Connect with us

ከቤት ሰራተኛነት እስከ ኦሊምፒክ

Social media

መዝናኛ

ከቤት ሰራተኛነት እስከ ኦሊምፒክ

ከቤት ሰራተኛነት እስከ ኦሊምፒክ

ሀያ ሶስተኛ አመት የልደት ሻማዋን ከለኮሰች ገና ስድስተኛ ቀኗ ነው። የእኔ ጥሪ ለአትሌቲክሱ ነው ብላ ብዙ መስዕዋትነትን ከፍላለች። ብዙዎች በማይደፍሩት ብዙዎች በማያውቁት የእርምጃ ውድድር ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ ወክላለች

የኋልዬ በለጠው

የተወለደችው ሰሜን ሸዋ ዞን መሀል ሜዳ ነው። ቤተሰቦቿ ትምህርቷ ላይ እንድትበረታ ይፈልጋሉ። የእሷ ሀሳብ ግን ከሩጫው ጋር ሸፍቷል። ቀለም ቅሰሚ ጥናትሽ ላይ በርቺ የሚሏትን የቤተሰቦቿን ምክር ችላ ብላ ደብተር ማገላበጡን ትታ የእነ ጥሩነሽን ታሪክ መከታተል ስራዋ ሆነ። የስፖርት መምህሯም ወደ ሩጫው እንድትገባ ገፋፋቻት። አጫጭር ርቀቶችን መሮጥ ጀመረች

ቤተሰብ አሁንም ደስተኛ አልሆነም፤ ትምህርት ይሻልሻል የሰርክ ምክርና ቁጣቸው ሆነ። የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ከወሰደች በኋላ ግን ከትምህርቱ ሩጫው ይሻለኛል ብላ ከቤት ጠፋች።

ከከባዱ ህይወት ጋር ግብግብ ገጠመች፤ ልብስ እያጠበች፥ ፅዳት እየሰራች የነገ ተስፋን ሰንቃ ልምምዷን አጠናክራ ቀጠለች። የእለት ጉርስ ለማግኘት በቤት ሰራተኛነት ተቀጥራ እስከ መስራት መገደዷንም በአንድ ወቅት ከኢቲቪ ጋር በነበራት ቆይታ ተናግራለች።አንድ ቀን ያሰብኩበት ቦታ እደርሳለሁ ብላ ለነገዋ ከፍታ ዛሬ ዝቅ ልበል አለችና ለፋች፤ ተስፋ አልቆረጠችም

ወደ ደብረብርሀን አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ሄዳ አስገቡኝ ብላ ጠየቀች። አቅሟን አዩና በ5ሺህና በ10 ሺህ ሜትር እንድትሮጥ ፈቀዱላት፤ ማዕከሉን ተቀላቀለች

የደብረብርሀን ማዕከል አሰልጣኞቿ የእርምጃ ውድድር እንድትሞክርም ጠየቋት። ለስድስት ወር ልሞክረው ብላ ገባችበት። ባህርዳር ላይ በተካሄደው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች በ20 ኪ.ሜ ወርቅ አመጣች። እርምጃ ህይወቴ ብላ ጉዞዋን ቀጠለች

የልጅነት ህልሟን ለማሳካት የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ርቀት ሩጫዎችን ሞክራ በመጨረሻ እርምጃ ላይ አረፈች። ለየት ያለ የአሯሯጥ ስልት ያለው፣ አለም ትኩረት አይሰጠውም የሚባለውን፣ ብዙ አያበላም የሚሉትን የእርምጃ ውድድር መረጠች፤ ጠቅልላ ገባችበት፤ ልምምዷንም አጠነከረች፤ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ስፖርት ክለብን ተቀላቀለች

በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በእርምጃ ውድድር የመጀመሪያውን ወርቅ አመጣች። በአመቱ በሪዮ ኦሊምፒክ በ20 ኪ.ሜ ሮጣ አልተሳካላትም። በአለም ሻምፒዮና ደግሞ ለንደን ላይ 44ኛ እንዲሁም ዶሀ ላይ 16ኛ ሆና አጠናቃለች

የኋልዬ በለጠው በአፍሪካ ውድድሮች ላይ የተሻለ ውጤት አላት። በአፍሪካ ሻምፒዮና ናይጄሪያ ላይ ወርቅ፣ ደቡብ አፍሪካ ላይ የብር እንዲሁም በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ሞሮኮ ላይ የነሀስ ሜዳሊያ በ20 ኪ.ሜ አጥልቃለች፤ የሀገር ውስጥ ክብረወሰንም በእሷ እጅ ነው

የኢትዮ ኤሌክትሪክ ክለብ ሯጭ የሆነችው የኋልዬ አሁን ቶኪዮ ትገኛለች። ዛሬ በሚካሄደው የ20 ኪ.ሜ የእርምጃ ውድድር ብቸኛዋ ኢትዮጵያዊት ሆና ሀገራችንን ትወክላለች። በዛሬው ውድድር 58 አትሌቶች ይሳተፋሉ።

በእርምጃ በአፍሪካ ሁለተኛ ምርጥ ሰዓት ያላት የኋልዬ በለጠው ከቀደመው ኦሊምፒክና የአለም ሻምፒዮናዎች የተሻለ ውጤት ለማምጣት ማቀዷን ተናግራለች። ለዚህም በዘርፉ የካበተ ልምድ ካላቸው አሰልጣኝ ሻለቃ ባዬ አሰፋ ጋር በመሆን ከፍተኛ ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች

በሀገራችን የእርምጃ ውድድር ብዙ ትኩረት ባይሰጠውም የኋልዬ ወደ ኋላ ሳትል ህልሟን እየኖረችው ትገኛለች። ከኩሽና ወጥታ በአለም አደባባይ ሀገርን እስከመወከል ደርሳለች። በዚህ ትኩረት በተነፈገው ዘርፍ ለሚሳተፉ ለእሷና ለመሰል አትሌቶች እንዲሁም ለአሰልጣኞች ምስጋና ማቅረብ የግድ ነው። ውድድሩ ዛሬ አርብ ሀምሌ 30 ከጠዋቱ 4:30 ይጀምራል

ዛሬ ከሰዓት ከ9:00 ጀምሮ የወንዶች 5ሺህ ሜትር የፍፃሜ ውድድር ይካሄዳል፤ ሚልኬሳ መንገሻ ብቸኛ ተወካያችን ሆኖ ይሮጣል። ፍሬወይኒ ሀይሉ የምትሳተፍበት የሴቶች 1500 ሜትር ፍፃሜ ደግሞ ከቀኑ 9:50 ጀምሮ ይከናወናል

መልካም እድል ለአትሌቶቻችን!!!

Via:-tamiru alemu

Continue Reading
Click to comment

More in መዝናኛ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top