Connect with us

ያለማቋረጥ የሚያንኳኳው ሞጋች

Social media

ነፃ ሃሳብ

ያለማቋረጥ የሚያንኳኳው ሞጋች

ያለማቋረጥ የሚያንኳኳው ሞጋች
(ዮሐንስ መኮንን)

ከ25 ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆነ ዶክተር (ከአሁን በኋላ “ሞጋቹ” እያልኩ እጠራዋለሁ) የሕግ ግንዛቤውን ለማሳደግ ከማስተማር ሥራው ጎን ለጎን በዩኒቲ ኮሌጅ (አሁን ዩኒቨርስቲ ሆኗል) በምሽት መርሐግብር የሕግ ትምህርት መከታተል ይጀምራል።

በወቅቱ ተማሪዎች ሁሉ የሚፈሩት የ”ኮንትራት ሕግ” ትምህርትን የሚያስተምር ኮስታራ መምህር ይገጥመዋል።

ትምህርት በተጀመረ ሰሞን መምህሩ ክፍል ከገባ በኋላ ከሥራ ወጥተው በትራንስፖርት ችግር ተሯሩጠው ጥቂት ደቂቃዎችን አርፍደው የደረሱ ተማሪዎች በር ያንኳኳሉ። ይህ ሕግን ለተጨማሪ ዕውቀት የሚማረው “ሞጋቹ ተማሪ” አፈፍ ብሎ ለተማሪዎቹ የክፍሉን በር ሊከፍት ሲነሳ መምህሩ በቁጣ “እንዳትከፍትላቸው መግባት አይቻልም” ይላል። ሞጋቹም የሕግ መምህሩን “አንተ የኮንትራት ሕግ መምህራችን ነህ።

ተማሪዎቹ ለዩኒቲ ኮሌጅ ገንዘብ ከፍለው ሲመዘገቡ የገቡበት ኮንትራት ስንት ደቂቃ ማርፈድ ይፈቅድላቸዋል? አንተስ በየትኛው ሕግ እንዳይገቡ ትከለክላቸዋለህ?” ሲል ይጠይቀዋል። የሕግ መምህሩ በቁጣ “ለዚህ መልስ መስጠት አይጠበቅቅኝም። በሰአቱ መድረስ የእናንተ የተማሪዎች ኃላፊነት ነው” በማለት ተማሪዎቹን ያባርራል።

ሞጋቹ ጉዳዩ ስለከነከነው ዩኒቲ ኮሌጅ አስተዳደር ሄዶ ጉዳዩን ያጣራል። በኮሌጁ ከተማሪዎች ጋር በሚገባው ኮንትራት መሠረት በተለያዩ ምክንያቶች ተማሪዎች ቢያረፍዱ ለ15 ደቂቃዎች መምህራን ሊታገሷቸው እንደሚገባ ያዝዛል።

በቀጣዩ የትምህርት ቀን ሞጋቹ ተማሪ 15 ደቂቃዎች አርፍዶ ወደክፍሉ ይመጣል። የኮንትራት ሕግ መምህሩ እንደተለመደው ቀድሞ ወደ ክፍል ገብቶ በሩን ዘግቷል። ሞጋቹ ቢያንኳኳ ቢያንኳኳ የሚከፍትለት ያጣል። ሞጋቹ ያለማቋረጥ በሩን ማንኳኳቱን ይቀጥላል። በሁኔታው የተደነቁ ተማሪዎች ከውስጥ ያውካካሉ።

መምህሩ ተናድዷል። ያለማቋረጥ በሚሰማው የማንኳኳት ድምጽ የተበሳጨው የሕግ መምህር በሩን ከፍቶ “ለምን ትረብሸኛለህ? በማርፈድህ መግባት አትችልም” ይለዋል። ሞጋቹ “መግባት እችላለሁ” ይላል። ንግግሩን እንደ ድፍረት የቆጠረው መምህር “አንተ ማን ስለሆንክ ነው አርፍደህ የምትገባው?” ሞጋቹ መለሰ። “ኮሌጁ ስመዘገብ የሰጠኝ ኮንትራት ለ 15 ደቂቃዎች ቢረፍድብኝ ክፍል መግባት እንደምችል ያዝዛል” በማለት ፎቶኮፒ አድርጎ ያመጣውን የኮሌጁን የኮንትራት ሕግ ያሳየዋል።

ክርክራቸውን የሚከታተሉት የክፍሉ ተማሪዎች ቆመው ጭብጨባቸውን ያቀልጡታል።

በክርክሩ የተረታው የኮንትራት ሕግ መምህር በብስጭት ክፍሉን ለቅቆ በመውጣት በቀጥታ ወደ ኮሌጁ አስተዳደር በመሄድ በገዛ ፈቃዱ ማስተማሩን ማቋረጡን እና ሌላ መምህር እንዲፈልጉ ነግሯቸው ከኮሌጁ ይወጣል። እስከወዲያኛውም አልተመለሰም።

ይህ ከሆነ ከዓመታት በኋላ ዩኒቲ ኮሌጅ ወደዩኒቨርሲቲ ሲያድግ በመድረኩ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ ከተጋበዙት ክቡራን እንግዶች አንዱ የዚያን ጊዜው ሞጋች ተማሪ ነበር። ይህተናጋሪ እንግዳም በንግግሩ ከዓመታት በፊት በኮሌጁ የነበረውን ገጠመኝ አስታውሶ “ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ሀገራዊ ተቋሞቻችን የዕውቀት ብቻ ሳይሆን የሞራል እና የመርኅ ማዕከላት መሆን ካልቻሉ እንደ ሀገር የምንፈልገው ቦታ አንደርስም” ብሎ ነበር።

ይህ ሞጋች ተማሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የነበረው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ነበር።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ (ወዳጆቹ እንደሚጠሩት ካሡ) በሀገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲመሠረት እና ነጻ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲያብቡ ላለፉት ለአርባ ዓመታት ያለማቋረጥ አንኳኩቷል። ሰውዬው ከልጅነት እስከ ዕውቀት ለመርኅ እና ለሞራል ከፍ ያለ ዋጋ ይሰጣል።

ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ ቢሉ ከእምነቱ ዝንፍ አይልም። ማንኳኳቱንም አያቆምም። በመስደብ ስሙን በማጥፋት ወይንም በማንጓጠጥ አታሸማቅቀውም። ክርክሩ የድርቅና አይደለም። የዕውቀት እና የመርኅ (Principle) በመሆኑ በእብሪትም ሆነ በሴራ ትገፋው ይሆናል እንጂ አታሸንፈውም።

መልካም የሥራ ጊዜ ካሡ !

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top