‘ሕዝብ ያስባል’ ብሎ የማያስበው የህወሓት ጭንቅላት
(አሳዬ ደርቤ ~ ድሬ ቲዩብ)
አንዳንድ ፖለቲከኞች ሕዝቡ የሚያስበውን ሲናገሩና የሚመኘውን ሲተገብሩ ይታያሉ፡፡
አንዳንዶቹ ደግሞ ሕዝቡ የሚያስበውን እያወሩ፣ እራሳቸው የሚፈልጉትን ይተገብራሉ፡፡
እንደ ህወሓቶች ያሉት ግን ‹‹ሕዝብ አያስብም›› በማለት ይክዳሉ፡፡ በተለይ ደግሞ እነሱ ከሚበዘብዙት ክልል ውጭ የሚኖረው ሕዝብ ጭንቅላት ሁሉ ያለው አይመስላቸውም፡፡
አፋር እና አማራ ክልል ላይ ያጋጠማቸው ሽንፈትም ‹‹ሕዝብ አያስብም›› ከሚል አመለካከት የመጣ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል አፋር ላይ ወረራ ሲፈጽሙ ይጠብቀናል ብለው ያሰቡት ሕዝብ በመንገዱ ዙሪያ ተንበርክኮ እየሰገደ በእልልታና በጭብጨባ ወደ አራት ኪሎ የሚሸኝ ነበር፡፡ አፋርን አስገብረው ለማለፍ ሲሞክሩ ግን ያጋጠማቸው ሕዝብ፡-
ከፍየል ጥበቃ- ከግመል ኮቴ ስር- ወስኖን የኖረ
በጨው ሥም ሲነግድ፥ ድንጋይ ነህ ተብሎ፥ የተወረወረ
ያ ግፈኛ ጨቋኝ- ነጻ አውጭ ነኝ፥ ብሎ ድጋሜ ከመጣ
በል ከብበህ ደቁሰው- ከገባበት ምድር- አምልጦ እንዳይወጣ›› እያለ የሞትን መራር ጽዋ የሚያስጎነጭ ነበር፡፡
‹‹አያስብም›› ብለው ከሚያስቡት ሕዝብ ያላሰቡትን አልቂት ሸምተው፣ የእርዳታ መጋዘን አቃጥለው፣ የጋሊኮማ ሕጻናትን ጨፍጭፈው የፈረጠጡት የትሕነግ አመራሮች ግን፣ ከዚህ ሽንፈት ተገቢውን ትምህርት በመቅሰም ፈንታ ‹‹የአፋርን ሕዝብ በሰላም አሳልፈንና ከጂቡቲ አስፓልት ጋር የአራት ኪሎን መንግሥት በቁጥጥር ስር እናውልልህ ስንለው ‘እንቢ’ በማለቱ ውሳኔውን አክብረን ተመልሰናል›› በሚል መግለጫ ሕዝብ ያወድም ዘንድ ያስገቡትን ሠራዊታቸውን እንጂ ‹‹ሕዝብ አያስብም›› የሚል አመለካከታቸውን ጥለው አለመውጣታቸውን ይገልጹልኻል፡፡
ለእነሱ ሕይወት የሚሞት ወይም ደግሞ ለእነሱ ወንበር የሚቀበር ሕዝባዊ ሠራዊት መገንባታቸው ኮራ ብለው ይነግሩህና ወረራ ፈጽመው ተጠቂ ያደረጉትን የአፋር እና የአማራ ክልል ሕዝብን ግን የወንበር ጠባቂ በማድረግ ‹‹ለአገኘሁ ተሻገርና ለሃጂ አወል አርባ ሥልጣን ብለው ዋጋ ባይከፍሉ ይሻላቸዋል›› የሚል ምክር ሲለግሱ ትሰማቸዋለህ፡፡
‹‹ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ እንጦሮጦስ ድረስ እንጓዛለን›› በሚል ፉከራቸው ተበሳጭቶ አገሩን ከፍርሰት ሊታደግ የዘመተውን ሠራዊት ክንዱን ከቀመሱት በኋላ፣ ከትናንት ዛቻቸው በተቃራኒ ‹‹ለዶከተር ዐቢይ ወንበር ብለህ ከእጃችን ላይ አትጥፋ›› እያሉ ሲያባብሉት ትታዘባለህ፡፡
አማራ ክልል ገብተው የወረሯቸውን ከተሞች ልቅምቅም አድርገው ከዘረፉና ከጨፈጨፉ በኋላ ወደ ቀጣዩ ከተማ ያመሩና በመድፍ አረር የንጹሐንን ጎጆ እያወደሙ ‹‹ጠባችን ከዐቢይ ጋር ስለሆነ አሳልፉን›› እያሉ ሲጃጃሉ ትሰማቸዋለህ፡፡
የአጋምሳን መንደር በከባድ ጦር መሣሪያ ሲደበድቡ አድረው ወደ መካነ መቃብር እየቀየሩ፣ የሰሜን ወሎን ንብረት በሲኖ ትራክ ሲያጓጉዙ እያደሩ፣ ንጹሐንን ገድለው እየቀበሩ ‹‹የአማራ ክልል ሕዝብ የትግል ዓላማችንን ተረድቶ በፍቅር እያስተናገደን ነው›› የሚል ጥቅም አልባ ፕሮፖጋንዳ ሲነዙ ታገኛቸዋለህ፡፡
ከቻለ እነሱን አራት ኪሎ አስገብቶ የማንገስ፣ ካልቻለ ደግሞ አገር የማፍረስ ተልዕኮ አንግቦ ወረራ የፈጸመውን ታጣቂያቸውን ‹‹ምክንያታዊ ሠራዊት›› መሆኑን በተናገረ አንደበታቸው፣ ከእነሱ ክልል ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ግን ለወንበሩ ይቅርና ለአገሩ አስቦ መዝመቱ ትልቅ ጥፋት መሆኑን ያስረዱኻል፡፡
የእነሱ ሠራዊት የብልጽግናን አመራሮች በቁጥጥር ስር ከማዋል ባለፈ ሕዝብ ጋር ምንም አይነት ችግር እንደሌለበት ከቀባጠሩልህ በኋላ፣ ጥቂት ግለሰቦችን ለመቆጣጠር አስቦ የዘመተውን የኢትዮጵያን ሠራዊት ግን ‹‹የትግራይን ሕዝብ ማስገበር አይቻልም›› በሚል የደንቆሮ መግለጫ ‹‹ሕዝብ ነን›› ሲሉት ትሰማቸዋለህ፡፡
የዚህ ሁሉ ተጣርሶ ምክንያት ታዲያ ‹‹ሕዝብ ያስባል›› ብሎ የማያስብ ጭንቅላት ባለቤት መሆናቸው ነው፡፡