Connect with us

ለእውቅናው እናመሰግናለን!!

ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም

ባህልና ታሪክ

ለእውቅናው እናመሰግናለን!!

ለእውቅናው እናመሰግናለን!!

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም)
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ይኼ ነበር የጎደለው፡፡ እንደ እኔ አንዱንም ላልጀመሩት ሳይሆን ህይወታቸውን ዘርፉን በማገልገል ለጨረሱት ባለውለታዎች ስሳቀቅ ኖሬያለኹ፡፡

ዛሬ በእግሩ መቆም ጀመረ ለሚባለው የሀገሬ ቱሪዝም ዘመናቸውን ቆመው ምትክ የለሽ አበርክቶ የነበራቸው ባለውለታዎች እናመሰግናለን ሲባሉ አይታይም፡፡

በዚህ በኩል ፕሮፌሰር ሂሩት ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ የቀድሞዋ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም የቱሪዝም ባለውለታን እውቅና በመስጠት ባለውለታ ናቸው፡፡ ኢንዱስትሪውን የፈጠሩት፣ የወለዱት፣ ያረሱትና ያሳደጉት አቶ ሀብተ ሥላሴ ታፈሰን በብሔራዊ ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትር እጅ እናመሰግናለን በሚል ሜዳሊያ ሸልመውልናል፡፡

እውነት ለመናገር ታላቁ ሰው ከሽልማቱ በኋላ ብዙም ዘመን አልኖሩም፡፡ ከነ ዕዳችን አልፈው ቢሆን ዛሬ ማናችን ቀና ብለን እንሄድ ነበር?

ሀዋሳ ሀገር ለ34ኛ ጊዜ በብሔራዊ ደረጃ እያከበረችው ባለችው የዓለም ቱሪዝም ቀን ኩነት ኢንዱስትሪው ላይ አስተዋጽኦ ነበራቸው ተብለው እውቅና ከተሰጣቸው ሰዎች መካከል አንዱ ሆኛለሁ፡፡

ይኸ መድረክ በንድፈ ሀሳብም በተግባርም ዘመናቸውንና እውቀታቸውን የሰውት ዶክተር ቴዎድሮስ እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ በተመሳሳይ የአስጎብኚዎች አባት አቶ ጥምቀተም እንዲሁ፡፡

ፋና ወጊዎቹ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሞግዚት ተቋማትና የሀገር ምሰሶዎችም እንዲሁ የመድረኩ ተሸላሚዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድን እንዴት ከኢትዮጵያ ቱሪዝም መነጠል ይቻላል?

ደግሞ የሀገሩ ቱሪዝም በመላ ሲቆም እውቀት ሰጥቶ የሰለጠነ አቅርቦ በዚያ ጨለማ ዘመን ብርሃን መሆን ጀምሮ ዛሬ ድረስ የልቀት ማዕከል በመሆን ውለታው አምስት አስርት ዓመታት ከነክብሩ የኖረውን የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ማዕከልስ?

የቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ከቱሪዝም ጋር መንትያ አይደለም፤ አንድም ሁለትም ሊባሉ የሚችሉ አንድ ገጽታ ያላቸው ተቋማት ናቸው፡፡ እነኚህን እናመሰግናን ማለት ሴክተሩን ማክበር ነው፡፡

ለማኅበራቱ ለውለታቸው እውቅና መሰጠቱም ሸጋ ነው፡፡ በተለይ ከአዲሶቹ ተቋማት ለቱሪዝም ኢትዮጵያ የተሰጠው እውቅናም ጅምሩን ሸጋ አድርጎ ለሚጓዘው ጉዞ ስንቅ ነው፡፡ እንደ ወይዘሮ ሳምራዊት ሞገስ አይነት ምሳሌ የኢንዱስትሪው ሰዎች ስለተከበሩበት ምስጋናዬ ወደር የለውም፡፡

ተነጥቀን ተከበሩ አንልም፡፡ ማክበር ነበረብን ብለን አስበን ተከብረዋል፡፡ ሀገር ሲያከብራቸው ማየት ክብራችን ነው፡፡
በዚህ አግባብ ቤተሰቤ የሆነው ሃይሌ ሪዞርትስ ለአበርክቶው የላቀ አስተዋጽኦ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ ለመዝናኛ ቱሪዝም ጽንሰ ሀሳብ ፈር ቀዳጁ የቅንጡ አገልግሎት አሰጣጥና የአዳዲስ ሀሳቦች ባለቤት ኩሪፍቱ ሪዞርት እና የሀዋሳው ሴንትራል ሆቴል ባለቤትም ለፋና ወጊ ተግባራቸው እንዲሁ ተሸልመዋል፡፡

ሌላው የእኛና የእኔ ዘመን ሰዎች መሸለም፡፡ ኢትዮጵያዊው የዱር ህይወት ፎቶ ግራፈር አዚዝ አህመድ፣ የኢትዮጵያ ሬዲዮ የቀድሞ ኢትዮጵያን እንቃኛት ጋዜጠኛና የአሁኑ የማውንቴን ሚዲያ ባለቤት አስቻለው ጌታቸው፣ እኔ ሄኖክ ስዩምም በዕለቱ እውቅና ከተሰጣቸው መካከል እንገኛለን፡፡

እውነት ለመናገር ይህ ሽልማት ለኢንዱስትሪው አዲስ ነው፡፡ መቀጠል አለበት፡፡ ብዙ ባለውለታዎች አሉን፤ በእነሱ ስኬት የሚኖርን ኢንዱስትሪ ይዞ የስኬቱን ባለውለታዎች ችላ ማለት እዳ መብላት ነው፡፡

የሀዋሳ ቆይታዬ ቀጥሏል፡፡ ምሽት ወደ ታቦር ተራራ ወጥተን ነበር፡፡ ከታቦር አናት ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ በሚል ውብ ቆይታ ሀዋሳን እንደልብ እያየን ያሳለፍነውን ጊዜ እተርክላችኋለሁ፡፡
ፈጣሪ ከኢትዮጵያና ከህዝቦቿ ጋር ይሁን፡፡
***
#ከአዘጋጁ:- ሄኖክ ሥዩም በቱሪዝምና በአካባቢ ጉዳዮች የድሬቲዩብ ምርጥ የምንለው ዘጋቢ/ፀሐፊ ነው። ላገኘኸው ዕውቅና እንኳን ደስ አለህ እንላለን።

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top