የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ቅጣት የተፈረደበትን እስረኛ እንዲያመልጥ በመርዳት ወንጀል የተከሰሰው ግለሰብ በ7 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጣ
ተከሳሽ ብሩክ ኃይሉ የተባለው በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 462(2 ሀ እና ለ) ላይ የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ በ1ኛ ክስ እስረኛ እንዲያመልጥ ማመቻቸትና መርዳት ወንጀል እንዲሁም በ2ኛ ክስ በአንቀጽ 555/ሐ/ ላይ የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ በፈፀመው ከባድ የአካል ጉዳት ማድረስ ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቧል፡፡
የክስ መዝገቡ እንደሚያስረዳው ተከሳሽ በ1ኛ ክስ መጋቢት 20 ቀን 2013 ዓ.ም ከጠዋቱ በግምት 3፡00 ሰዓት ሲሆን በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው አለርት ሆስፒታል ግቢ ውስጥ በወንጀል ተከሶ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመጋቢት 1/2012 ዓ.ም የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ቅጣት የተፈረደበትና በፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ማዕከል የሚገኘውን ሰይድ ደምስስን ለማስመለጥ በማሰብ አጅቦት ይሄድ የነበረውን የግል ተበዳይ ም/ሳጅን ለማ ጣፋን በተለምዶ የሌባ ጎማ ብረት በሚባለው ደጋግሞ በመምታት እንዲወድቅ ያደረገና እስረኛውም የአጃቢ ፖሊሱን ክላሽ መሳሪያ ይዞ እንዲሰወር ያደረገው በመሆኑ በፈፀመው እስረኛ እንዲያመልጥ ማመቻቸትና መርዳት ወንጀል ክሰ የቀረበበት ሲሆን፤ በ2ኛ ክስ ደግሞ በሰው አካል ወይም ጤና ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ከላይ በ1ኛ ክስ በተገለጸው ጊዜ እና ቦታ የግል ተበዳይ ም/ሳጅን ለማ ጣፋን በሌባ ጎማ ብረት ደጋግሞ ጭንቅላቱን በመምታት በራስ ቅሉ የቀኝ ጎን የአይኑ ጉድጓድ ከጆሮ ግንድ የሚገናኝበት አጥንት ስብራት፣ የራስ ቅሉ ብዙ ቦታዎች እና የቀኝ ቅንድቡ የቆዳ ቁስለት ጉዳት እንዲደርስበት ያደረገ በመሆኑ በፈፀመው ከባድ የአካል ጉዳት ማድረስ ወንጀል ተከሷል፡፡
ተከሳሹ የተከሰሰበት ክስ በችሎት ተነቦለት የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምኩም ያለ ሲሆን አቃቤ ህግም ክዶ የተከራከረ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የሚያስረዱ የህግ ምስክሮቻችን ስላሉ ይሰሙልኝ በማለት 3 የሰው ምስክሮችን አቅርቦ በማሰማት እና በተሰሙት ምስክሮች መሰረት ተከሳሽ እንዲከላከል ተገቢውን ብይን ይሰጥልኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም በክሱ አቤቱታ ላይ የተመለከተውን ድርጊት ተከሳሹ ስለመፈፀሙ የአቃቤ ህግ ምስክሮች እንደ ክሱ ያስረዱ በመሆኑ ተከሳሹ በተከሰሰበት በሁለቱም የህግ ድንጋጌ ስር እንዲከላከል የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርብ ቀጠሮ ቢሰጠውም የመከላከያ ማስረጃ የለኝም ያለ በመሆኑ የመከላከያ ማስረጃ የማቅረብ መብቱ ታልፎ ተከሳሹን ይከላከል በተባለባቸው በሁለቱም ድንጋጌዎች ስር ጥፋተኛ ነህ ብሎታል፡፡
ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ኮልፌ ቀራኒዮ ምድብ አር ቲ ዲ /ፈጣን/ የወንጀል ችሎት በተከሳሹ ላይ በቅጣት አወሳሰን መመሪያው መሰረት በእርከን 23 ስር የተመለከተውን ቅጣት ተከሳሹን ያርማል ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያስተምራል ያለውን በ7 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኖበታል፡፡(ፌ/ጠ/ዐ/ህግ)