ከሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተጠርጣሪዎች መካከል ላምሮት ከማል እንድትለቀቅ ሌሎቹ ደግሞ እንዲከላከሉ ተወሰነ
በድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከነበሩት መካከል አንዷ የሆነችው ላምሮት ከማል በነጻ እንድትለቀቅ ፍርድ ቤት ወሰነ።
በግድያው ተጠርጥረው መዝገብ ከተከፈተባቸው አራት ግለሰቦች ውስጥ ላምሮት ከማል ግድያውን በማመቻቸት ተጠረጥራ የነበረ ሲሆን ፍርድ ቤቱ በወንጀል ድርጊቱ ውስጥ ተሳትፎዋን የሚያረጋግጥ የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃ ዐቃቤ ሕግ አለመቅረቡን በመግለጽ ነው እንድትለቀቅ የወሰነው።
ዛሬ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ወንጀል ሁለተኛ ምድብ ችሎት የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የሰው ማስረጃና የሰነድ ማስረጃ ከመረመረ በኋላ ነው ብይን የሰጠው።
ፍርድ ቤቱ አንደኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ የድምጻዊ ሃጫሉን ግድያ መፈፀሙን ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ መርምሮ ማረጋገጡን ገልጿል።
አንደኛ ተከሳሽን በተመለከተ የፖለቲካ ተልዕኮን ከግብ ለማድረስ ሰዎችን በመግደል በመንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠርና ሕዝብን ለማሸበር የሸኔ አባል ከሆነው ገመቹና ሌላ ለጊዜው ካልተያዘ ግለሰብ ተልዕኮ በመቀበል ሃጫሉን መግደሉን ዐቃቤ ሕግ ያቀረበው የሰውና የሰነድ ማስረጃ አረጋግጧል ብሏል።
ከዚህ ውጪም ይህ ተከሳሽ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እያለ እንዴት ወንጀሉን እንደፈፀመ ለፖሊስ በሚያሳይበት ወቅት ይህን ድርጊቱን እነዴት እንደፈፀመ በቪዲዮና በድምጽ ተቀርጾ ማሳየቱን ገልጿል።
ከዚህም ውጪ ግለሰቡ ድምጻዊ ሃጫሉን የገደለበት ሽጉጥ ከአንደኛ ተከሳሽ ቤት መገኘቱ እንዲሁም ወንጀሉ የተፈፀመበት ቦታ የተገኙት ቀለህና እርሳስ ከሽጉጡ ውስጥ የተተኮሱ መሆናቸውን በተካሄደው የፎረንሲክ ምርምራ መረጋገጡን ፍርድ ቤቱ ተናግሯል።
በዚሁ መረት የአንደኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ ጉዳይ ሽብርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 በመተላለፉ እንዲታይና እንዲከላከል ተወስኗል።
ሁለተኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹ የፖለቲካ አመለካከትን ከግብ ለማድረስ ሰዎችን በመግደል መንግሥት ላይ ጫና በመፍጠርና ሕዝብን ለማሸበር ድርጊቱን መፈፀሙን ዐቃቤ ሕግ ያቀረበው የሰውና የሰነድ ማስረጃ እንዳልተረጋገጠ ተናግሯል።
ይሁን እንጂ ሁለተኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹ አንደኛ ተከሳሽ የሆነው ጥላሁን ያሚ በሚፈጽመው የዝርፊያ ድርጊት እንዲተባበረው አስማምቶ በግድያው ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን እንዳደረገው መረጋገጡ ተገልጿል።
ስለዚህ የግድያ ድርጊቱን ለመፈፀም አውቆና ተዘጋጅቶ ባለመሳተፉ ጉዳዩ በወንጀል ሕግ 1996 በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 540 ስር እንዲታይና እንዲከላከል ተወስኗል።
በሌላ በኩል ሦስተኛ ተከሳሽ አብዲ አለማየሁ ድርጊቱን መፈፀሙ ያልተረጋገጠ ሲሆን፣ ነገር ግን ድርጊቱ በሚፈፀምበት ወቅት አይቶ ለሕግ አካል ባለማሳወቁ ጉዳዩ በ1996 በወጣው የወንጀል እግ አንቀጽ 443/1ሀ ስር እንዲታይና እንዲከላከል ተወስኗል።
በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ከአንድ እስከ ሦስት ያሉትን ተከሳሾች ጥላሁን ያሚ፣ ከበደ ገመቹ እና አብዲ አለማየሁ የመከላከያ ማስረጃን ለመስማት ለመጋቢት 20 እና 21/2013 ቀጠሮ ይዟል።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ አዲስ አበባ ውስጥ የተፈጸመውን የታዋቂውን ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተከትሎ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተከሰተ አለመረጋጋት ከ150 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በመቶ ሚሊዮኖች የሚገመት ንበረት መውደሙ ይታወሳል።
ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና አመራሮችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር በወቅቱ ተገልጿል።(BBC)