በዉንብድና ወንጀል ክስ የተመሰረተበት ወጣት በጽኑ እስራት ተቀጣ
ዋሪዮ እሹ ዋቤ ዕድሜው 22 ዓመት ሲሆን ቋሚ የመኖሪያ ሰፈርም ሆነ ስራ የለውም፣ ዋሪዮ እሹ በአዲስአበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጎዳና ተዳዳሪ በመሆኑ ምክንያትም ወጣትነቱን ራሱንም ሆነ አገሩን ለመለወጥ አልተጠቀመበትም ነገር ግን በተቃራኒው አላፊ አግዳሚውን ባሻዉ ጊዜ እያስፈራራና እየቀማ መኖርን ምርጫዉ አድርጓል፡፡
ታድያ ወጣቱ ግንቦት 17 ቀን 2011ዓ.ም ከጠዋቱ 4፡00 ሲሆን በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 መላጣ ጋራ ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ የግል ተበዳይ ዶ/ር ይሄይስ አይተንፍሱን ከነልጁ በአንድ ክፉ አጋጣሚ አገኘዉ፡፡ አጋጣሚውን ተጠቅሞም በኪሱ የያዘዉን ስለት መዞ እሱ የፈለገዉን ለመፈጸም ወደሚያስችለዉ አቅጣጫ እንዲሄድ አስገደደዉ፡፡
ዶ/ር ይሄይስ ግን ለጊዜዉም ቢሆን ራሱን መከላከልን መረጠ ግን አልተቻለውም፣ ዋሪዮ በዚህ ጊዜ ነበር የያዘዉን ስለታማ ቢላዋ ወደ ዶ/ር ይሄይስ ግራ እጅ የሰነዘረዉና የግራ እጁን ጣት የቆረጠዉ ፡፡
ተከሳሽ በዚህ አላበቃም በድንጋይ የግል ተበዳይን ታፋ በመምታት እንዲሁም የግል ተበዳይ ልጅን በማስፈራራት ያለ የሌለ የዉንብድና አቅሙን ተጠቅሞ የግል ተበዳይ ንብረት የሆነና የዋጋ ግምቱ 16‚000 የኢትዮጵያ ብር የሆነ ሳምሰንግ የእጅ ሞባይል ስልክ ቀምቶ ወስዷል፡፡
ዐቃቤ ህግም በወንጀል ህጉ አንቀጽ 671/1/ለ ስር የተደነገገዉን በመተላለፍ ከባድ የዉንብድና ወንጀል መፈጸሙን በበቂ ማስረጃ አረጋግጦ በተከሳሽ ላይ ክስ መስርቶበት ጉዳዩ በክርክር ላይ ቆይቷል፡፡
ተከሳሽ ምሐምሌ 3 ቀን 2011 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ወንጀል ችሎት ቀርቦ የእምነት ክህደት ቃሉን ተጠየቀ ሆኖም ወንጀሉን እንዳልፈጸመና ጥፋተኛም አለመሆኑን ገልጾ የዋስትና መብቱ እንዲጠበቅለት ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቀረበ፡፡
ይሁን እንጂ ዐቃቤበ ህግ ተከሳሹ በተመሳሳይ ጥፋት ክስ እንዳለበትና በዋስትና ቢወጣ ሊጠፋ እንደሚችል ለፍርድ ቤቱ አሰምቶ ዋስትናዉን ተቃዉሟል፡፡
ፍርድ ቤቱም ዐቃቤ ህግ ያሰማዉን ተቃዉሞ ተቀብሎ ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም ምስክሮችን አሰምቶ ተከሳሽ በተከሰሰበት ወንጀል እንዲከላከል ብይን አስተላልፏል፡፡ በመሆኑም አንድ የመከላከያ ምስክርም ቀርቦ መስክሯል፡፡ ሆኖም ፍርድ ቤቱ የቀረቡለትን ማስረጃዎች ግራና ቀኝ መርምሮ ተከሳሽ ጥፋተኛ ነዉ ሲል ብይን ሰጥቷል፡፡
በዚህም መሰረት ጥር 24 ቀን 2013 ዓ.ም ባስቻለዉ ቦሌ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሽን በ7 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡(የፌ/ጠ/ዐቃቤ ሕግ)