ዶናልድ ትራምፕ በፕሬዝደንታዊ ምርጫ መሸነፋቸውን አምነው እንዲቀበሉ ጉትጎታው እየበዛባቸው ነው
ትራምፕ “እንቅልፎ” እያሉ ያንጓጥጧቸው በነበሩት የ78 ዓመቱ ፖለቲከኛ ጆ ባይደን በሰፊ ልዩነት መሸነፋቸው የእግር እሳት ሆኖባቸዋል።
በአሜሪካ ታሪክ ታይቶም በማይታወቅ ሁኔታ ሽንፈታቸውን እስከዛሬ በጸጋ ለመቀበል እያመነቱ ያሉት ዶናልድ ትራምፕ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የገዛ ወዳጆቻቸው ሽምግልና እየሄዱባቸው ነው።
አሁን ትራምፕን ለማሳመን አዲስ ጥረት ከጀመሩት ሰዎች መካከል የትራምፕ የምንጊዜም አጋርና ቀኝ እጅ ናቸው የሚባሉት ክሪስ ክሪስቲ ይገኙበታል።
የቀድሞው የኒው ጀርዚ ገዥ ክሪስ ትራምፕ የምርጫ ውጤቱን ለመቀልበስ ፍርድ ቤት መሄዳቸው “ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነው” ብለዋል። “የሚሻለው ፕሬዝዳንቱ የመጣውን ውጤት በጸጋ መቀበል ነው።”
በርካታ የሪፐብሊካን አጋሮቻቸው ዶናልድ ትራምፕ በየግዛቱ እየሄዱ የክስ ዶሴ በማስከፈት ፍርድ ቤትን ሥራ ማስፈታታቸውን አልወደዱላቸውም።
ባለፈው ቅዳሜ ትራምፕ በፔኒሲልቬኒያ ግዛት የምርጫውን ውጤት ውድቅ ለማድረግ ያስገቡትን ማመልከቻ ዳኛው ውድቅ አድርገውባቸዋል።
ይህም ማለት ዛሬ ሰኞ የፔኒሲልቬኒያ ግዛት ለጆ ባይደን የአሸናፊነት ሙሉ የእውቅና ሰርተፍኬት ታስረክባለች ማለት ነው። ትራምፕ በዚያች ወሳኝ ግዛት የተሸነፉት በ80ሺ ድምጽ ልዩነት ነው።
አሁን ትራምፕን ለማግባባት እየሞከሩ ካሉ ሰዎች በቀዳሚነት የሚወሱት ክሪስ ለኤቢሲ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ምርጫውን ለመቀልበስ የሚደረገው የፍርድ ቤት ክስ ብሔራዊ ውርደት ነው ሲሉ ተችተውታል።
“የትራምፕ ደጋፊ ነኝ። ለሱ ሁለት ጊዜ ድምጽ ሰጥቻለሁ። ነገር ግን ምርጫ ሲባል መሸነፍም ማሸነፍም ያለ ነገር ነው። አንዱን ውጤት ብቻ መፈለግ ትክክል አይደለም” ብለዋል ክሪስ።
ሚስተር ክሪስ ትራምፕ በ2016 ለፕሬዝዳንትነት እጩ ሲሆኑ ድጋፍ የሰጧቸው የመጀመርያው ታዋቂ ባለሥልጣን ናቸው። በዚህ ዓመትም ቢሆን ትራምፕ ከጆ ባይደን ጋር ለነበራቸው ክርክር ፕሬዝዳንቱን ያዘጋጇቸው የነበሩ ሰው ናቸው።
ዶናልድ ትራምፕ ምክራቸውን ሊሰሙ ይችላሉ ተብለው ከሚታሰቡ ሰዎች አንዱ እኚህ የቀድሞ የኒው ጀርሲ ገዥ ሚስተር ክሪስ ይገኙበታል።
ትናንትና እሑድ ሌሎች የሪፐብሊካን የትራምፕ አጋሮችም ዶናልድ ትራምፕ ሽንፈታቸውን እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሜሪላንድ ገዥ ላሪ ሆጋን ለሲኤንሴን እንደተናገሩት ትራምፕ ሽንፈትን አላምን ማለታቸው አሜሪካ አንዳች ታዳጊና ድሀ አገር አስመስሏታል ሲሉ ቀልደዋል።
የሜሪላንዱ ገዥ ላሪ ከዚህ አስተያየታቸው ቀደም ብሎ በትዊተር ሰሌዳቸው “ትራምፕ ጎልፍ ጨዋታውን ገታ አድርገው ሽንፈታቸውን ቢቀበሉ” ሲሉ ጽፈዋል።
ይህ በአንዲህ እያለ የጆ ባይደን ቡድን መንግሥት ለመሆን ዝግጅቱን እያጧጧፈው ይገኛል።
ነገ ጆ ባይደን አንዳንድ ለካቢኔ ያጯቸውን ሰዎች ስም ያሳውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለጊዜው ባይረጋገጥም ጎምቱው ዲፕሎማት አንቶኒ ብሊንከን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይሆናሉ እየተባለ ነው። የ58 ዓመቱ አንተኒ ብሊንከን በኦባማ ጊዜ በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉ ሰው ናቸው።. (BBC)