ከአዲሱ መንግሥት የምጠብቀው…
(ፋሲል የኔዓለም)
ከአዲሱ መንግስት ብዙ ነገሮችን እንጠብቃለን። ለወደፊቱ አንድ በአንድ እያነሳሁ የሚሰማኝን ለመተንፈስ እሞክራለሁ። አንዳንድ ስለ ነጻ መንፈስ ያልገባቸው ሰዎች፣ የእኔ ብዕር የእኔን አዕምሮ ሳይሆን፣ የሌላ ሰው አዕምሮ ያመነጨውን ሃሳብ የሚጽፍ ይመስላቸዋል።
ለእነዚህ ሰዎች የኒቼን ስድብ ይዘዝባቸው ከማለት ውጭ ሌላ የምለው የለኝም። ኒቼ እንዲህ አይነት ነጻ አስተሳሰብ ለማይገባቸው ሰዎች፣ ተራራ የሚያክል ስድብ ጽፎላቸው አልፏል። እኔ የምጽፈው ትንሿ አዕምሮዬ ከምትፈበርካቸው ትንንሽ ሃሳቦች መካከል አንዷን ትንሽዬ ሃሳብ ብቻ መዝዤ ነው።
የሌላ ሰው አዕምሮ የወለደውን ሃሳብ ስወስድ በትምህረተ ጥቅስ አስቀምጣለሁ። እናም እኔ፣ እኔ ነኝ። እንደኔ እንድታስቡ እደማላስገድዳችሁ ሁሉ፣ እናንተም እንደናንተ እንዳስብ አታስገድዱኝ። እኔም እናንተም ነጻ መንፈሶች ነው። በነጻነት አስበን በነጻነት እንጻፍ።
እንግዲህ ዛሬ የምጽፈው አዲሱ መንግስት በሌብነት ላይ ሰይፉን እንዲያነሳ ለመጠየቅ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት አይነት ሌቦች ይታዩኛል፤ የጓዳና የአደባባይ። የጓዳ ሌቦች የሰረቁትን ለራሳቸው ብቻ የሚጠቀሙ ናቸው። ምናልባት ጥቂት ዘመዶቻቸውንም ሊጠቅሙ ይችላሉ።
“ገንዘብ ከየት አመጣችሁ?” እንዳይባሉ አንገታቸውን ደፍተው፣ ደሃ መስለው በፍርሃት ይኖራሉ። ቤታቸው ግን በተሰረቀ ሃብት ሙሉ ነው። በዚህ ስር የሚመደቡት ብዙ ጊዜ ባለስልጣናት ወይም ሙያቸውን ተጠቅመው በስርቆት የከበሩ ናቸው።
የአደባባይ ሌቦች በተቀራኒው ሰርቀው ከህዝብ ጋር የሚካፈሉ ናቸው። ለጠየቃቸው ሰው ሁሉ ገንዘብ ይበትናሉ። ገንዘብ በሚፈለግበት ቦታ ሁሉ ቀድመው ፊት ይሰለፋሉ። አንዱ ጋ 10 ሺ ሌላው ጋር 10 ሚሊዮን ይረጫሉ። እንጠየቃለን ብለው አይፈሩም።
ከባለስልጣን እስከ ተራው ህዝብ አነካክተውታልና። ጥያቄ እንኳን ቢመጣ የበላው ሰው ሁሉ ሰምቶ እንዳልሰማ እየሆነ አፉን ለጉሞ ይቀመጣል እንጅ አጋልጦ አይሰጣቸውም። ያጎረሱት ህዝብ “ያ ደግ ሰው፣ ያ የደሃ አባት ታስረ” እያለ እንደሚያዝንላቸው ያውቃሉ ። ህዝባዊ ድጋፍ ያላቸውን ሌቦች ደፍሮ የሚያስር ሰው አይኖርም።
የእነዚህ ሌቦች ኔትወርክ ጠንካራ ነው። ከታች እስከ ላይ መረጃ አቀባዮች አሏቸው። ለሁሉም እንደ ድርሻውና እንደ አስተዋጾው ይከፍላሉ። የሚረጩት ገንዘብ ቢያልቅባቸው እንኳን ከየትኛውም ባንክ መበደር ይችላሉ። አላበድርም የሚል ባንከር ካለ ዋጋውን ያገኛል። የአደባባይ ሌቦች 10 ሚሊዮን ሰጥተው፣ 100 ሚሊዮን በሌላ መንገድ ይቀበላሉ።
የአገሬ ሰው የሚያወግዘው፣ ሰርቆ ለብቻው የሚበላውን የጓዳ ሌባ እንጅ ፣ ሰርቆ ህዝብን እያካፈለ የሚበላውን የአደባባይ ሌባ አይደለም። ማን ሰርቆ ያካፍላል የሚለውን እንጅ፣ ስርቆትን ራሱን አይጸየፍም። በእኛ አገር መስረቅ ወንጀል አይደለም።
ወንጀል የሚሆነው፣ የሰረቀው ሰው የዘረፈውን ለብቻው የሚበላ ከሆነ ብቻ ነው። የሰረቀውን ሃብት ለህዝብ አካፍሎ ከበላ፣ ሰውየው ሌባ ሳይሆን ቢዝነስ ሰሪ ተብሎ ይሞካሻል።
የአደባባይ ሌቦች ፖለቲካውን መጠቀም ይችሉበታል። በተለይ ብሄርተኝነት የወንጀላቸው መሸፈኛ ትልቅ ድንኳናቸው ነው። በዚህ የሌቦች ጎራ የሚመደቡት በአብዛኛው ነጋዴዎች ናቸው።
አዲሱ መንግስት የጎዳናና የአደባባይ ሌቦችን በመዋጋት በኩል ትልቅ የቤት ስራ ይጠብቀዋል። ያ ካልሆነ፣ አንዱን ወንጀለኛ ቢያጠፋ እንኳን በሌላኛው ወንጀለኛ አንገቱን መታነቁ አይቀርም። ልክ እንደ ላቲን አሜሪካ ፖለቲካ። ወይም እንደ ጣሊያን ማፊያዎች።