Connect with us

የአሸናፊነታችን ሚስጢሩ!..

በሰላም ጊዜ ለጦርነት መዘጋጀት
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የአሸናፊነታችን ሚስጢሩ!..

የአሸናፊነታችን ሚስጢሩ!..

(ፋሲል የኔዓለም)

ፈረንጆቹ ሊያጣጥሉት እንደሚሞክሩት ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ጦር ያሸነፈው ታግሎና አታግሎ ነው። በእኔ እምነት ሰራዊቱ ያሸነፈባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፦

1 የጠ/ሚንስትር አብይ አህመድ ተጽዕኖ

ጠ/ሚ አብይ አህመድ ወደ ጦር ግንባር መዘመታቸው ሶስት ጥቆሞችን አስገኘቷል። አንደኛው፣ በሰራዊቱ ውስጥ ከፍተኛ የመንፈስ መነቃቃትን ፍጥሯል ። ሁለተኛ፣ ሰራዊቱ በጠላት ላይ ለሚወስደው እርምጃ”ፈጣን ውሳኔ” እንዲያገኝ ረድቶታል። ሶስተኛ የአመራር አንድነትና ወጥነት እንዲፈጠር አግዟል። እነዚህ ሶስት ምክንያቶች ቢተነተኑ መጽሃፍ ስለሚወጣቸው ከዚህ በላይ አልሄድም።

2 ህወሃት ለታክቲካል ድል እንጅ ለስትራቴጅክ ድል አለመዘጋጀቱ።

ህወሃት ወረዳዎችንና ከተማዎችን ሲይዝ ከፍተኛ የሰው ሃይልና የጦር መሳሪያዎችን ይገብር ነበር። የሚወድምበትን የሰው ሃይልና የጦር መሳሪያ ለመተካት የሚያስችል አቅም አልነበረውም። እንዳሰበው ከአማራ፣ አፋርና ኦሮምያ ክልሎች የጥይት ማብረጃ የሚሆኑ ወዶ ዘማቾችን በሚፈልግው መጠን አላገኘም። ሃይሉን በየመንገዱ ባደረጋቸው ውጊያዎች በመጨረሱ፣ አዲስ አበባን ለመያዝ የሚያስችለውን የመጨረሻ ምት የሚያሳርፍበት በቂ የሰውና የመሳሪያ ሃይል አልነበረውም። 

ነዳጁን ጨርሶ የመጨረሻውን ጭስ እንደሚያቦን መኪና፣ ህወሃትም ነዳጁን ጨርሶ ደብረሲና ላይ ጭሱን ያቦን ነበር። በአጭሩ ለታክቲካል ድል እንጅ ለስትራቴጂክ ድል አልተዘጋጀም ነበር። የኢትዮጵያ ጦር በአንጻሩ፣ በኣንድ በኩል በመከላከል ውጊያ ህወሃትን እያዳከመና የራሱን ሃይል እየቆጠበ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አዳዲስ የሰራዊት አባላትን እየመለመለና የጦር መሳሪያዎችን እየገዛ ለስትራቴጅክ ድል ሲዘጋጅ ነበር። ውጤቱም በአጭር ጊዜ ውስጥ ታዬ።

3 የአመራሩና የህዝቡ መቀናጀት

ጦርነት የቅንጅት ውጤት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ እና የመንግስት አመራሩ ያሳዩት ቅንጅት፣ ሰራዊቱ የሰው ሃይል፣ የቁስና የመረጃ ክፍተት እንዳያጋጥመው አግዟል። የአዲስ አበባ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ፣ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴና ሌሎችም በርካታ አርቲስቶች፣ አክቲቪስቶችና ጋዜጠኞች የነበራቸው ተሳትፎ፣ ህዝቡ ጦርነቱን እንደ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ እንዲወስድ ማገዝ ብቻ ሳይሆን፣ ለሰራዊቱ ስሜት መነቃቃትም ከፍተኛ እገዛ አድርጓል።

4 የምዕራባውያንና የጎረቤት አገሮች ጫና

ህወሃትን በገባባቸው ከተሞች ሁሉ የፈጸመው ወንጀል ከፈጠረው ቁጣ በተጨማሪ፣ የምዕራባውያን፣ የግብጽና የሱዳን ሴራ የኢትዮጵያን ህዝብ በእጅጉ አበሳጭቷል። ህዝቡ ትግሉን የህልውና አድርጎ እንዲወስድና ህወሃትን ካላጠፋ ህልውናው በማንኛውም ጊዜ አደጋ ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል እንዲረዳና በቆራጥነት እንዲዋጋ አግዟል።

5 የቴክኖሎጂ አጠቃቀም

ህወሃት ድሮንን የመሳሰሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የሚያገኝበት እድል ዝግ ነበር። የኢትዮጵያ መንግስት አለማቀፍ ጫናዎች ቢበረቱበትም፣ በባሌም በቦሌም ብሎ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን መግዛቱ የሚያስመሰግነው ነው። በሱዳን በኩል በቂ የጦር መሳሪያዎች እንዳይገቡ የወሰደው እርምጃም ትክክለኛና ድል እንዲመዘገብ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል የሚጠቀስ ነው።

ጀግናው የኢትዮጵያ ሰራዊት በህወሃት ላይ ድል የተቀዳጀው በእነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች እንጅ፣ ፈረንጆቹ እንደሚሉት በድሮን ብቻ ስለተዋጋ አይደለም። ህወሃት ከአማራና አፋር አካባቢዎች የወጣው ለሰላም አስቦ ሳይሆን፣ ተቀጥቅጦ፣ ተደቁሶ እና እጅግ አብዛኛው ሃይሉን አራግፎ ነው።

( ማስታወሻ የኢትዮጵያ ጦር ወይም የኢትዮጵያ ሰራዊት ማለት መከላከያውን፣ ልዩ ሃይሉን፣ ሚሊሺያውንና ፋኖውን ያካትታል።)

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top