ወንድማማቾቹ በፈጸሙት የመግደል ሙከራ ወንጀል በ7ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተፈረደባቸዉ
ተከሳሾቹ ቅባቱ አጋዊ እና ጸጋዬ አጋዊ ይባላሉ፡፡ የ23 እና የ18 ኣመት ዕድሜ ያላቸው ወጣቶች ናቸዉ፡፡
የዐቃቤ ህግ ክስ እንደሚያስረዳው ወንድማቾቹ ተከሳሾች በኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 27/1/፤ 32/1/ሀ እና 540 ስር የተደነገገዉን በመተላለፍ ሚያዚያ 20 ቀን 2011ዓ.ም ከምሽቱ 2፡30 ሲሆን በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ልዩ ቦታዉ መገናኛ ቢታኒያ ሆቴል ዉስጥ 1ኛ ተከሳሽ ቅባቱ አንገቱን ዝቅ አድርጎ በሀይል ሲይዘዉ ታናሽ ወንድሙ ጸጋዬ አጋዊ በጩቤ ጭንቅላቱን በመዉጋት ጉዳት አድርሶበታል፡፡
በዚሁም መሰረት ሁለቱም ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ ሆነዉ በፈጸሙት የሰዉ መግደል ሙከራ ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ተከሳሾቹ ህዳር 18 ቀን 2012ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት ቀርበዉ የተከሰሱበት የወንጀል ድርጊት ላይ የእምነት ክህደት ቃላቸዉን እንዲሰጡ ተጠይቀው የወንጀል ድርጊቱን እንዳልፈጸሙ፤ ጥፋተኛም አይደለንም ሲሉ ቃላቸዉን ለፍርድ ቤቱ ሰጥተዋል፡፡
ዐቃቤ ሕግም የወንጀል ድርጊቱን መፈጸም እንዲያስረዱለት የግል ተበዳይን ጨምሮ አራት የሰዉ ምስክሮችንና የደረሰዉን የጉዳት መጠን የሚገልጽ ከናሽናል አጠቃላይ ሆስፒታል የተገኘ የህክምና ማስረጃን በማቅረብ እና በማሰማት ከበቂ በላይ ያስረዳ በመሆኑ ተከሳሾች በማስረጃ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡ ይሁንና ተከሳሾች የቀረበባቸውን ክስ እና ማስረጃ ማስተባበል ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
በዚህም መሰረት የካቲት 17 ቀን 2013 ዓ.ም የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሾች በሌሉበት እያንዳንዳቸዉ በ7 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡ ፖሊስም ተከሳሾችን ይዞ ቅጣቱን ተፈጻሚ እንዲያደርግ ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡
ተከሳሾች የዋስትና መብት ተጠብቆላቸው ክርክሩን ከማቆያ ውጭ ሆነው የሚከራከሩ በመሆናቸው ጥፋተኛ እንደሚባሉ በመገመት ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ ከቀጣዮች የፍርድ ቤት ቀጠሮዎች ላይ በመቅረታቸው በሌሉበት ሊወሰን ችሏል፡፡
ፍርደኞቹ በማንኛውም ጊዜ በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ማረሚያ ቤት እንደሚላኩ የሚያውቁ በመሆኑ በቀጣይ የሚኖራቸው ኑሮ ከሰቀቀን ያልተለየ ሊሆን ከመቻሉም በላይ ፍርድ በተሰጠበት እለት በችሎቱ ቢገኙ ኑሮ ቅጣቱ እንዲቀልላቸው ሊያነሱ የሚችሉትን የቅጣት አስተያየት ማንሳትም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
ለጊዜው ይሁን እንጂ አድራሻን በመለዋወጥ እና ከፖሊስ ጋር አባሮሽ በመጫወት ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ የሚደረግ ጥረት አዋጪ አለመሆኑን ከዚህ ቀደም በተለያዩ ዜናዎቻችን በተጨባጭ ለማሳየት ሞክረናል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ፖሊስ ከተበዳይ እና ከማህበረሰቡ ጋር በጋራ በመሆን ተከሳሾችን በቁጥጥር ስር አውሎ ተገቢውን የማረም ስራ እንዲሰራ ተገቢውን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡(የፌ/ጠ/ዐቃቤ ህግ)