዛ አደባባይ ላይ መገኘት የለባትም ብዬ አስባለሁ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ሰላም ናት›› የሚል ባነር ሰቅሎ ሙዚቃ ማጫወት ግን ከእውነት ብቻ ሳይሆን ከምኞትም ያፈነገጠ ነው፡፡ ማደሪያቸውን ምሽግ ውስጥ ባደረጉ ወታደሮቻችን እና ጎዳና ላይ በወደቁ ዜጎቻችንን ሞራል ላይ እንደመረማመድ የሚቆጠር ነው፡፡
ስለዚህ ኮንሰርቱ ከፍተኛ አገራዊ ፋይዳ ያለው የአዲሱ ምዕራፍ ዋነኛ እቅድ ከሆነ ‹‹ኢትዮጵያ ሰላም ናት›› በሚለው ፈንታ ‹‹ኢትዮጵያ ሰላም ትሆናለች›› ወይም ደግሞ ‹‹አዲስ አበባ ሰላም ናት›› በሚል መሪ ቃል ቢከናወን ሳይሻል አይቀርም፡፡
መልዕክቱ ኢትዮጵያን ማተራመስ ለሚፈልጉ የውጭ ሃይሎች ከሆነ ደግሞ ጦር ሜዳ ላይ ቁሞ ‹‹ኢትዮጵያ ሰላም ናት›› ከማለት ይልቅ እዚያው አነሱ ምድር ላይ ድግሱን አዘጋጅቶ ማብሸቅ ወይም ደግሞ መሞዘቅ የሚሻል ይመስለኛል፡፡ በተረፈ ግን አገራችንን ሰላም የነሳውን አሸባሪ ድባቅ መምታት ከቻልን ባሁኑ ሰዓት የተቃወምነውን መሪ ቃል መስቀል አደባባይ ላይ ሰቅለን ‹‹ኢትዮጵያ ሰላም ናት›› ማለታችን አይቀሬ ነው፡፡ የዚያ ሰው ይበለን ብቻ!